የድሬደዋ ነዋሪዎችን ያማረረው የመንገድ ላይ ዝርፊያ

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራውጥቅምት 4 ፣ 2014
City: Dire Dawaማህበራዊ ጉዳዮች
የድሬደዋ ነዋሪዎችን ያማረረው የመንገድ ላይ ዝርፊያ

ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ያጋጠመው የጎርፍ አደጋ የተለያዩ የድሬዳዋ ከተማ መንደሮችን ጎድቷል። አሸዋ ውስጥ የሚገኘው መተላለፊያ መንገድ እና ድልድይ ከመካከላቸው አንዱ ነው። ጎርፉ መተላለፊያ ድልድዩን ሰብሮ መንገዶችን አበላሽቷል። የታክሲ መጫኛ እና ማውረጃ የነበረው ይህ ስፍራ የጥገና ሥራው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሲሰጥ የቆየው የከተማ ትራንስፖርት መናኸሪያ አገልግሎት ወደ “ነምበር ዋን” ተዛውሯል። ስፍራው ሰኢዶ፣ መስቀለኛ፣ ሼል፣ ገንደቆሬ ለሚጓጓዙ መንገደኞች መነሻ እና መድረሻ ሆኖ ያገለግላል። የታክሲ መጫኛ እና ማውረጃ ለውጡ እንደ ቀድሞው ምቹነት የሌለው፣ በመኖርያ መንደር አካባቢ በመሆኑ ነዋሪዎችን የሚረብሽ እንደሆነ የነምበር ዋን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ከሁሉም የሚከፋው ትልቁ ችግር ግን የንጥቂያ ወንጀሎች እጅግ መበራከታቸው ነው።

አቶ ሙሉጌታ ተስፋዬ በድሬዳዋ ከተማ የነምበር ዋን አካባቢ ነዋሪ ናቸው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጎዳና ላይ ንጥቂያዎች በከተማዋ እየተስፋፉ እንደሆነ ማስተዋላቸውን ይናገራሉ። የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትና ታዳጊዎች ቁጥር መጨመር ከንጥቂያ ወንጀሉ መስፋፋት ጋር ግንኙነት እንዳለው ያምናሉ። ወደ መኖርያ ሰፈራቸው ለመጓዝ በተለይ አመሻሹ ላይ መጨናነቅ መፈጠሩ ለንጥቂያው የሚመች አስተዋጽኦ ስለማበርከቱ ነግረውናል። የእጅ ስልክ፣ የገንዘብ ቦርሳ፣ ጌጣጌጥ እና ሌሎችንም ከመንገደኛው መንትፈው በሩጫ የሚሰወሩ ወንጀለኞችን መመልከት ዕለታዊ ገጠመኝ እየሆነ ነው። እንደ አቶ ተስፋዬ ግምት “ሁሉም ናቸው ባይባልም የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናት እና ታዳጊዎች የንጥቂያው ወንጀል ዋነኛ ተዋንያን ናቸው” አቶ ተስፋዬ እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሱት በአካባቢው በሚመላለሱበት ጊዜ በተደጋጋሚ ካስተዋሉት ተደጋጋሚ እውነታ በመነሳት ነው።

“ነገሮች ቀድሞ ከነበሩበት አካሄድ ሲቀየሩ ለውጦች መከሰታቸው ተጠባቂ ቢሆንም አሉታዊ ጎናቸው እጅግ ያመዘነ ሲሆን ቅሬታ ያስነሳሉ” የሚለው ሌላ የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሳሙኤል ከበደ ነው። እንደ አቶ ሳሙኤል ሐሳብ አዲሱ የትራንስፖርት መጫኛ እና ማውረጃ ቀድሞ የፈጠረው ችግር የ“ነምበር ዋን”  የመኖርያ አካባቢን ገጽታ ማበላሸት ነው።

“ነምበር ዋን የመኖሪያ ሰፈር ነው። በመንደሩ የሚያድጉ ብዙ ህፃናት አሉ። ትራንስፖርቱ ወደዚህ ከዞረ በኋላ የፅዳቱ ሁኔታ ተበላሽቷል። ከፍተኛ የሚረብሽ ድምፅ አለ። ረብሻው በተለይ በምሽት ይባባሳል። የከተማ መናኸሪያው አሁን ወደሚገኝበት ነምበር ዋን ከመዘዋወሩ ነፊት ይህ ችግር አልተስተዋለም። ቀድሞ የነበረበት ስፍራ አሸዋ ነው። አሸዋ ሰፋ ያለና የንግድ ቦታም ነው። ነምበር ዋን ላይ ያጋጠመው ዐይነት ችግር አይገጥመውም። ትራንስፖርቱ ወደ ነምበር ዋን መዛወሩ ስህተት ነው” ብሎናል።

የነምበር ዋን ነዋሪ የሆነው ሌላኛው አስተያየት ሰጪአችን አቶ የሱፍ ሥዩም ነው። የቀደሙ አስተያየት ሰጪአችንን የአቶ ሳሙኤልን ሐሳብ የሚጋራው አቶ የሱፍ ጀጎል አካባቢ የምትገኘው ጠበብ ያለች ጨለምተኛ መተላለፊያ የንጥቂያ ወንጀሉ በብዛት የሚታይባት ስለመሆኗ ይናገራሉ። መኖሪያቸውን ጎዳና ያደረጉት ሕጻናት እና ታዳጊዎችም የወንጀሉ ተሳታፊ ስለመሆናቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

“አብዛኛዎቹ የጎዳና ልጆች እለታዊ ችግራቸውንና ረሃባቸውን ለማስታገስ አደገኛ ሱሶች ውስጥ ይደበቃሉ። ድርጊታቸው ጤናቸውን ጎድቶ ብቻ አያበቃም። የተለያዩ ወንጀሎችን እንዲፈፅሙ ያደፋፍራቸዋል።” ይህንን ያለችው ሳያት መስፍን ናት። እንደ ሳያት ገለፃ በአካባቢዋ ቁጥራቸው የበዛ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ተመልክታለች። ታዳጊዎቹ ማስቲሽ ከዕጃቸው እንደማይለይም ተመልክታለች። በሌሎች እጾች ደንዝዘው እርስ በእርስ እና ከሌሎች የአካባቢው ሰዎች ጋር ሲጋጩም አስተውላለች። 

የድሬደዋ አስተዳደር ሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ኤጀንሲ ስራ አስካሂያጅ አቶ ሸርማርኬ መሀመድ በከተማው በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ አንድ ሺህ አንድ መቶ ሰባ አራት ዜጎች በጎዳና ህይወታቸውን እየመሩ መሆናቸውን የሚጠቁም ጥናት እንደወጣ ነግረውናል።  ከእነዚህ ዜጎች መካከል ሦስት መቶ አምሳ ሁለት የሚሆኑት በልጅነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎችን ለማንሳት በተደረገው ጥረት በ2013 ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ  ሦስት መቶ ሰባቱ ከጎዳና ተነስተው ወደ ድጋፍ ማዕከል መግባታቸውን እና በቀጣይ በሌላ እድሜ ክልል ያሉ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑትን ለማንሳት ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል። እነዚህን ህፃናት አንስቶ የሁለት ዓመት ፕሮጀክት በመንደፍ ከመንግሥት ጋር በመሆን ልጆቹን በማዕከል በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ፖዘቲቭ አክሽን ፎር ዴቨሎፕመንት (PAD) የተባለው ሀገር በቀል ግብረ-ሰናይ ድርጅት ነው። የድርጅቱ  ዋና ዳይሬክተር አቶ ግርማ አድማሱ በበኩላቸው ልጆቹ በተለያዩ ሱሶች ውስጥ የቆዩ በመሆናቸው በአሁኑ ሰዓት ከሱስ እንዲያገግሙ እና በባህሪ እንዲቀየሩ የሚያስችል ድጋፍ እንደተሰጣቸው ገልፀዋል።

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የቀበሌ 03 መስተዳድርን እና የአካባቢውን ፖሊስ ሐሳቦች ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

Author: undefined undefined
ጦማሪዝናሽ ሽፈራው

Zinash is Addis Zeybe's correspondent in Dire Dawa.