በማላዊ ሰሜናዊ ክፍል የ25 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አስክሬን የያዘ የጅምላ መቃብር ማግኘቱን የሃገሪቱ ፖሊስ ገለፀ። ከማላዊ ዋና ከተማ ሊሎንግዌ 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ከተማ የተገኘው የጅምላ መቃብር በአካባቢው ነዋሪዎች የተገኘ ሲሆን የሀገሪቱ ፖሊስ የማጣራት ስራ መስራቱን አስታውቋል።
በአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ መሰረት የተገኙት አስክሬኖች 25 ሲሆኑ በአንፃሩ የማላዊ የዜና አውታሮች የሟቾቹ ቁጥር 26 እና ከዚያ በላይ እንደሚሆን ዘግበዋል። በተጨማሪም ከአስክሬኖቹ ከኢትዮጵያውኑ በተጨማሪ የሶማሊያ ዜጎችም እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
በትላንትናው እለት ለመገናኛ ብዙኀን መረጃ የሰጠው የማላዊ ፖሊስ “መቃብሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ማከሰኞ እለት የጠቆሙ ሲሆን ቦታዉን በመቆፈር እስካሁን 25 አስክሬኖች ማግኘት ተችሏል” ብሏል። እንደፖሊስ መረጃ ከሆነ የተገኙት አስክሬኖች በማላዊ አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ እየተጓዙ የነበሩ ህገ ወጥ ስደተኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል።
በተጨማሪም በአካባቢው ላይ ከተሰበሰበው መረጃ መረዳት የተቻለው አስክሬኖቹ የኢትዮጵያውን ዜግነት ያላቸው ወንዶች ሲሆኑ እድሜያቸውም ከ25 እስከ 40 የሚሆኑ ናቸው ተብሏል። የማላዊ ፖሊስ እንዳስታወቀው ሰዎቹ የተቀበሩበት ጊዜ ከአንድ ወር አያልፍም ካለ በኋላ የአስክሬን ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
ባለፉት 9 ወራት ብቻ የማላዊ መንግስት 221 በህገ ወጥ መንገድ የሚሰደዱ ሰዎችን በሀገሪቱ ክልል ውስጥ መያዙን ገልፆ 186ቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንም አረጋግጧል። ማላዊ እና ሞዛምቢክ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚደረጉ ህገ ወጥ የስደተኞች ዝውውር ዋነኛ መተላለፊያ መስመር መሆናቸው በተደጋጋሚ መታየቱንም የማላዊ መንግስት ገልጿል።
ከሁለት ዓመታት በፊት በማላዊ ጎረቤት ሀገር ሞዛምቢክ ውስጥ በአንድ እቃ ጫኝ ተሽከርካሪ ውስጥ 64 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ህይወታቸው አልፎ መገኘቱ ይታወሳል።