ጥር 14 ፣ 2014

የቡና ተረፈ ምርትን ጥቅም ላይ የሚያውለው ኢትዮጵያዊ ኩባንያ ለዓለም አቀፍ ዉድድር እጩ ሆነ

City: Addis Ababaየፈጠራ ዐውድወቅታዊ ጉዳዮች

ኮፊ ሪሰሬክት የተሰኘው በወጣት አልማው ሞላ የተመሰረተው ከቡና ምርት የሚወገድን ቆሻሻ እና የቡና ፍሬን በመጠቀም የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት የተቋቋመ የመጀመሪያ ኩባንያ ነው።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

የቡና ተረፈ ምርትን ጥቅም ላይ የሚያውለው ኢትዮጵያዊ ኩባንያ ለዓለም አቀፍ ዉድድር እጩ ሆነ

የ Coffee Resurrect, Inc. መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አልማው ሞላ ኢትዮጵያን በመወከል በ Global Startup Awards (በአለም አቀፍ የአዲስ ስራ መስራች) ውድድር ከምስራቅ አፍሪካ አሸናፊነት ወደ መላው አፍሪካ አሸናፊነት በሚደረገው ውድድር ለመጨረሻ ዙር እጩ ሆኗል።

ኮፊ ሪሰሬክት የተሰኘው በወጣት አልማው ሞላ የተመሰረተው ከቡና ምርት የሚወገድን ቆሻሻ እና የቡና ፍሬን በመጠቀም የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት የተቋቋመ የመጀመሪያ ኩባንያ ነው።

ኮፊ ሪሰሬክት በአሁኑ ወቅት ሀገር አቀፍና ቀጠናዊ ውድድሮችን በማሸነፍ በዓለም አቀፍ የአዲስ ስራ ምስረታ (Start UP) ዘርፍ ውድድር ብቁ መሆን ችሏል። ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረገው የኮፊ ሪሰሬክት መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አልማው ሞላ፤ የፈጠራ ስራ ዓላማው በአካባቢ ላይ የሚፈጠር ተጽእኖን መቀነስና የአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጿል።

በየዓመቱ ከቡና ምርት ሂደት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው ዉጋጅ ከ10 ሚልየን ተሽከርካሪዎች የጭስ ልቀት ጋር የሚቀራረብ መሆኑን የሚገልጸው ኮፊ ሪሰሬክት፤ ይህ ውጋጅ ሰዎችን፣ አካባቢን፣ አፈርን እና የውሃ ሀብት ላይ ጉዳት ማድረሱ የኮፊ ሪሰሬክት መመስረት አንዱ ምክንያት ነው።

ኮፊ ሪሰሬክት የቡናን ጠቀሜታ ከመጠጥነት ባለፈ ለዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ማዋል ይፈልጋል። የኩባንያው መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ እንደገለጸው “ኮፊ ሪሰሬክት በቀዳሚነት ትኩረት የሚሰጠው ቡና እና ከቡና ምርት የሚወገድ ቆሻሻን በመጠቀም ለግል ንጽህና መጠበቂያ፣ እንደ ዱቄትና ዘይት የመሳሰሉ የምግብ ግብዓቶችን እንዲሁም ለጤና ጠቃሚ የሆኑ የመድኀኒት ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማምረትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ነው።”

“በተለይ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ ከሆኑት መካከል ቢሆንም በተሻለ ዋጋ አይሸጥም። የኮፊ ሪሰሬክት ስራዎች ጠቅላላ አላማ ቡና አምራች ገበሬዎች እና የኢትዮጵያ ቡና ተገቢዉን ጥቅምና ክብር አግኝተው ሁለቱም እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው” ይላል አልማው ሞላ።

ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ በየሀገሩ ተፈላጊ የሆነ ምርት ቢሆንም የኮፊ ሪሰሬክት መነሻ የኢትዮጵያ ቡና አምራቾች የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ አለመሆኑ እንደሆነ አልማው ሞላ ይናገራል።

“ዋነኛ ዓላማችን ከቡና ምርት ዘርፍ ኢትዮጵያ የምታገኘውን ጥቅም ማሳደግ እና ቡና የሚያመርቱ ዜጎች የሚገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ ነው።” ሲል የኮፊ ሪሰሬክት መስራች ይገልጻል።

ኮፊ ሪሰሬክት ከቡና እና ከቡና ተረፈ ምርት የቡና ዘይት፣ ፋይበር፣ ዱቄት፣ የመድኀኒትና የምግብ ግብዓት፣ የውበት መገልገያዎች ግብዓት እና ሌሎችንም የሚያመርት ድርጅት ነው።

ኮፊ ሪሰሬክት በአሁኑ ወቅት ሀገር አቀፍና ቀጠናዊ የውድድር እርከኖችን አልፎ ለ Global Startup Awards (አለም አቀፍ የአዲስ ስራ መስራቾች ውድድር) እጩ ሆኗል። በምስራቅ አፍሪካ ምርጥ የአዲስ ስራ ጀማሪ ዘርፍን ያሸነፈ ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ በ5 ዘርፎች አሽንፏል።

“በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሸነፍናቸው ዘርፎች ምርጥ የአዲስ ስራ ፈጠራ፣ የዓመቱ ምርጥ የአዲስ ስራ መስራች፣ የዓመቱ ምርጥ አዲስ ፈጠራ፣ ምርጥ የጤና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ምርጥ የከባቢያዊ፣ ማህበራዊና የአስተዳደር ቴክኖሎጂ ናቸው” ሲል አልማው ሞላ ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል።

ኮፊ ሪሰሬክት በተጨማሪም በ Entrepreneurship World Cup (የስራ ፈጠራ የአለም ዋንጫ) እጩ ከሆኑ ፈጠራዎች መካከል ኢትዮጵያን የሚወክል ብቸኛ ተቋም ነው።   

ዋና ስራ አስኪያጁ አልማው እንደሚናገረው አፍሪካን በመወከል ድርጅቱ በሚያደርገው ውድድር በ 121 የተለያዩ ዘርፎች ባለሙያዎች ነጥብ የሚሰጡበት ሲሆን 122ተኛው ነጥብ የሚሰጠው ከህዝብ በሚሰበሰው ድምጽ ነው። ዳኞቹ የሚሰጡት ነጥብ የሚያስተማምን ባይሆን እንኳን ለኮፊ ሪሰሬክት የህዝቡ ድምጽ ወሳኝ በመሆኑ የድርጅቱን መልካም ጅማሮ በመመልከት ህዝቡ ድምፅ እንዲሰጥ ጥሪውን አቅርቧል።

ኮፊ ሪሰሬክት ኩባንያ ከሁለት ዓመታት በፊት ጉዞዉን የጀመረ ቢሆንም ወደ ስራ ከገባ አንድ ዓመት ሆኖታል። በአሜሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ ከተለያዩ ተቋማት በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ የፈጠራ ምስረታ አመልካቾች ጋር ተወዳድሮ የእውቅና ሰነድ ማግኘቱንም ዋና ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

በ በአለም አቀፍ የአዲስ ስራ መስራች ውድድር በምርጥ አዲስ ስራ መስራች ዘርፍ የኢትዮጵያውን ኮፊ ሪሰሬክት ጨምሮ ሁለት ተቋማት ከኮንጎ እና ደቡብ አፍሪካ የታጩ ሲሆን በሌሎች የተለያዩ ዘርፎ ደግሞ 28 ኩባንያዎች በውድድሩ ይሳተፋሉ።

የድምጽ መስጫ ገጹ ይህንን ሊንክ https://bit.ly/3I1Lt0d  በመከተል የሚገኝ ሲሆን የድምፅ አሰጣጡ የካቲት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ይጠናቀቃል።

አስተያየት