የካቲት 14 ፣ 2015

ለጤና መድህን ትብብር የነፈገው የአዳማ ከተማ አስተዳደር

City: Adamaጤናወቅታዊ ጉዳዮች

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከሚጠበቅበት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የከፈለው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ብቻ ሲሆን ለዓመታት የታየ ችግር ሆኖ ቢቀጥልም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ለጤና መድህን ትብብር የነፈገው የአዳማ ከተማ አስተዳደር

በኦሮሚያ ክልል ከጥር 1 እስከ የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የጤና መድህን ምዝገባ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን በአዳማ ከተማ ያለው የጤና መድህን አገልግሎት በከተማ አስተዳደሩ ምክንያት እየተበደለ ይገኛል። 

በአዳማ ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ቅርንጫፍ አዳማን ጨምሮ በ3 ዞኖች እና 61 ወረዳዎች ላይ ይሰራል። በቅርንጫፉ ስር የሚገኙ አካባቢዎች ላይ ያለው አፈፃፀም ከቦታ ቦታ የሚለያይ ቢሆንም የአዳማ ከተማ ሁኔታ ግን አሳሳቢ ነው።

የሰላም እና ፀጥታ ችግር ያለባቸው የመተሐራ እና አካባቢው፣ ቦራ እንዲሁም ሊበን ወረዳዎችን የሚይዘው ይህ ቅርንጫፍ የእቅድ አፈፃፀሙ በአሁን ወቅት ከ80 በመቶ በላይ እንደደረሰ ማወቅ ተችሏል። ይሁን እንጂ በዚሁ ቅርንጫፍ ስር የሚገኘው አዳማ ከተማ አፈፃፀም ከ50 በመቶ ብዙም ፈቅ አላለም። አዲስ ዘይቤ ከዚህ ቀደም ባለፈው ዓመት እንዲሁም በ2015 ዓ.ም እንደዘገበችው በአዳማ ከተማ የጤና መድህን እንቅስቃሴ እጅግ ደካማ ነው። 

በአዳማ ከተማ የጤና መድህን አገልግሎት ለመዳከሙ ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን የተጠቃሚዎች ምዝገባ እና የከተማ አስተዳደሩ የመዋጮ ጉዳይ ናቸው። አቶ እንድሪስ አህመድ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የአዳማ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ በስራ ክልላቸው ውስጥ ጥሩ አፈፃፀም መኖሩን ገልፀው የአዳማ ከተማ የጤና መድህን አፈፃፀም ግን ዝቅተኛ እንደሆነ ገልፀዋል። 

በ2014 ዓ.ም ከታቀደው 27 ሺህ በላይ አባዎራዎች ምዝገባ የተከናወነው 10 ሺህ 800 አባወራ ብቻ ነው ያሉት አቶ እንድሪስ፣ ዘንድሮ እየተካሄደ የሚገኘው አዲስ ምዝባም ዝቅተኛ ከመሆኑም ባለፈ እድሳትም ከዓምና ተጠቃሚዎች ግማሾቹ ብቻ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የጤና መድህን አዋጅ በመንግስት ላይም ግዴታ የሚጥል ሲሆን ከጤና መድህን ተመዝጋቢዎች መካከል የ12 በመቶ የሚሆኑትን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ወጪ መሸፈንን አዋጁ ያስገድድዋል፣ ነገር ግን በአዳማ ከተማ እየሆነ ያለው የዚህ ተቃራኒ እንደሆነ የአዲስ ዘይቤ ምንጮች ገልፀዋል።

ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የአዳማ ከተማ ጤና ቢሮ ሰራተኛ እንደገለፁልን በተከታታይ ዓመታት የከተማ አስተዳደሩ አነስተኛ ገቢ ላለቸው ሰዎች እንዲመድብ ከሚጠበቅበት በጀት ግማሹን ብቻ ነው የሚያቀርበው። “በተደጋጋሚ የከተማ አስተዳደሩን ብንጠይቅም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም” ሲሉም የጤና ቢሮው ሰራተኛ ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የአዳማ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ እንድሪስ በጉዳዩ ላይ ባነጋገርንበት ወቅት “የአዳማ ከተማ ከሚጠበቅበት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የከፈለው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወይም 52 በመቶውን ብቻ ነው” ብለዋል።

የኢንሹራንስ ዋናው መርህ መደጋገፍ ነው የሚሉት ስራ አስኪያጁ ይህ ችግር ካለፉት ዓመታት ሲንከባለል የመጣ በመሆኑ በጊዜ ሂደት የበጀት ጉድለት ማምጣቱ እንደማይቀር ይናገራሉ።

ስለበጀት ጉድለቱ ለከተማ አስተዳደሩ በክልል እና በከተማው ጤና ቢሮ በኩል ለማስረዳት መሞከራቸውን የገለፁት ኃላፊው የመክፈያ ጊዜው ባለመጠናቀቁ እስከ ጥር 30 ሊከፍል እንደሚችልም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እንደተቀሩት የዓለም ሀገራት መንግስታት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለዜጎች በፍትሃዊ መንገድ የማቅረብ ኃላፊነት የተጣለበት ነው፤ ዋነኛው ደግሞ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ነው። በተለይም በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ እና አቅመ ደካማ የሆኑ ዜጎችን በአገልግሎቶቹ ጥቅማቸው እንዲከበር ማድረግ ለህገ መንግስቱም ሆነ ለፖለቲካ ተፎካካሪዎች የርዕዮተ ዓለም መነሻ ይሆናሉ።

ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት መከላከልን መርህ ያደረገ የጤና ፖሊሲ ያላት ሲሆን ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የጤና መድህን ፈንድ የተሰኘ ትግበራን እያከናወነች ትገኛለች። 

ምንም እንኳን በአዋጅ ቁጥር 1273/2014 የመንግስት መዋጮ ግድ ሆኖ ቢደነገግም ያለፉት ዓመታትን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ይህንን ግዴታውን እየተወጣ አይገኝም። ይህ በተጨማሪ ከፌደራል መንግስት የሚደረገውን በመዋጮ መጠን ላይ የተመሠረተ ድጎማ እንዳይገኝ እያደረገም ይገኛል።

በዘንድሮው ምዝገባ 7 ሺህ 8 ሰዎች "የደሃ ደሃ" ተብለው መለየታቸውን የሚያሳየው መረጃው የተያዘው በጀት ግን ለግማሾቹ ብቻ የሚበቃ መሆኑን ያሳያል።

ባለፈው 2014 ዓመት በአዳማ ከተማ 28 ሺህ የጤና መድህን ተጠቃሚ ቤተሰቦችን ለመመዝገብ ታቅዶ የተመዘገቡት ግን 49 በመቶ ወይም 13 ሺህ 714 ብቻ ናቸው። ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም በሚጠናቀቀው የዚህ ዓመት ምዝገባ ደግሞ በከተማዋ 58 ሺህ 404 ሰዎችን ለመመዝገብ እቅድ የተያዘ ሲሆን ከዚህ መሃል 13 ሺህ 714 የነባር አባላት እድሳት እንዲሁም 45 ሺህ 724 አዲስ አባላት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

አስተያየት