“አንድ ቀን ወደ ከዚራ በመጓዝ ላይ ነበርኩ። ግሪክ ቤተክርስቲያንን እንዳለፍኩ ሼኽ ኢብራሂም ቢሊሳ የሚባሉ የሀይማኖት አባት ቤት አካባቢ ስደርስ ሁለት ዘናጭ ሴቶች ተመለከትኩ። ያየኋቸው ቆነጃጅት ትራንስፖርት እየጠበቁ ነበር። ትኩረቴን የሳቡት በቁንጅናቸው እና በአለባበሳቸው ብቻ አልነበረም የሚሄዱበትን ትራንስፖርት በመምረጣቸውም ነው። ከንግድ ባንክ ወደ ግሪክ ቤተክርስቲያን አቅጣጫ አንድ ፔጆ መጣች። በወቅቱ ሰዎችን የሚያጓጉዙ የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ፔጆ፣ ሬኖ፣ ዳትሰን የሚባሉ ናቸው። መንገደኞቹን ሴቶች ለማሳፈር አንድ ፔጆ መጣች። ሴቶቹ ግን ለመሳፈር ፈቃደኛ አልነበሩም። አንደኛዋ ልጅ መኪናዋን ተመልክታ “በዚህችማ አንሄድም! ከርካሳ ነች። ሌላዋ ስትመጣ እንሄዳለን” አለቻት። ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ ሌላ ፔጆ መጣች። ጥቂት ቆየት ብሎ ሌላ ፔጆ አጠገባቸው ቆመች። ሴቶቹ ግን አሁንም በአንሄድም አቋማቸው እንደጸኑ ናቸው። ሌላ ዳትሰንም ብትመጣ “ከርካሳ ነች አንሄድም” በሚል እምቢ አሉ። ይህንን ሳይ እነዚህ ልጆች ትንሽ ያረጀ መኪና የናቁ ጋሪንማ እንዴት ሊያደርጉት ነው ብዬ…
ቀጠሮ ነበረኝ ከፍቅርዬ ጋራ
ማነው ያዘገያት የኔ ባላጋራ
ወደኔ ስትመጣ የዘወትር መንገዷ
አይደለም በሌላ በጋሪ ነው ልምዷ
ጋሼ ባለጋሪ በጣም ብዙ ብረር
ፍቅርዬን ይዘሀት በከዚራው ጥላ ስር
በከዚራው ጥላ ስር
ባለጋሪው ባለጋሪው
ቶሎ ቶሎ ንዳው
የሚል ዘፈን አዘጋጀሁ። የዘፈኑ ዐላማ ቆንጆዬ ልጅ በጋሪ ልትሄድ እንደምትችል ለማሳየት ነው።”
ከ36 ዓመታት በፊት የተዘፈነው “ባለጋሪው” የተሰኘው ሙዚቃ እንዴት እንደተፃፈና እንደተዘፈነ ድምፃዊ አበራ ሙላቱ ያብራራል። በወቅቱ ድሬደዋ ከተማ ውስጥ በብዛት ለትራንስፖርት አገልግሎት ይውል የነበረው የፈረስ ጋሪ ነበር።
ድሬደዋ ካፈራቻቸው ድምጻውያን መካከል አንዱ የሆነው አበራ ሙላቱ ድምጻዊ ብቻ አይለም። የታሪክ ጸሐፊ፣ መምህር፣ ጋዜጠኛም ጭምር እንጂ፤ በ1976 ዓ.ም. ለአድማጭ ባደረሰው “ባለጋሪው” የተሰኘ ሙዚቃው በስፋት ይታወቃል።
“ባለጋሪው” መጀመሪያ የተሰራው በድምፅ ብቻ ነበር። ዘፈኑ ተወዳጅነትን በማትረፉ በክራር ታጅቦ ተቀረጸ። ብቸኛው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድሬዳዋ ተጉዞ ቃለ-መጠይቅ አድርጎለታል። ለቃለ-መጠይቁ ማጀቢያ ይሆን ዘንድም “ባለጋሪው”ን ታምራት አበበ ከተባለ ጓደኛው ጋር በክራር አጅበው ተጫውተውታል። ለገሀሬ እና ግሪክ ቤተክርስቲያን ፊትለፊት የተቀረጸው ቪድዮ የተወዳጁ ዘፈን ዝና እንዲናኝ አድርጓል።
ባለጋሪው የተሰኘው ዘፈን በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኘ አሁንም በሰው ልብ ውስጥ ተቀርፆ የቀረ ዘፈን እንደሆነ የድሬደዋ ህዝብ ምስክር ነው። ባለጋሪውን ያልተጫወተ ድምጻዊ የለም ማለት ያስደፍራል። አንጋፋዎቹ እስከ ጀማሪዎቹ ተጫውተውታል። አስቴር አወቀ፣ ታደለ ሮባ እና ብርሃኑ ተዘራ (ላፎንቴን) ከመካከላቸው ይጠቀሳሉ። “በማንም ድምጻዊ ፈቃድ ተጠይቄ አላውቅም” የሚለው ድምጻዊ አበራ ከግጥም እና ዜማ ድርሰቱ በተጨማሪ ሌሎች የኪነ-ጥበብ እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፋቸውን አጫውተውኛል።
ድምፃዊ አበራ ሙላቱ ከ1976 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ዓመታት ስምንት የቲያትር ድርሰቶችን ጽፈዋል። በትወናም ተሳታፊ ነበሩ። ከድርሰቶታቸው መካከል “ካቺሳው”፣ “ደባልቄ”፣ “ትኬት ይቁረጡ”፣ “ዝግጅት”፣ “ሰነፉ ጫማ ሰፊ” የተሰኙት ይጠቀሳሉ። የቪድዮ ፊልም በተስፋፋባቸው ጊዜያቶችም ድምጻዊ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ፣ ተዋናይ፣ የቲያትር እና ፊልም ድርሰቶች ጸሐፊ የሆነው አበራ ሙላቱ አስተዋጽኦ አበርክቷል። “አይነጋ መስሏት” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ጽሑፉ በወቅቱ ተወዳጅ ከነበሩ ሥራዎቹ ውስጥ ይመደባል። በአምስት ተከታታይ ክፍሎች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀረበውን ድራማ መላኩ ከበደ፣ ሰብለ ጋሻው፣ አፈወርቅ አበራ በትወና ተሳትፈውበታል። ድራማው የተቀረጸው ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ እንደነበር የተመለከቱት ሰዎች ያስታውሳሉ።
የድሬ ልጅ ማለት ወርቅ ቀለበት ነው
ሹልክ ያለ እንደሆን ከጣት ላይ ፈላጊው ብዙ ነው
ድንገት ሌላ አግኝቶሽ እኔም መና እንዳልቀር
ገሪኝ አንቺ ልጅ ሸዋ ነሽ ወይ ሀረር
የሚሉ ስንኞች የያዘው የወቅቱ ተወዳጅ ዘፈንም ከአበራ ሙላቱ ዘመን ተሻጋሪ ተወዳጅ ሥራዎች መካከል ይገኛል። ዘፈኑ በአብዛኛው የድሬደዋ ነዋሪ ዘንድ የሚታወቀው “ሰዋ ሰዋ” በሚል መጠርያ ነው።
የተሰራው በ1973 ዓ.ም. ሲሆን በግጥሞቹ ይዘት የድሬዳዋን ልጅ ያወድሳል። ግጥሙን የጻፉት አፈወርቅ አበራ እና የባለጋሪው ዘፋኝ አበራ ሙላቱ በጋራ ነው። ተዋናይ አፈወርቅ አበራ በአበራ ሙላቱ ክራር ታጅቦ አቀንቅኖታል። ሁለቱ የድሬዳዋ ፈርጦች ሙዚቃን የጀመሩት በልጅነታቸው ነው። የሰፈር ውስጥ “ኦርኬስትራ” አቋቁመው የሙዚቃ ጥማታቸውን ይወጡ እንደነበር አቶ አበራ ይናገራል። “የፈጠራ ስራዬን አሁንም አላቋረጥኩም” የሚለው አቶ አበራ ከ100 በላይ የዜማ ሥራዎች በእጁ እንደሚገኙ አጫውቶናል።
ድምጻዊ አበራ “ቡትጂ” የተሰኘ ጋዜጣ ነበረው። በ2012 ዓ.ም. ለንባብ ይበቃ የነበረው ጋዜጣው ስያሜውን ያገኘው ድሬዳዋ ከተማ ከሚገኝ “ቡትጂ” የተሰኘ የተፈጥሮ መዋኛ ስፍራ ነው።
ጣልያን የሲሚንቶ ፋብሪካውን ሲያቋቁም ከዚህ የተፈጥሮ ኩሬ ሁለት ሜትር ራቅ ብሎ ነበር። ለውሀ ግብአት ለመጠቀም ብሎ የገነባው። “ለፋብሪካ ግብአት ታስቦ የተገደበው ውሀ በወቅቱ ለነበሩ የድሬደዋ ታዳጊዎች የመዋኛ ስፍራ ሆኖ አገልግሏል። ከሁሉም አቅጣጫ የድሬደዋ ልጅ ነኝ የሚል ሁሉ በቡትጂ ያልዋኘ የለም” የሚለው አቶ አበራ የጋዜጣውን ስያሜ “ቡትጂ” የሚል ስያሜ የሰጠው ልጅነቱን ለማስታወስ ነበር።
“በልጅነቴ ቡትጂ እንዳንሄድ እንከለከል ነበር የቡትጂ ውሀ ህፃናትን ይወስዳል ሰይጣን አለበት ተብሎ ስለሚታሰብ አብዛኛው ወላጅ ልጁ ቡትጂ ውሎ ማታ ሲመጣ ይገረፍ ነበር። ለመዋሸትም አይመችም ነበር ብዙ ሰአት ስለምንዋኝ ነጭ እንሆናለን ከዚያ መገረፍ ነው። ከዛ አንድ ጊዜ የማልረሳው ዱላው ሲሰለቸኝ ከጓደኞቼ ጋር ተማከርንና ዘይት ከቤት ይዘን ሄደን ልክ ስንጨርስ ዘይቱን ሙሉ ሰውነታችንን ተቀብተነው ወደቤት ተመለስን። ለካ ሳናስበው ዘይቱን በጣም አብዝተነው ነበርና ከዱላ አላመለጥንም” ሲል አበራ የቡትጂ ትዝታውን በዚህ መልኩ ይናገራል።
ጋዜጣውንም ቡትጂ የሚል ስያሜ የሰጠው ይህንንና መሰል የተለያዩ ትዝታዎችን ስለሚያስታውሰውና የድሬደዋ ልጅ ሆኖ በወቅቱ ይህን የመሰለ ትዝታዎች የማያሳልፍ ስለማይኖች ጋዜጣው ደግሞ ትኩረቱን የሚያደርገው ድሬደዋ ላይ በመሆኑ እንደሆነም ገልፀዋል። ቡትጂ የተሰኘው ጋዜጣን ገዛኸኝ እና ጆኒ ከሚባሉ ወዳጆቹ ጋር አብሮ ያዘጋጅ እንደነበር አበራ ሙላቱ ገልፆአል። ጥሩ ይዘት እንደነበረው እና በሕብረተሰቡም ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ እንደነበር የሚገልፀው ድምፃዊ አበራ አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ጋዜጣው እንደታገደበት ይገልፃል።
ድምፃዊ አበራ ሙላቱ የስድስትና ሰባተኛ ክፍል መምህር በመሆን ለአምስት ዓመት በከዚራና አባዮሀንስ ት/ቤት ውስጥ አገልግለዋል። በአሁን ሰዓት ገንደቆሬ የተባለ የመኖርያ መንደር ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እየኖሩ የሚገኙ ሲሆን አሁንም ከጥበብ እንዳልራቁ ይናገራሉ። “በአሁን ሰዓት የድሬደዋን ኢንሳኪሎፕዲያ እያዘጋጀሁ እገኛለሁ። የድሬደዋን ሙሉ ታሪክ፣ የህዝቡን የአኗኗር ዘይቤ፣ የቋንቋ አጠቃቀምና በአጠቃላይ ድሬደዋ ያላትን የተለየ ነገር የሚያወጣ መጽሐፍ በማዘጋጀት ላይ እገኛለሁ። መጽሐፉ 85 በመቶ ያህሉ ተጠናቋል።” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።