የመውሊድ ብርሃን

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታጥቅምት 5 ፣ 2014
City: Addis Ababaባህል
የመውሊድ ብርሃን

"መውሊድ" የሚለው ቃል የተቀዳው ከአረብኛ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም “የመወለጃ ቦታ ወይም የመወለጃ እለት” የሚል ነው። በመንፈሳዊ ትርጉሙ ደግሞ ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተወለዱበትን እለት ለማሰብ ለሚደረግ ክብረ-በዓል የተሰጠ ስያሜ ነው።

የፎክሎር ባለሙያው መሐመድ ዓሊ (ዶ/ር) መውሊድን የሚያከብሩ አማኞች ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለተወለዱበት ወር የተለየ ክብር እንዳላቸው እና ረቢእ ብለው እንደሚጠሩትም ይናገራሉ።  “ይህ ወር የዓለሙ መሪ ነቢዩ የተወለዱበት፣ ከፈጣሪ ወህይ መቀበል የጀመሩበት፣ ተልዕኳቸውን አድርሰው፣ ለሕዝባቸው አደራ ሰጥተው ያለፉበት ነው” ሲሉም ያብራራሉ። 

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የመውሊድ በአል አከባበርና ጅማሬውን በተመለከተ የተለያየ አመለካከት አለ። እንደምሳሌ ሲጠቅሱም መውሊድ መከበር የጀመረው በራሳቸው በነቢዩ መሐመድ ሲሆን ሊከበርም የሚገባው ነቢዩ የተወለዱበትን ቀን በመጾም ነው የሚል ወገን ያለ ሲሆን መውሊድ መከበር የጀመረው ነቢዩ ከዚህ አለም ከተለዩ በኋላ በአስራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተጀመረ፣ አከባበሩም መካ ወደሚገኘው ነቢዩ ወደተወለዱበት ቤት ዚያራ/መንፈሳዊ ጉብኝት በማድረግ ነው የሚል ወገንም አለ።

በሌላ በኩል በዓሉ ሺኣ ፋጢምዮች በሚያስተዳድሯት ግብጽ እንደተጀመረ፣ አከባበሩም ከነቢዩ ሙሐመድ ልደት በተጨማሪ ከሺኣ ወልዮችና ከግዛቱ ኻሊፋዎች ወይም መሪዎች ልደት ማክበር ጋር የተያያዘ ነው የሚል አመለካከት ያለ ሲሆን መውሊድ በሱኒ ሙስሊሞች ዘንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ ህዝባዊ በዓል ሆኖ መከበር የጀመረው በአስራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ በኢራቅ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኝ ኤርቤል በምትባል ከተማ ነው የሚል እምነትም አለ ይላሉ ዶክተር መሀመድ።

“በኢትዮጵያ መውሊድን ማክበር በአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ እንደተጀመረ እና ከሱፊዝም መስፋፋት ጋር እንዳደገ ይታመናል። ሱፊዎች መውሊድን የአምልኮ ተግባሮቻቸውና የመንፈሳዊ ንቃታቸው ማበልጸጊያ የአንድነታቸው ማጠናከሪያ መሳሪያ አድርገው ይገለገሉበታል” የሚሉን ደግሞ በታሪክ ዙሪያ በሚጽፏቸው መፅሀፍት የሚታወቁት እና የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ተሾመ ብርሃኑ ናቸው። 

በአገራችን የመውሊድ በአል ከአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ አንስቶ ህዝባዊ ክብረ በአል ሆኖ ቢቀጥልም እስከ ደርግ ዘመን ድረስ የአገሪቱ ይፋዊ ክብረ በአል እንዳልነበረ እና ከ1967 ዓ.ም. ወዲህ ግን፣ በህዝበ ሙስሊሙ የቀደመና ተከታታይ ጥያቄ የአገሪቱ ይፋዊ በአል ሆኖ፣ በረቢ አል አወል አስራ ሁለተኛው ቀን መከበር መጀመሩንም ያብራራሉ።

የመውሊድ በዓል በበርካታ ድርጊቶች ይደምቃል። ከእነዚህም መካከል የሰደቃ ወይም የምጽዋት፣ የጀባታ፣ የተመረጡ የቁርአን ክፍሎችና የመውሊድ ምንባብ፣ የመንዙማ ፕሮግራሞች እንደሚገኙ በዓሉን የሚያከብሩት አማኒያን ይናገራሉ። 

“በሰደቃው ባለፀጎችና ባለ ስለቶች በሬ ወይም በግ፣ ፍየል ወይም ዶሮ አርደው ለድሆች ያበላሉ፤ ያጠጣሉ” ትላለች ኢክራም ሰዒድ የተባለች ወጣት “በዱዓው ክፍለ ጊዜ ደግሞ ጀባታ ወይም ስጦታ እየተሰጠ የታመመው እንዲሽር፣ የደኸየው እንዲከብር፣ የተበደለው እንዲካስ፣ አገር ሰላም እንዲሆን፣  ወዘተ ይመረቃል” ስትል ታስረዳለች።

አያይዛም በቁርአንና በመውሊድ ንባብ ክፍለ ጊዜ ከነቢዩ ሙሐመድ ጋር የተያያዙ የቅዱስ ቁርአን ክፍሎች እንደሚቀሩና ስለ ነቢዩ ውልደት፣ በህይወት በነበሩ ጊዜ ስለ ፈጸሟቸው ገድሎችና ተአምራት፣ ስለ ባህሪያቸው፣ ወዘተ የሚገልጹ የመውሊድ ኪታቦች እንደሚነበቡ ትናገራለች።

እስልምና እና በዓላቱ ሲታወሱ አንደኛው የኢትዮጵያ ኢስላማዊ ቀለም የሆነውን መንዙማን አለማንሳት አይቻልም። “መንዙማ ምስጋና (ማወደስ) ማለት ነው። መንዙማ በይዘቱ በዋነኛነት ከሃይማኖታዊ ዝማሬዎች ይመደብ እንጂ በውስጡ የተለያዩ ማኅበራዊና ፖለቲካ መልዕክቶችንም ያቀፈ ነው። ሃይማኖታዊ ይዘቱም አላህ የሚመሰገንበት፣ ነቢዩ መሐመድ የሚሞገሱበት፣ የእስልምና ትምህርት የሚሰጥበት፣ ታላላቅ ሰዎች (አውሊያዎች) እና መላዕክት የሚወደሱበት፣ ገድላቸውና ተአምራቸው የሚነገርበት፣ ችግር (ድርቅ፣ ረሃብና በሽታ) የመሳሰሉት ሲያጋጥሙ የተማፅኖ ጸሎት የሚደረግበት ነው” ይላል በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የተዘጋጀ የጥናት መድበል።

ሆኖም መውሊድም በመንዙማ በተለያየ መልኩ ይገለፃል። “የመውሊድ መንዙማ ክዋኔ እንደ መውሊዱ ቦታና እንደተሳታፊው ባህሪ ልዩነት አለው። መውሊዱ በቤት ውስጥ ሲከናወን ወንዶችና ሴቶች ተቀላቅለው ወይም በመጋረጃ ተከፍለው የመንዙማ ከበራው ይካሄዳል” ይላሉ ዶክተር መሀመድ ዓሊ።

“መውሊዱ በመስጊድ ውስጥ ሲሆን ወንዶችና ሴቶች በመጋረጃ ተለይተው ወይም ወንዱም ሴቱም ለብቻ ቡድን ፈጥረው መንዙማው ይካሄዳል። የመውሊዱ ከበራ በሱፊ ማእከሎች ሲሆን ደግሞ ከሰው ብዛትና አይነት የተነሳ በርካታ የወንዶች፣ የሴቶች፣ የወንዶችና የሴቶች ቡድኖች ተፈጥረው ሁሉም በያሉበት መንዙማውን ከበራ ያካሂዳሉ” ሲሉም ያስረዳሉ።

ሙስሊሞች በበዓሉ ነቢዩ መሀመድን በመንዙማ እንዲህ ሲሉ ያወዱሷቸዋል፦

  1. “ረቢእ ተብለህ የምትጠራ፤

            የወራት ጓል ንጉስ አውራ፣

            ነቢ ባለ ሙሉ ሰብእና፣

             እውድጥህ ፈለቁና፣

           ሀሴት አዝለህ አስደሰትከን ተስፋ ወልደህ አደመቅከን፣

           ቃል አደራህ ለኛ ከብዷል፣ ውለታህ ክፋይን ገዷል”

       2. “የመድናውን ባየነው አይኑን

            በኑር አረንጓዴ የተኳለውን

            ፊቱ ከጨረቃ የሚያበራውን

            ፀጉሩ የሚመስለው የሀር ጉንጉን

           ብሎ ያወደሰው ጦሀው ያስኔ”

በዓላት ከሀይማኖታዊ ዳራቸው ባለፈ ለማህበራዊ ህይወትም ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ማድረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ አኳያ የመውሊድስ ፋይዳ ምን ይመስላል ስትል አዲስ ዘይቤ ለዶክተር መሀመድ ዓሊ ጥያቄ አቀረበች፣

ሲመልሱም “የመውሊድ መንፈሳዊ ፋይዳው ሲታይ በሀገራችን ህዝበ ሙስሊሙን በማሰባሰብ እምነቱን እንዲያውቅና አንድነቱን እንዲያጠናክር ረድቶታል፣ ከማህበራዊ ፋይዳው አኳያ ደግሞ ሰደቃ ይካሄድበታል፤ በዚህም ሀብታምና ድሃ ይገናኙበታል፣ ያለው ለሌለው ምጽዋእት ይሰጥበታል ከዚህም በተጨማሪ የማህበራዊ ግንኙነትና ትስስር ይጠናከርበታል” ብለዋል።

አያይዘውም የመውሊድ በዓል ባህላዊ ፋይዳ እንዳለው በመግለጽ በመውሊድ ላይ የሚቀርቡ ልዩ ልዩ መንዙማዎች የጥበብ ፈጠራዎች ሲሆኑ እንዲህ አይነቱ ፈጠራ ሲበለጽግ ደግሞ ባህሎች እንዲያድጉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ይላሉ። በሌላ በኩል መንዙማዎቹ በዜማና በአጀብ የሚፈጸሙ በመሆናቸው የተዝናኖትና የፍስሀ አገልግሎት ይገኝበታል ይላሉ።

አክለውም መውሊድ የአከባበር ባህሉ እንዳይጠፋ ተደርጎ ከተያዘ ወደ ሃላል ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ማደግ እንደሚችል እና በዚህም አገርንና የአካባቢውን ህብረተሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ወደሚሆኑበት ደረጃ ማሸጋገር እንደሚቻል ይናገራሉ።

የእምነቱ ተከታዮች የመውሊድ በዓልን በየቤታቸው ከማክበር ባለፈ በልዩ ሥነ በዓል የሚያከብሩባቸው ቦታዎች አሉ። ከነዚህ ልዩ ቦታዎች መካከል የጡርሲና መስጊድ ተጠቃሽ ነው። መስጊዱ በወሎ ዞን ርዕሰ ከተማ ከከሚሴ 16 ኪሎ ሜትር ርቃ በከሚሴና በወልዲያ ከተሞች መካከል በምትገኘው ሸከላ ተብላ በምትጠራ ትንሽ የገጠር ከተማ ይገኛል።

ዶ/ር መሀመድ አሊ እንደገለፁልን የጡርሲና መስጊድ መሥራች ሼክ መሐመድ አማን ተብለው የሚጠሩ ታላቅ ሰው ሲሆኑ መስጊዱ የተሠራው በሳርና በእንጨት ነው። ስፋቱ ደግሞ 625 ሜትር ነው። መስጊዱ ከትልቅነቱ የተነሳ በትልልቅ ምስሶዎች የተደገፈ ነው። በ85 የውጭ ምሰሶዎች እና በ41 የውስጥ ምሰሶዎች በተሰራው በዚህ መስጊድ ውስጥ ለኅብረተሰቡ የሚቀርበው ቡና የሚዘጋጅበት ክፍል ውስጥ ርዝመቱ ሁለት ሜትር የሚሆን ረከቦት እና ከ190 የሚበልጡ ሲኒዎች ያሉ ሲሆን ጀበናዎቹ ደግሞ የእንስራ መጠን ያላቸው ከብረትና ከሸክላ የተሠሩ ናቸው። የቡና ሙቀጫዎችም በተለምዶ ለእህል መውቀጫነት የሚያገለግለው ሙቀጫ መጠን ያላቸው ናቸው። ለቡና ቁርስ የሚሆነው ንፍሮ ሚቀቀለው በበርሜል መሆኑንም ነግረውናል። 

ሌላው የሥጋ ቤቱ ክፍል ሲሆን የዚህ ክፍል ዋነኛ ተግባር የዕርድ ከብቶች ከታረዱ በኋላ ሥጋው የሚቀመጥበትና ተዘጋጅቶ ለመስጊዱ የሚደርስበት ቦታ ነው። በመውሊድ ጊዜ እስከ 27 ከብት ይታረዳል። ማር እየተበጠበጠ የሚዘጋጅበትና ለመስጂዱ ኅብረተሰብ የሚከፋፈልበት ክፍል ደግሞ ማር ቤት ይባላል። በዚህ ታላቅ ጡርሲና መስጂድ በየዓመቱ የመውሊድ በዓል ከዓመት ዓመት በተለየ ድምቀት ይከበራል አማኞችም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በዓሉን ለማክበር ወደ መስጊዱ ይተማሉ።

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1496ኛው የመውሊድ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ።

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist works at Addis Zeybe as a reporter while exploring her passion for storytelling and content creation.