የካቲት 15 ፣ 2015

ከጦርነት ውድመት መንፈስ ለማገገም የሚፍጨረጨረው የትግራይ ክልል ጤና አገልግሎት

City: Mekelleጤናወቅታዊ ጉዳዮች

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መሻሻሎች ቢኖሩም በ2015 ዓ.ም ስድስት ወራት ብቻ 112 ህፃናት በምግብ እጥረት በጤና ተቋማት ውስጥ ህይወታቸው አልፏል

Avatar: Meseret Tsegay
መሰረት ፀጋይ

መሰረት ፀጋይ በጋዜጠኝነት ስራ ልምድ ያላት ሲሆን የአዲስ ዘይቤ የመቀሌ ከተማ ዘጋቢ ናት።

ከጦርነት ውድመት መንፈስ ለማገገም የሚፍጨረጨረው የትግራይ ክልል ጤና አገልግሎት
Camera Icon

(የፎቶ ምንጭ፡ ዴይሊ ሳባህ ጋዜጣ፤ በትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት የወደመ የጤና ተቋም)

በትግራይ ክልል ከጦርነቱ በፊት የህክምና አገልግሎት እና የመድኀኒት አቅርቦት ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ የነበረ በመሆኑ ድንገተኛ የመድኀኒት እጥረት ቢያጋጥም እንኳን በፍጥነት ይሟላ እንደነበረ የአዲስ ዘይቤ ትዝብትም፣ የነዋሪዎች አስተያየትም ነበር። ይሁን እንጂ በጥቅምት 2013 ዓ.ም. ከተጀመረው ጦርነት በኋላ ግን የነበሩት እንዳልነበሩ ሆነዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው በ2014 ዓ.ም ሙሉ ዓመት የምግብ እጥረት የገጠማቸው ህፃናት ቁጥር 36 ሺህ የነበረ ሲሆን በ2015 ዓ.ም ግማሽ ዓመት ብቻ 28 ሺህ ህፃናት ለምግብ እጥረት ሲዳረጉ 112 የሚሆኑት በጤና ተቋማት ውስጥ ህይወታቸው አልፏል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው የጤና አገልግሎት ደካማ የሚባል ሲሆን ይህም ደግሞ እንደ መቀሌ ባሉ ትላልቅ ከተማዎች እንጂ በትግራይ ገጣራማ ክፍሎች የሚገኙ የጤና ተቋማት በከፊልና ሙሉ ለሙሉ አገልግሎቱ ያቋረጡ እና የወደሙ ተቋማት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።

የመድኀኒት አቅርቦትም በከፍተኛ ደረጃ እጥረት የሚስተዋልበት ሲሆን አንዳንድ ሆስፒታሎች በዚሁ የመድኀኒት እጦት እና  በህክምና መሳሪያ እጥረት ምክንያት አገልግሎት ያቋረጡበት ሁኔታ አለ። የተቋማት መውደምም ሌላኛው የትግራይ ክልል የጤና ዘርፍ ተግዳሮት ሲሆን በዚህ ምክንያት ደግሞ አገልግሎት ማግኝት የነበረባቸው ሰዎች ህክምና እና መድኀኒት ባለማግኘታቸው ለሞት እና ወደ ላልተገባ እንግልት እየዳረጋቸው ነው።

አዲስ ዘይቤ በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ከደረሰባቸው የጤና ተቋማት አንዱ ወደሆነው ሃገረ ሰላም ሆስፒታል አቅንታ አሁናዊ ሁኔታዎችን ለመታዘብ ችላለች። ሃገረ ሰላም ሆስፒታል ከጦርነቱ በፊት የተሟላ በሚባል ደረጃ ግልጋሎት እየሰጠ የነበረ ተቋም ሲሆን አሁን ግን በጦርነቱ ወቅት በገጠመው ችግር ሙሉ ለሙሉ ከአገልግሎት ውጪ ሆኗል። 

አዲስ ዘይቤ በሆስፒታሉ ተገኝታ እንደተመለከተችው የተገልጋዮች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም ለህክምና ሄደው አገልግሎት ሳያገኙ የሚመለሱ ሰዎች ቁጥራቸው የበዛ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በሆስፒታሉ የሰራተኛ እጥረት መኖሩ ችግሩን የከፋ እንዳደረገው አዲስ ዘይቤ ታዝባለች።

በትግራይ ክልል ትልቁ የህክምና ተቋም የሆነውና በክልሉ መቀመጫ መቀሌ የሚገኘው አይደር ሆስፒታል በዚህ ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ለስኳር ታማሚዎች የሚሰጥ አንዲት የኢንሱሊን መርፌ እንኳን ማቅረብ የማይችልበት ሁኔታ ላይ እንደደረሰ እና የኩላሊት እጥበትም ሆነ በበሽታው የተጎዱ የሰውነት አካላትን ቆርጦ ለማስወገድ እንኳን አስፈላጊ ቁሳቁሶችና የህክምና ግብአቶች ማጣቱን አስታውቆ እንደነበረ ይታወሳል።

በሃገረ ሰላም ከተማ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም በሆስፒታሉ ያለው አገልግሎት እና የህክምና ፈላጊዎች ቁጥር አለመመጣጠን እንደሚታይ ገልፀውልናል። አቶ ገብረመድህን አሳይ የከተማው ነዋሪ ሲሆኑ አሁን ከተገኘው የሰላም ሁኔታ አንፃር ሃገረ ሰላም ሆስፒታል የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልገው ሁሉ ሊሟላለት ይገባል ብለዋል። 

በተጨማሪም በአንቡላንስ እጥረት በርካታ እናቶች በቤት ውስጥ የመውለድ ሁኔታ እየሰፋ ሲሆን ያሉትን ኣንቡላንሶች ለመጠቀም ደግሞ የነዳጅ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ አለመኖሩን ተከትሎ “የእናቶች ሞት እና በመድኀኒት እጦት የሚሞቱ ሰዎችን ለመታደግ ትኩረት መደረግ አለበት” ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች አሳስበዋል።  

በትግራይ ክልል በጦርነቱ ሳቢያ የገጠሙ ችግሮች አሁን በሰላሙ ጊዜም የቀጠሉ መሆናቸውን የሚያመላክቱት የህክምና ባለሞያዎች እጥረት እና የሰራተኞች ሙሉ በሙሉ ወደስራ አለመመለስ፣ የህክምና መሳሪያ እጥረት፣ የመድኀኒት እጥረት እንዲሁም ለአገልግሎቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና የሰው ኃይል ከተገልጋዮች ብዛት ጋር የተራራቁ እንዲሆኑ አድርጓል። 

በህዳር ወር 2015 ዓ.ም የጤና ሚኒስቴር በትግራይ ክልል የህክምና አገልግሎት ለማስጀመር እና የመስክ ምልከታ ለማድረግ ባለሙያዎችን ወደ ሽሬ፣ አክሱም እና አድዋ ልኮ የነበረ ሲሆን በወቅቱም ከ111 ሚልየን ብር በላይ የሚያወጡ የህይወት አድን መድኀኒቶች እና የህክምና ግብዓቶች ወደ ትግራይ ክልል መድረሳቸው ተዘግቦ ነበር።

በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ለድፍን ሁለት ዓመታት በቆየው ጦርነት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች የመሰረት ልማት ውድመት እና ዝርፊያ ተበራክቶ የቆየ ሲሆን በጤና ዘርፍ ላይ በደረሰው ጉዳት የሰዎች ህይወት አልፏል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በትግራይ ክልል ብቻ 6 ሚልየን ሰዎች የጤና ቀውስ ውስጥ ገብተው ነበር።

የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴርም እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም ከ2 ሺህ 700 የሚበልጡ የጤና ተቋማት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን አስታውቆ ነበር ቢያንስ 1.4 ቢልየን የአሜሪካ ዶላር የወደሙትን የጤና መሰረተ ልማቶች ለመመለስ እንደሚያስፈልግ ተመላክቶ ነበር። 

አስተያየት