መጋቢት 8 ፣ 2015

ኢትዮጵያውያን በሱዳን የመኖሪያ ፈቃድ የላችሁም በሚል እየታፈሱ መሆኑን ገለፁ

City: Adamaወቅታዊ ጉዳዮች

በሱዳን የኢትዮጵያ ኤንባሲ አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት እና ለማደስ 150 ዶላር እንዲሁም ለጠፋ ፓስፖርት ምትክ ለማውጣት 350 ዶላር የሚያስከፍል ቢሆንም የተቀላጠፈ አሰራር አለመኖሩ የዜጎችን ችግር አብሶታል

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ኢትዮጵያውያን በሱዳን የመኖሪያ ፈቃድ የላችሁም በሚል እየታፈሱ መሆኑን ገለፁ
Camera Icon

(ሱዳን የሚገኙ ስደተኞች ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ለአዲስ ዘይቤ የላኩት)

በሱዳን ሚገኙ ኢትዮጵያውያን ህጋዊ ሆኖ ለመሰንበት ይጠየቁ የነበረው የመኖሪያ ፍቃድ ቀርቶ በፓስፖርት ቢተካም ፓስፖርት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በዘመቻ መልክ የመኖሪያ ፍቃድ (ኢቃማ) የላችሁም በሚል እየታሰሩ መሆናቸውን ይከሳሉ።   

በሱዳን ያለውን የኑሮ ውድነት እና የስራ-አጥ ሱዳናውያን ቁጥር ማሻቀቡን ተከትሎ በኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እንዲሁም የሌሎች ሀገራት ስደተኞች ላይ በሱዳን መንግስት የጸጥታ ኃይሎች የሚደረገው ጫና መበርታቱን ስደተኞቹ ገልፀዋል።

በሱዳን የኢትዮጵያ ኤንባሲ ለተማሪዎች እና ለአዋቂዎች አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት እና ለማደስ 150 ዶላር፣ ለጠፋ ፓስፖርት ምትክ ለማውጣት 350 ዶላር የሚያስከፍል ቢሆንም፤ አገልግሎቱ ግን በተቀላጠፈ ሁኔታ ባለመስጠቱ ዜጎች ለችግር እየተጋለጡ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ህጋዊ መኖሪያ ፍቃድ (ኢቃማ) ያላት እና ካርቱም በሚገኝ ዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ ሰራተኛ የሆነችው አስታያየት ሰጪ እንደገለጸችው ምንም እንኳን ህጋዊ ፍቃድ ቢኖራትም ከተማው ውስጥ በጸጥታ አካለት እና በስደተኞች መካካል የሚደረገውን ሰዶ ማሳደድ በየቀኑ እንደምትታዘብ እና ህጋዊ ፈቃድ ለማውጣት ያለው ክፍያም በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን ትናገራለች። 

ኢትዮጵያውያንን ማፈስ ከዚህ በፊትም የነበረ ነው የሚለው ሌላኛው የካርቱም ነዋሪ ኢትዮጵያዊ አሁን ግን በሁሉም የውጪ ዜጎች ላይ ጫናው በርትቷል ይላል። አስተያየት ሰጪው እንደሚያነሳው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የመኖሪያ ፍቃድ ስለሌለው ጫናው ኢትዮጵያዊያን ላይ እንደሚብስም ይናገራል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በተመሳሳይ በስደተኞች ላይ በርትቶ የነበረውን እስር እና እንግልት አዲስ ዘይቤ መዘገቧ ይታወሳል። ከሳምንት በፊት በተጀመረው አፈሳ ቅጣቱ 5 መቶ ሺህ የሱዳን ፓውንድ መሆኑን የገለጸው የመረጃ ምንጫችን ለተከፈለው ክፍያ ደረሰኝ የማይሰጥ በመሆኑ ቢከፈልም ድጋሚ መታሰር ሊኖር እንደሚችል ያለውን ሁኔታ የከፋ እንዳደረገው ይገልፃል። 

ከዚህ ቀደም በ2014 ዓ.ም. አዲስ ዘይቤ በሰራችው ዘገባ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ካርቱም ለሚገኘው ኤምባሲ ከለላ እንዲደረግላቸው በጠየቁበት ወቅት ከኤምባሲው ኃላፊዎች “ዲፕሎማሲያችን የተበላሸ በመሆኑ ምንም ማድረግ አንችልም” የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተናግረው ነበር።

ለአዲስ ዘይቤ ቅሬታቸውን የተናገሩት በካርቱም እና አካባቢው የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ፓስፖርት ለማውጣት የተመዘገቡ ቢኖሩም ፓስፖርት በበቂ ሁኔታ እየመጣ አይደልም ይላሉ። እንደትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ ሪፖርት የሱዳን ስራ አጥ ዜጎች ምጣኔ በአውሮፓውያኑ 2023 ዓመት የመጀመሪያ ወራት 22 በመቶ ደርሷል።

አስተያየት