የአዋሽ መልካሳ የኬሚካል ፋብሪካ 2014 ዓ.ም በኪሳራ ማጠናቁቁን ለአዲስ ዘይቤ ገለፀ። ድርጅቱ በስሩ 318 ቋሚ፣ 7 የኮንትራት እንዲሁም 60 ጊዜያዊ ሰራተኞችን ያስተዳድራል።
"በ2014 ዓ.ም 237 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ለማስመዝገብ እና 33 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ አቅደን የነበረ ቢሆንም 5.3 ሚልዮን ብር ኪሳራ አጋጥሞናል" በማለት ለአዲስ ዘይቤ የተናገሩት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አድማሱ፣ ባሳለፍነው ዓመት ድርጅቱ በአብዛኛው ያለስራ ማሳለፉን ገልፀዋል።
ድርጅቱ የሰልፈሪክ አሲድ ምርትን ለማምረት የሰልፈር ግብዓትን ከውጭ እንደሚያስገባ የገለጹት ኃላፊው 2013 ዓ.ም ላይ ውጭ ሀገር ካለ አቅራቢ ጋር ውል ቢፈፅምም በተገቢው ሁኔታ ግብአቱ መቅረብ ባለመቻሉ ድርጅቱ ያሰበውን ስራ አለመስራቱ ለኪሳራው አንዱ ምክንያት መሆኑንም ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
ከ3 ሺህ እስከ 4 ሺህ ቶን ከሚሆነው የኢትዮጵያ የሰልፈሪክ አሲድ ምርት 85 በመቶውን የሚሸፍነው ድርጅቱ እስከ 2012 ዓ.ም ምርቱን ወደ ሱዳንም ይልክ እንደነበር ማወቅ ተችሏል።
ለውሃ ማጣሪያ የሚያገለግለውና የድርጅቱ ምርት የሆነው አልሙኒየም ሰልፌት በዋነኛነት ለማምረት በግባትነት የሚያገለግለው ሰልፈሪክ አሲድ ሲሆን ከላይ እንደተገለጸው የገጠመው የሰልፈር አቅርቦት እጥረት በአቅርቦቱ ላይ መስተጓጓል መፍጠሩን አቶ አድማሱ ገልጸዋል።
ከትናንት በስተያ ድርጅቱን የጎበኙት የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ታከለ ዑማ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ "ፋብሪካው ባለበት የግብአት ችግር ምክንያት ማምረት በሚችለው ልክ እያመረተ አይደለም" ሲሉ ገልፀው ነበር።
"በአሁን ወቅት 1000 ቶን የሰልፈር ጥሬ እቃ አግኝተን ምርት አስጀምረናል” ያሉት ኃላፊው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከተቀረፈ ያለመቆራረጥ የምርት ሂደቱን ለመቀጠል እንደሚችሉ ገልጸዋል።
የሚኒስትሩ ጉብኝት ዓላማን የጠየቅናቸው ስራ አስኪያጁ በዋናነት የኬሚካል ኢንደስትሪውን ከማዕድን ኢንደስትሪው ጋር ለማስተሳሰር ያለመ እንደሆነ ነግረውናል።
በመንግስት ደረጃ ሊሰሩ ከሚታሰቡ እንደማዳበሪያ፣ የብረታብረት እንዲሁም ሌሎች የኢንደስትሪ ውጤቶች ግብዓትነት የሚጠቅመው ሰልፈሪክ አሲድ በዓለምአቀፍ ደረጃም የኢንደስትሪያላይዜሽን ማሳያ ተደርጎም ይወሰዳል። በ1987ዓ.ም በአዳማ ሶደሬ መንገድ ከአዳማ 20 ኪሜ ርቀት ላይ የተመሠረተው ብቸኛው የአልሙኒየም ሰልፌት እና ሰልፈሪክ አሲድ አምራች ድርጅት በአሁን ወቅት ከሁለቱ ኬሚካሎች በተጨማሪ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ሀይድሮጅን ፐር ኦክሳይድ ኬሚካልን እያመረተ ይገኛል።