ጥር 15 ፣ 2014

የዲያስፖራው ጥሪ በአገልግሎት ዘርፉ ላይ ምን ለውጥ አመጣ?

City: Adamaምጣኔ ሃብትማህበራዊ ጉዳዮች

ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በበቂ መጠን ወደ ሐገር ውስጥ ስለ መግባት አለመግባታቸው ሁሉም እንደ ውሎው እና ምልከታው የየራሱን አስተያየት እየሰጠ ይገኛል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የዲያስፖራው ጥሪ በአገልግሎት ዘርፉ ላይ ምን ለውጥ አመጣ?
Camera Icon

Photo credit:- Nor hospitality consulting plc

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ህዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ከሐገር ውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ማስተላለፋቸው አይዘነጋም። ጥሪው እስከ ታህሳስ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ አንድ ሚልዮን ዲያስፖራ ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ የሚያሳስብ ነው። ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮያውያንን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ወዳጆች ሐይማኖታዊ መሰረት ያላቸውን የገና እና የጥምቀት በዓላትን ከወገኖቻቸው ጋር በሐገራቸው እንዲያከብሩ የሚጋብዘውን ጥሪ ተከትሎ ልዩ ልዩ አገልግሎት ሰጪዎች የዋጋ ቅናሽ ስለማድረጋቸው እና የአገልግሎት ጥራት ስለመጨመራቸው አሳውቀዋል። በጥሪው እና በጥበቃው መሰረት ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በበቂ መጠን ስለ መግባት አለመግባታቸው የሚመለከተው አካል አስተያየት ባይሰጥም በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የአቀባበልና የእንኳን ደህና መጣችሁ ስነ-ስርአት ተካሂዷል። የግል እና የመንግሥት ቢሮዎች ዲያስፖራው ለሐገሩ እና ለራሱ ሊያከናውን ስለሚችላቸው ቁምነገሮች ገለጻዎች ተደርገዋል። ኤግዚቢሽንና ባዛር፣ ሲምፖዝየም እና ሴሚናር ተካሂዷል።

ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በበቂ መጠን ወደ ሐገር ውስጥ ስለ መግባት አለመግባታቸው ሁሉም እንደ ውሎው እና ምልከታው የየራሱን አስተያየት እየሰጠ ይገኛል። የአዲስ ዘይቤ አዳማ ሪፖርተር የዲያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባት አገልግሎት ዘርፉ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ በሚመለከት ባለድርሻዎችን አነጋግሯል።

ቴዎድሮስ ገዛኸኝ በአዳማ ከተማ የሚገኝ የመኪና አከራይ መደብር ባለቤት ነው። ከሦስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን መኪናዎቻቸውን እስከ ሦስት ወራት ለሚሆን ጊዜ መኪና ስለማከራየታቸው ነግሮናል። “ወቅቱ የሰርግ እና የበዓል በመሆኑ የመኪና እጥረት አለ” የሚለው ቴዎድሮስ እንደርሱ ያሉ በመኪና ማከራየት ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦች ጥሩ የሚባል ገቢ ያገኙበት ጊዜ ስለመሆኑ አልሸሸገም። “የዲያስፖራዎች መምጣት በስራዬ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ አሳድሯል። ገቢዬንም ጨምሮታል። መኪና ጠፍቶ ጥቂት ዲያስፖራዎች መኪና መከራየት ፈልገው አጥተዋል” ሲል አጋጣሚውን አካፍሎናል።

የማሳጅ፣ የጸጉር እና መሰል የውበት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም በተመሳሳይ ሐሳባቸውን አጋርተውናል።  ዝናሽ ተክለማርያም የ”አንያ ዴይ ስፓ ባለቤት እና ስራ አስኪያጅ ናት። "ከ90 በመቶ በላይ ማለት በሚያስችል መልኩ እያስተናገድን የምንገኘው ቀድሞ ደንበኞቻችንን ነው" ብላለች። የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ዲያስፖራ ተጠቃሚዎች እንደጎበኟቸውም ትናገራለች። የታህሳስ ወር የመጨረሻ ሳምንት እና ሙሉ የጥር ወር ከጾሙ መውጣት እና የሰርግ ወቅት ከመሆኑ አንጻር የስራ ጫና ያለበት ወቅት እንደሆነ አስታውሳ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ በጥሪው ምክንያት ያስተዋለችው ለውጥ እንደሌለ ነግራናለች።

ለረዥም ዓመታት በስደት የኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከሚፈልጓቸው ቁሳቁሶች መካከል ባህላዊ አልባሳት እና መገልገያዎች ይገኛሉ። ዳንኤል ስሜ የዳኒ ዲዛይን ባለቤት እና ዲዛይነር ነው። "የዲያስፖራውን ጥሪ ተከትለን ከፍተኛ ዝግጅት አድርገናል። ያገኘነው ግን የጠበቅነውን ያህል አይደለም” ይላል። ይህ ለመሆኑ እንደ ምክንያትነት ካስቀመጣቸው ነገሮች ውስጥ የጊዜ እጥረት አንዱ ነው። በጥሪው ሐገራቸው የገቡት እንግዶች አብዛኞቹ አጭር የቆይታ ጊዜ እንደነበራቸው የሚናገረው ዲዛይነሩ የበርካቶችን የዘገየ ትእዛዝ ወደ መጡበት ሐገር ከተመለሱ በኋላ በፖስታ ቤት ለመላክ መገደዱን ነግሮናል። አጋጣሚው ለወደፊት የስራ ግንኙነት መሠረት የጣለ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነም ነግሮናል።

ናትናኤል ምትኩ የ”አዳማ ገበታ” መስራች ነው። አዳማ ገበታ በአዳማ የሚገኙ ሆቴል እና ሬስትዎራንቶችን አገልግሎቶች የሚቃኝ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ነው። ናትናኤል “የዲያስፖራው ቁጥር ከፍተኛ ቢሆን እንኳን አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ ለዚህ የተዘጋጁ አልነበሩም” ይላል። "ሆቴሎቹም ኦንላይን ከሚሰሩ ተቋማት ጋር መስራት የጀመሩት በቅርብ ነው። በሬስቶራንቶች ደረጃ ግን ምንም የጠለየ ዝግጅት ዓላየሁም" ሲል ትዝብቱን ነግሮናል።

የጄ ሪዞርት ስራ አስኪያጅ ምንከፋው ሰለሞን ሆቴሉ በአገልግሎቶቹ ላይ በመኝታ ከስታንዳርድ እስከ ፕረዘደንሻል ደረጃ ባሉት ላይ ከቀደመው ዋጋ እስከ 35 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። ከምግብ እና መጠጥ አገልግሎት ላይም እስከ 40 በመቶ ቀንሰዋል።

"ቁጥሩ የጠበቅነውን ያህል ባይሆንም ከሐሙስ እስከ እሁድ ባሉ የእረፍት ቀናት እንግዶችን ተቀብለን እያስተናግደን ነው" የሚለው ምንከፋው ሰለሞን ሆቴሉ ወደ አዳማ ከተማን ከሚረግጡ ዲያስፖራዎች ቢያንስ ግማሽ ያህሉ እንዲመለከቱት አቅዶ መዘጋጀቱንና በልዩ ቅናሽ እንግዶቹን እየተቀበለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የ”ሮቢ ሆቴል” ስራ አስኪያጅ ኪሩቤል ሰብስቤ በሚድያ ማስታወቂያ ባያስነግሩም በሆቴሉ አገልግሎቶች ላይ ቅናሽ ማድረጋቸውን ነግረውናል።

"በእያንዳንዱ አገልግሎት ላይ የ30 በመቶ ቅናሽ አድርገናል። ለሰራተኞቻችንም ስልጠና ሰጥተናል" የሚለው ኪሩቤል ሰብስቤ ዲያስፖራው የሆቴሉን የተለያዩ አገልግሎቶች እየተጠቀመ እንደሆነ ነግሮናል።

ባንኮች የመጣው ዲያስፖራ የያዘውን የውጭ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ፣ ለቀጣይ ሀገራዊ ጥቅም በሚሆን መልኩ ለመጠቀም ምን እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ። እንዲሁም ምን ለውጥ በስራቸው ላይ አስተናገዱ የሚለውን  ባለሞያዎችን እና የባንክ አመራሮችን አነጋግረናል።

ዝናሽ በየነ የኦሮምያ ሕብረት ስራ ባንክ አዳማ ቅርንጫፍ የውጭ ምንዛሬ ሱፐርቫይዘር ናት። ባንካቸው ከዲያስፖራው መምጣት ጋር በተያያዘ ልዩ የብድር እድል እንዳመቻቸ ነግራናለች። "የቤት መግዣ ብድር ነው ያመቻቸው።  ቀድሞ ዲያስፖራው የዋጋውን 30 በመቶ በዶላር  ካስቀመጠ 10 በመቶ ወለድ የነበረውን አስተካክሎ የዋጋውን 10 በመቶ በዶላር ካስቀመጡ ወለዱም ወደ 8 በመቶ ቀንሷል” ስትል ትናገራለች። ይህንን እድል እና የወጭ ምንዛሬን ግብይትን ለማከናወን ምን ያህል ደንበኛ አስተናገዳችሁ ያልናት ዝናሽ "በዲያስፖራው በኩል ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ለውጥ ዓላየንበትም" የሚል ምላሽ ሰጥታናለች።

በቅዳሜ ጥር 7 ቀን 2014 ዓ.ም.ከተዘጋጀው የ10 ኪ.ሜ. የጎዳና ሩጫ በኋላ በተከናወነ የግብዣ ስነ-ስርዓት እና መሠል ዝግጅቶች ዲያስፖራውን የባንክ አካውንት ለማስከፈት መንቀሳቀሳቸውን የሚናገሩት የአዋሽ ባንክ አዳማ ዲስትሪክት ኮንቬንሽናል ሪሌሽን ማኔጀር አቶ ተሾመ ተስፋዬ ባንኩ ከዚህ ቀደምም በአነስተኛ የወለድ ምጣኔ የዲያስፖራውን ማኅበረሰብ እያገለገለ እንደነበር አስታውሰው ለዚህም ጥሪ ተዘጋጅቶ እንደጠበቀ አንስተዋል። "ምን ያህል ደንበኞች መጡ? ምን ያህል ገቢ ተሰበሰበ የሚለውን አሁን ላይ መረጃው ባይኖርም ይመጣል  የተባለው ቁጥር እና ያገኘነው ደንበኛ ግን ተመጣጣኝ አይደለም" የሚለው አቶ ተሾመ ተስፋዬ ባንኩ አሁንም አማራጩን አዘጋጅቶ ደንበኞቹን እየጠበቀ እንደሆነ ነግሮናል።

ከረጅም ጊዜ የስደት ኑሮ በኋላ ወደ ሀገሯ የተለመሰችውና ነዋሪነቷን በአዳማ ያደረገችው አበበች ጉተማ ስለ “ወደ ሀገር ቤት” ጥሪ አነጋግረናት ነበር። እንደ ወ/ሮ አበበች ማብራሪያ ጥሪው በርካታ በውጭ ሀገራት ያሉ ወዳጆቿን ቀልብ ስቧል። ብዙ ጓደኞቿም ወደ ሀገር ቤት መጥተዋል።

በምትኖርበት አሜሪካ ወቅቱ የስራ መሆኑን በማንሳት ከግንቦት በኋላ የእረፍት ጊዜ ስለሆነ የሚመጡ ብዙ እንግዶች እንደሚኖሩ ዝግጅቱ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ትመክራለች።

አስተያየት