የአዲስ ዓመት ዘፈኖች ትዝታ

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታጳጉሜ 5 ፣ 2013
City: Addis Ababaባህል
የአዲስ ዓመት ዘፈኖች ትዝታ

ኢትዮጵያውያን ለበዓል ልዩ ስሜት አላቸዉ። በዓላትን ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በተቻለ አቅም በልዩ ስሜት ለማሳለፍ ይጥራል። ከዚህ አኳያም ማንነታችንን በሚያጎሉ ወግ እና ባህል መሰረት ታጅቦ በዓልን ማክበር አንዱ መገለጫችን ነው።

በዓልን ለየት አርጎ ማሳለፍ ሲባል ቤት ከማጽዳት፣ አልባሳት ከመግዛት፣ ዶሮ፣ በግ እና የመሳሳሉትን ለመግዛት ከሚኖር የገበያ ግርግር እና መሰል ቅድመ ዝግጅቶች አንስቶ ለዋዜማው የሚኖሩ የምግብ እና የመጠጥ ዝግጅቶች ድረስ እንዲሁም የበአሉን ቀን ጨምሮ የሚኖሩትን ድባቦች በማጉላት እና ትዝታ በማስቀረት ረገድ ሙዚቃዎች ያላቸው ሚና ይህ ነው የሚባል አይደለም።

በአዲስ አመትም ወቅቱ ከመዋቡ እንዲሁም አዲስ ተስፋ የመሰነቅ እና ከአሮጌ የመላቀቅ ውብ ስሜት አብሮ ከመምጣቱ ባለፈ 

የዘመን መለወጫ ሲመጣ ከሚሰሙን ልዩ ልዩ ስሜቶች ጋር ሳይነጣጠሉ የበዓል ሙዚቃዎችም ከነስሜታቸው ይከተላሉ። ከቄጤማ፣ ከአደይ አበባ፣ ከችቦ እና ከአበባይሆሽ ጭፈራ በተጨማሪ ድባቡን የሚያሳምሩልን ዘመን የማይሽራቸው ዜማዎች አሉን። እንደውም “በበኩሌ እነዚህን ዜማዎች ካልሰማሁ በዓሉ በዓል አይመስለኝም” የሚሉና “ከአዲስ አመት ጋር የተያያዙ ዜማዎች ናቸው እንቁጣጣሽ ከሌሎች በዓላት የተለየ ስሜት እንዲያሰማን የሚያደርጉት” የሚሉ ሰዎችን መስማት የተለመደ ነው።

ይህን አስመልክቶም ከእነዚህ ዘመን አይሽሬ ሙዚቃዎች መካከል ሰባቱን ለማውሳት ወደድን

፩. እንቁጣጣሽ- ዘሪቱ ጌታሁን

አዲስ ዘመን በአደይ አበባ ተሞሽሮ ሲመጣ፣ በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን 

እንቁጣጣሽ

እንኳን መጣሽ

በአበቦች መሐል

እንምነሽነሽ 

አበባ... በሚል የዝግታ ዜማ ተጀምሮ ሞቅ ወዳለ ሙዚቃ የሚሻገረውን የዘሪቱ ጌታሁንን ሙዚቃ የማይሰማ አይኖርም ቢባል ውሸት አይሆንም። 

ይህ በብዙኃኑ ዘንድ ተወዳጅ የሆነውና ግጥምና ዜማው በክቡር ዶክተር አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) የተደረሰው ዜማ ከአደይ አበባ እኩል ለኢትዮጵያውያን የእንቁጣጣሽ በዓልን ብስራት መናገሩን ይዞ ዘመናትን መሻገሩን ቀጥሏል።

"መስከረም ጠባ እሰይ እሰይ" በማለት የመስከረም መጥባት ያለውን የደስታ ስሜት እያነሳች ፍካት፣ ውበት፣ አደይ አበባ የሚያጋባውን ስሜት ታወሳለች። ከዛም አልፋ "ኢትዮጵያ ሀገሬ የምመኝልሽ፣ በአዲሱ አመት እንዲያምርብሽ" እያለች ሁሉም መስከረም ሲጠባ ለሀገሩ ሁሌም እንደ አዲስ ለሀገሩ ለየት ያለ ምኞት እንደሚመኝ ታሳያለች።

፪. ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ... "የ13 ወር ፀጋ"

"በፀሐይ ብርሃን ደምቃ ክረምትና በጋ

የትውልድ ማገር ያላት የ13 ወር ፀጋ

ወግና ልማዳችን የወረስነው ካበው 

የአውደ አመቱ ትዝታ አይጠፋም ህያው ነው…"

እያለ ሚቀጥለው ሙዚቃም አዲስ አመት በመጣ ቁጥር ቢሰማ የማይሰለች እና የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ የሆነውን የ13 ወር ፀጋ ከበዓላት ሽታ፣ ወግና ጠረን ጋር አቅፎ የያዘ ውብ ዜማ ነው።

በ1980 የወጣው ይህ ሙዚቃ ግጥሙ በክፍለእየሱስ አበበ እና ታምራት አበበ ሲሰራ ዜማው ደግሞ በታምራት አበበ የተደረሰ ነው። 

"ግንቦት ሰኔም አለፈ ዳመና አያለበሠ

ሐምሌም በክረምት ዝናብ መሬቱን አያራሰ

ልጆች በየቤታቸው ለሆታ ሲጠራሩ

ከጅራፉ ጩኸት ጋር የቡሔን በአል ሲያከብሩ" ሲልም ከትውልድ ትውልድ የተላለፈውን የልጅነት ባህል ከወቅቱ መለዋወጥ ጋር አዋዝቶ በዜማ ይናገራል።

፫. ሰለሞን ደነቀ " ስርቅታዬ" 

በየአመቱ ከቡሄ እስከ እንቁጣጣሽ ባለው የአዲስ ዘመን መቀበያ ጊዜ ‘ስርቅታዬ’ በተሰኘው እና

“... ትምህርት ቤት ተከፍቶ፣ ሁሉም ረፍት ጨርሶ

ለእንቁጣጣሽ ዝግጅት፣ ቅዱስ ዮሐንስ ደርሶ

ሁሉም ብቅ ብቅ ሲል፣አዳዲስ ልብስ ለብሶ

ቤቱ ተጎዝጉዞ በለምለም ቄጤማ

ታስነኪው ነበረ እንዲህ በሚል ዜማ

አበባይሆሽ

ለምለም…”

እያለ በሚቀጥለው የተወዳጁ ድምፃዊ ሰለሞን ደነቀ ሙዚቃ የበአል አከባበሩን ድምቀት እና ወደ የልጅነት ጣፋጭ ጊዜን ፍንትው አድርጎ  የሚያስታውስ አይረሴ ዜማ ነው። ከነሀሴ እስከ መስከረም ባለው ወቅት መገናኛ ብዙሃንም በዚህ ሙዚቃ ብዙሃኑን “ስቅ” እያስባሉ ወደ ኋላ በትዝታ ማስኮብለላቸውን ይያያዙታል። እንደውም ከዚህ ሙዚቃ ጋር በተያያዘ ድምጻዊ ሰለሞን በህይወት በነበረበት ወቅት ለጋዜጠኛ ተወልደ በየነ ያጫወተው ፈገግ የሚያሰኝ ገጠመኝ ይታወሳል።

ነገሩ እንዲህ ነበር ሰለሞን ስርቅታዬን ዜማ ለመስራት ሲያስብ ሃሳቡ ከልጅነት ዕድሜ ጋር የተያያዘ በመሆኑና በዕድሜ የሚያንሱ የድምጽ ተቀባይ ህጻናት በማስፈለጋቸው ጥቂት ህጻናትን መርጦና ስለሁኔታው አስረድቶ ለስላሳና ኬክ ጋብዞ ሙዚቃው ወደሚቀረጽበት ስቱዲዮ ይዟቸው ይሄዳል። ህጻናቱ የተነገራቸው የተቀባይነት ሚና ኩኩሉ ሲባል አልነጋም አበባዮሽ ሲባል ለምለም ብለው እንዲቀበሉ ነበር። ስቱዲዮ ከደረሱ በኋላ ሰለሞን ህጻናቱን አስቀምጦ ከሙዚቀኞቹ ጋር የሙዚቃ መሳሪያዎችን በማሰናዳት ሂደት ላይ ተጠምዶ ለሰዓታት ረጅም ጊዜ ያጠፋል። ኋላ ላይም የዘፈኑ ቀረጻ ይጀመራል።

ሰለሞን የራሱን ግጥሞች በሚገባ ከተጫወተ በኋላ ወደቅብብል ግጥሞቹ ተሻግሮ ሲያዜም የሚቀበለው ያጣል። ያኔ ወዳ መጣቸው ዞር ብሎ ሲመለከት ለካስ በሚሪንዳና በኬክ ጠግበው እንቅልፍ ይዟቸዋል። ያ አልፎ ህጻናቱን የማሳተፉ ሃሳብ ተሰርዞ በድምጻዊት የሺእመቤት ዱባለ ና ጥቂት ድምጻውያን ተቀባይነት ሙዚቃው ባማረ ሁኔታ ተሰርቶ ለህዝብ በቃ። 

፬ አስቴር አወቀ - እዮሃ አበባዬ

“እዮሃ አበባዬ

መስከረም ጠባዬ

መስከረም ሲጠባ 

ወደ ሀገሬ ልግባ

ወደ አዲስ አበባ…” እያለች በተስረቅራቂ ድምጿ ስታዜም አብሯት የሚያዜመው ሰው ስፍር ቁጥር የለውም።  

በዚህ ዘፈን እንቁጣጣሽ በመጣ ቁጥር ሴቶች እየዞሩ ሚዘፍኑትን አበባየሆሽ ግጥም በሙሉ የምትለው ሲሆን በአዚያዚያም ዘዬዋ ሁሉም ሰው ልብ ውስጥ መቅረት የቻለና ከእንቁጣጣሽ አከባበር ጋር ላይለያይ የተሳሰረ ውብ ሙዚቃ ነው።

፭ ሀመልማል አባተ- እንኳን አደረሳችሁ

“የክረምቱ ወር አልፎ የበጋው መጥቷል

ሜዳው ሸንተረር ጋራው በአበቦች ደምቋል

ሸመንሟናዬ ውድ ሽቅርቅሩ

ድረስ ለአውድአመት በአገር መንደሩ”

የሚለው ሙዚቃ መግቢያዋ ላይ ከምታስቀድመው እልልታ ጋር የሰዉ ጆሮ ሲደርስ አዲስ አመት አዲስ አመት መሽተቱ ያይላል። ይህን ዜማ የበዓል አከባበርን ወግ እና ባህል ከሚያሳየው የሙዚቃ ቪድዮው ጋር ከዋዜማው ጀምሮ የማያስተላልፍ ቴሌቪዥን ጣቢያ የለም ለማለት ያስደፍራል።

"እንኳን አደረሳችሁ እንኳን አደረሳችሁ

እስኪ እልል እልል እንበል እስኪ እልል በሉ ሁላችሁ" እያለች በዜማ ምታደርሰው መልካም ምኞት ሙዚቃው ባልተከፈተበት ሁናቴ ውስጥ ሁሉ አውድአመት ስለሆነ ብቻ በጆሮ ያቃጭላል።

 ፮ ቴዎድሮስ ካሳሁን - አበባየሆሽ

የኢትዮጵያ ሚሊኒየምን ተከትሎ በአዲስ አመት ከተለቀቁ ሙዚቃዎች መካከል አንዱ ነው። አዲስ ዘመንን ተከትለው የሚመጡ ተስፋዎችን ሰንቆ ይዞ በአዲስ አመት መባቻ ሲሰማ መጪው አመት ጥሩ ይሆናል የሚል ንግርት በውስጣችን እንዲሰርጽ ያደርጋል።

“ምልኤላዊው ዘመን

የአምላክ በረከቱ

በኢትዮጵያ ትንሳኤ

ዘመነ ሁለቱ

ስትሰሙ መለከት

ወደ ምስራቅ ተመልከቱ…”

በማለት ለስለስ አድርጎ ጀምሮ አበባየሆሽ በመባል የሚታወቀውን የሴቶች ዜማ መነሻ በማድረግ ሞቅ አድርጎ የምርቃት እና የተስፋ ግጥሞቹን በውብ ዜማ ያወርደዋል።

በዚህ ሙዚቃ ቴዲ ከአዲስ አመት ጋር አያይዞ ለሀገሩ ትንሳኤ መድረሱን፣ መሰናክሎቿን ሁሉ አልፋ እና ጠላቶቿን አሸንፋ ልክ እንደ ዘመኑ የስም ስም እንደሚቀየር እንዲህ እያለ በዜማው ይነግረናል፦

"ሰለሞን አለ ጊዜ ለኩሉ

ይሰግዱልሻል የናቀሽ ሁሉ" እያለ ለሀገር የለውን ህልም ይናገራል።

፯ ሀሊማ አብዱራህማን- እዮሃ አበባ

“አበባው አበበ እዮሃ አበባ

ላየው መጥቻለሁ እዮሃ አበባ

ከአፋፍ ከገደሉ እዮሃ አበባ

አብሬህ እውላለሁ እዮሃ አበባ

ካጎረሰኝ እጅህ ርቄ ሰንብቻለሁ

አቤ ያደግኩበት ናፍቆኛል መንደሩ

እንዴት ከርሞ ይሆን ወገን ገራገሩ …”

እያለች ሆድ በሚያባባ ዜማ እና ግጥም በአባቷ የመሰለችውን ሀገሯን ለአዲስ አመት የምትጎበኝበትን መንገድ ታወጋለች። ይህ ሙዚቃ በተለይ በስደት ላይ ሲኮን የሚያጋጥመውን አውድአመትን በቤት የማሳለፍ ናፍቆት እና ህልም ያጋባል። ሆኖም ስትዘፍን ስደተኛውም በሀገሩ ኗሪውም አብሮ ስሜቷን እየተጋራ እያቀነቀነ ከዓመት ዓመት አዲስ አመትን ይቀበላል።

እንዲህ እንዲህ እያሉ ለመዘርዘር አያሌ ሙዚቃዎች በዓላትን ማድመቃቸውን አሁን ድረስ ቀጥለዋል። እኛም እንደተጠቀሱት እና ሌሎች አውድ ዓመትን በተለይም አዲስ ዘመንን ለመቀበል የሚኖረውን ስሜት የሚያጎለብቱ ሙዚቃዎች እንደሚመርቁት በመመረቅ ወጋችንን እንቋጭ። 

አመቱ ግጥማችን ይሁን፣ ሆሳው ይነሳ፣ እማይበጀንን ገለል ይበል፣ ለከርሞ በአማን ያድርሰን ፣ ለአገርና ለህዝብ ደግ ደጉን ያምጣልን፣ እንደ በሬ ሻኛ ከሰው በላይ ያውላችሁ፣ የእድሜ ጎዳና ይስጥልን፣ አገሩ ጥጋብ ቀየው ሰላም፣ አውድማውን ፍሬያማ ያድርግልን! አሜን!

መልካም አዲስ አመት

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist is working as a reporter and content creator at Addis Zeybe to explore her passion for storytelling. She has Bsc. in medical laboratories & BA in media and Communications.