ጥቅምት 11 ፣ 2015

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አካባቢ በሴቶች ላይ የተበራከተው ዝርፊያ ስጋት ፈጥሯል

City: Hawassaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

የኢንዱትሪ ፓርኩ ሴት ሰራተኞች በተለይም ምሽትን ተገን አድርገው በሚፈፀሙ የዝርፊያ ወንጀሎች ስጋት ውስጥ የገቡ ሲሆን በእዚሁ ስጋት መኖሪያ አካባቢ እስከመቀየር የደረሱም አሉ። ፖሊስ በዝርፊያ ወንጅል ላይ ጥብቅ ስራ መጀመሩን አስታውቋል

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አካባቢ በሴቶች ላይ የተበራከተው ዝርፊያ ስጋት ፈጥሯል
Camera Icon

ፎቶ፡ ኢትዮጵያን ሞኒተር

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚሰሩ ሴቶች ከስራ መልስ ወደ መኖሪያ ቤታቸው በሚጓዙበት ወቅት በምሽት እና በቀን የዘረፋ ወንጀል እየተፈፀመባቸው እንደሚገኝ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በፓርኩ የሚሰሩት ሴቶች በአብዛኛዉ ለመስሪያ ቤቱ ቅርብ በሆነው በተለሞዶ ዳቶ ተብሎ በሚጠራበት አካባቢ ቤት ተከራይተው ይኖራሉ። ሰራተኞቹ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት ድርጊቱ በምሽት ጨለማ ተገን ተደርጎ የሚፈፀመና ሲብስም በቀን ሶስትና አራት በሆኑ ዘራፊዎች ወንጀሉ እየተፈጸመ መሆኑ “ለህይወታችን ያሰጋናል” ይላሉ።

የከተማዋ ፖሊስ መመሪያ በበኩሉ በከተማዋ በሚገኙ ስምንቱም ክፍለ ከተሞች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ ገልጾ የስርቆት ወንጀል ላይ የተሰማሩትን በመለየት ለህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አሳውቋል።

በቱላ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ዳቶ አካባቢ በየዕለቱ የስርቆት ወንጀል እንደሚፈፀም ለአዲስ ዘይቤ የሚናገሩት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ሲሆኑ ድርጊቱ መነሻው ከጥቁር ውሃ ወደ ሐዋሳ ከተማ መግቢያ አንስቶ እስከ መልካም ወጣት ማዕከል ግንባታ ድረስ ባለው አካባቢ መሆኑን ይገልጻሉ። 

“ሁለት ጊዜ በተመሳሳይ ቦታ ስልኬን በቀን ተወስዶብኛል። ሶስት ወጣቶች ናቸው የዘረፉኝ። አቅም ስለሌለኝ ዝም አልኩኝ። የሚያሳዝነው ደግሞ በቀን በ12 ሰዓት መሆኑ ነው” የምትለው ፈትያ አህመድ፤ የምትኖረዉ ዳቶ ቀበሌ ሲሆን የምትሰራዉ ደግሞ ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሆነ ትናገራለች ። 

ሌላኛዋ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ሰራተኛና መኖሪያዋን ዳቶ ያደረገችው ወጣት ውብሃረግ እንደምትለው ከስራ መውጫዋ 11:30 ቢሆንም መንገዱ ረዥም በመሆኑ አምሽታ ቤት ትደርሳለች።

“ወደ መንደር ውስጥ የሚያስገባው ቅያስ ጨለማ ስለሆነ ቦታው ያስፈራል። ምሽት 1 ሰዓት ገደማ ላይ ሁለት ወጣቶች አንደኛዉ በእጁ ስለት ነገር ይዟል ሌላኛዉ ደግሞ አስፈራርቶ ስልኬን ወሰደብኝ” ብላለች። ውብሃረግ በዚህ ምክንያት ለስራዋ ቅርብ ከነበረው አካባቢ ለቃ ራቅ ወዳለ ቦታ ለመኖር መገደዷም ትገልጻለች።

የአዲስ ዘይቤ የሐዋሳ ከተማ ሪፓርተር ያናገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት በየዕለቱ እየተሰማ ለሚገኘዉ የስርቆት ወንጀል እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት የመንገድ ዳር መብራት አለመኖሩን ነው።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ረዳት ኢንስፔክተር መልካሙ አየለ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት የፀጥታ እና የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የሚፈፀምባቸው ቦታዎች ተብለዉ ከተለዩ አካባቢዎች መካከል ዳቶ አንዱ መሆኑን በማንሳት ከስርቆት ወንጀል ጋር ተያይዞ በ2014 ዓ.ም ከ100 በላይ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ገልጸዋል ። 

ፎቶ: እያሱ ዘካሪያስ  

“66 ወጣቶች ሞተር ሳይክል በመጠቀም የስልክ እና የቦርሳ ንጥቂያ የፈፀሙ ተለይተው ለፍርድ ቀርበዋል” ሲሉ ረዳት ኢንስፔክተር መልካሙ ተናገረዋል።

የማህበረሰብን እንቅስቃሴ በመጠበቅ የሚሰሩ የስርቶት ወንጀሎች መኖሩን የሚናገሩት የከተማዋ ፓሊስ መመሪያ ኃላፊ “ይህን ለመቆጣጠር በመንደር ውስጥ የነበረውን የፖሊስ ማዕከል ወደ መንገድ ዳር እንዲወጣ ተደርጓል” ብለዋል።  

በአሁኑ ሰዓት 32 ሺህ ሰራተኞች ያሉት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከዚህ ውስጥ ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

አስተያየት