መስከረም 6 ፣ 2014

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ

City: Addis Ababaዜናዎች

የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የሚያስችለውን ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ
Camera Icon

Photo: fklm-tours.com

የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የሚያስችለውን ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን ከሀገራችን ታላላቅ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል አንዱ የሆነውን ብሄራዊ ፓርክ በዩኔስኮ የአለም የተፈጥሮ ሀብት ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ለማስመዝገብ ላለፉት 12 ዓመታት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልፀው በአሁኑ ሰዓት ሁሉንም መስፈርት ማሟላቱን የሚገልፅ ዶክመንት ተዘጋጅቶ ውሳኔውን ለማስፀደቅ የዩኔስኮ 44ኛው ጉባኤ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ገልፀዋል። 

“ብሔራዊ ፓርኩ ከሀገራችን ታላላቅ ሀብቶች መካከል አንዱ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በቅርስነት በዩኔስኮ ለማስመዘገብ የሚያስችሉ ሥራዎች ላለፉት አመታት ሲሰሩ ቆይተው በአሁን ሰአት ሁሉም ስራዎች ተጠናቀው የባሌ ብሄራዊ ፓርክን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየጠበቅን ነው” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ካሏት ብሄራዊ በፓርኮች ውስጥ በዩኔስኮ የተመዘገበው ብቸኛ ፓርክ ሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ሲሆን የባሌ ተራራሮች ብሄራዊ ፓርክ ሁለተኛ ተመዝጋቢ እንደሚሆን ይጠበቃል። ምዝገባው ፓርኩ የዓለም ዐቀፍ ትኩረትን ማግኘት እንዲችል እና የተፈጥሮ ሀብቱን በጠበቀ መልኩ የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት ያስችለዋል ሲሉ ሀላፊው አክለው ገልፀዋል።

ምክትል ዳይሬክተሩ በመስፈርቱ የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ  በውስጡ የያዛቸውን የተፈጥሮ ብዝሃ ሀብቶች እና አሁን ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ የሚችል ሠነድ መዘጋጀቱን ጠቅሰው አሁንም ግን ፓርኩ ላይ የሚስተዋሉትን ችግሮችን ለመቅረፍ የሁሉም የተቀናጀ ትብብር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

“የሕዝብ ቁጥር መብዛት እና የተፈጥሮ ሀብት ፍላጎት ከፍ ማለት በብሄራዊ ፓርኮች አይነተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል። ከጫናዎቹ መካከልም ግጦሽ፣ እርሻ፣ ደን ጭፍጨፋ እና  ሕገ-ወጥ ሰፈራዎች ይጠቀሳሉ” የሚሉት አቶ ሰለሞን በመንግስት በኩል እነዚህን ሕገ-ወጥ ተግባራት ለማስተካከል የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን እና እየተሰሩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

በ1962 ዓ.ም የተመሰረተው የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ከአዲስ አበባ በ4ዐዐ ኪ.ሜ ርቀት በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ይገኛል። የፓርኩ ስፋት  ወደ 2200ኪ.ሜ የሚደርስ ሲሆን ከሰሜን ወደ ደቡብ 74 ኪ.ሜ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ደግሞ 53 ኪ.ሜትር ይሰፋል። ፓርኩ ከባህር ወለል በላይ ከ1450 እስከ 4377 ጫማ ባለ ልዩነት ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎችን የሚያካትት ሲሆን 4377 ጫማ የሚረዝመው እና ከኢትዮጵያ በከፍታው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የቱሉ ዲምቱ ተራራም በዚህ ፓርክ ውስጥ ይገኛል። ብሄራዊ ፓርኩ በተለያዩ መንገድ የተፈጠሩ ሀይቆች፤ እርጥበት አዘል መሬቶች እና የእሳተጎሞራ ቅሪቶችን አቅፎ ይዟል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የብዝኃ ሕይወት ተመራማሪ አቶ ላቀው ብርሃኑ “የባሌ ብሄራዊ ፓርክ በ “Bird Lite International” በዓለም ከሚገኙ አስፈላጊ የአዕዋፍ መኖሪያ ቦታዎች ጎራ ተመድቧል። በተጨማሪም ለብዙ የዱር እንስሳትም መጠለያ መሆኑ ይታወቃል። በባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ዋቢ ሸበሌ፣ ዌብ፣ ዱማል፣ ያዶትና ወልመል የተሰኙ ወንዞች ይፈሳሉ። ይህን ሁሉ ሀብት የያዘውን ቅርስ በዩኔስኮ ማስመዝገቡ ቅርሱ ተጠብቆ እንዲቆይ ከማድረግ አኳያ እና ለሀገሪቱም አሁን ካላት የተፈጥሮ ሀብት መስህብ በላይ በተጨማሪ መስህብነት ስለሚጠቅማት ጥረቱ ከግብ ሊደርስ ይገባል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአስደናቂ መልክዓ ምድሩ የሚታወቀው ይህ ብሔራዊ ፓርክ ከፍ ያሉት ተራሮቹ ፣ ለጥ ብለው የሚታዩት ሸለቆዎቹ እና የጎብኚዎቹ ብዛት ልዩ ልዩ መገለጫዎቹ ናቸው። በተጨማሪም የባሌ ተራሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታወቁት 1000 የመድኃኒት ዕፅዋት ዝርያዎች 40%ቱን የሚይዝ ሲሆን ከፍተኛ በሆነው የቡና ክምችቱም ይታወቃል።

ፓርኩን ልዩ የሚያደርገው ሌላው ነገር በኢትዮጵያ ትልቁና ወደ ሰባት ሺሕ ኪሎ ሜትር ስኩዬር የሚሸፍነው ‹‹የሐረና ደን›› በውስጡ በመገኘቱ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከ1600 በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ ዓይነት ዕፅዋቶች፣ 78 ዓይነት አጥቢ የዱር እንስሳትና ወደ 200 የሚጠጉ አእዋፋት በፓርኩ ተጠልለው ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል 32 ዓይነት ዕፅዋቶች እና 17 የሚጠጉት ብርቅዬ የዱር እንስሳት በዚሁ ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኙ ናቸው።

አስተያየት