መስከረም 5 ፣ 2014

ኢትዮጵያ እና ኬንያ የድንበር ላይ ንግድ ስምምነት ተፈራረሙ

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

የኢትዮጵያ እና የኬንያ መንግሥታት የአንድ-አለቅ (one stop) የድንበር አገልግሎትን ለመተግበር የሚያስችል ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

ኢትዮጵያ እና ኬንያ የድንበር ላይ ንግድ ስምምነት ተፈራረሙ

የኢትዮጵያ እና የኬንያ መንግሥታት የአንድ-አለቅ (one stop) የድንበር አገልግሎትን ለመተግበር የሚያስችል ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል። ድንበር ተጋሪ ሐገራቱ በአዲስ አበባ- ኢትዮጵያ ራዲሰን ብሉ ሆቴል በተካሄደ ስነ-ስርአት የስምምነት ፊርማቸውን ባኖሩበት ወቅት ከሁለቱም ሃገራት የተጋበዙ የመንግሥት ባለስልጣናት እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ስምምነቱ በሀገራቱ መካከል የሚካሄደውን የንግድ ትብብር ቀልጣፋ እና ውጤታማ ያደርጋል ተብሏል። የማእከሉ የአሰራር ሂደት መመሪያ የሁለቱ ሃገራት የድንበር ነክ ጉዳዮችን የሚቆጣጠሩ የመንግሥት ተቋማት ሰራተኞች የተቀናጀ የድንበር አስተዳደር ሥራዎችን በውጤታማነት መተግበር እንዲችሉ የሚያስችል ነው ተብሏል።

በመሆኑም ድንበር ለማቋረጥ መሟላት ያለባቸው ተገቢ የቁጥጥር ደንቦችን ባከበረ መልኩ በማእከሉ የሚስተናገዱ ነጋዴዎች፣ የጭነት አገልግሎት አቅራቢዎች ወይም አጓጓዦችና ሌሎች መንገደኞች ጊዜ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ እንዲስተናገዱ ያደርጋል።

ከፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ጎን ለጎን ከሁለቱም ሐገራት የተውጣጡ የግሉ ዘርፍ ተቋማትና አባላት የተሳተፉበት በሞያሌ አንድ-አለቅ የድንበር አገልግሎት ማዕከል ላይ የሚያተኩር ወርክሾፕም ተካሂዷል። 

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ባደረጉት ንግግር “ሁለቱ ሃገራት ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የወዳጅነት ግንኙነት ቢኖራችውም ሃገራቱ ካላቸው የንግድ ግንኙነት አቅም እና እድል አኳያ ሲታይ የንግድ ልውውጥ መጠናቸው ከግምት ያማይገባ ሆኖ ቆይቷል" ብለዋል።

አያይዘውም በአሁን ሰዓት ይህ ሁኔታ እየተቀየረ በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል የሚካሄደው ንግድ በዓይነትም ሆነ በመጠን በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝ በመግለፅ "የማእከሉ አገልግሎት መስጠት መጀመር ደግሞ የሁለቱን ሃገራት የንግድ ልውውጥና የተቀላጠፈ የመንገደኞች እንቅስቃሴን የበለጠ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ብለዋል።

“የአሰራር ሂደት መመሪያው መፈረም ሁሉም ሂደቶች በተገቢው መንገድ የተፈተሹና እንዲጣጣሙ የተደረጉ ለመሆኑ ማስተማመኛ ይሆናል።" ያሉት ዋና ፀሃፊው በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል የሚካሄድ ንግድና ትብብር ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚካሄድ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል ሲሉም ተናግረዋል።

የሞያሌ - ሞያሌ አንድ-አለቅ የድንበር አገልግሎት ማእከል ትሬድማርክ ኢስት አፍሪካ በተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከእንግሊዝ መንግሥት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የቴክኒክና መሰል እገዛ የሚደረግለት ሲሆን ጠቅላላ የመሰረተ ልማት ግንባታው የተከናወነው በአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም የኬንያና የኢትዮጵያ መንግሥታት በመደቡት በጀት መሆኑ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ሲሆኑ በኬንያ በኩል የኬንያ ልዑካን ቡድን መሪና የሃገሪቱ የድንበር አስተዳደር ሴክሬታሪያት ዋና ጸሃፊ ሚስተር ኬኔዲ ኒያዮ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡ 

የአገልግሎት ማእከሉ ኅዳር 30/2013 በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድና በኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ከኒያታ በይፋ ተመርቆ ሰኔ 1/2013 አገልግሎት መስጠት መጀምሩ ይታወሳል።

 

ለፈጣን መረጃዎች የአዲስ ዘይቤ የማህበራዊ ሚዲያዎችን ይቀላቀሉ፡

Twitter :  https://twitter.com/AddisZeybe
Facebook :  https://bit.ly/2SeU3Ev
Telegram : https://t.me/AddisZeybe
Website : https://addiszeybe.com/
YouTube : https://youtube.com/c/AddisZeybe
Instagram : https://bit.ly/3D1tEwC
LinkedIn : https://bit.ly/385nbCl

አስተያየት