ጥር 15 ፣ 2014

ከ400 ዓመታት በላይ የኖረው “ጃንተከል” ዋርካ

City: Gonderባህል ታሪክ

የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል እሴት ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ አቶ ልዕልና አበበ “ጃንተከል” ዋርካ በጎንደር ከተማ ከ400 ዓመት በላይ ያስቆጠረ የእድሜ ባለፀጋ የዋርካ ተክል ነው።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ከ400 ዓመታት በላይ የኖረው “ጃንተከል” ዋርካ
Camera Icon

Photo Credit: Getahun Asnake

በጎንደር ከተማ እድሜ ጠገብ ግዙፍ ጥንታዊ ዋርካዎች እስካሁን ከነግርማ ሞገሳቸው ይገኛሉ። የከተማዋን ወርቃማ ዘመን ከሚያስታውሱ ሁነቶች መካከል የተፈጥሮ ሃብቷን ጠብቃ ለትውልድ ማስተላለፏ አንዱ ነው። በከተማዋ ቁጥራቸው ከ40 የሚበልጥ ሰፋፊና ዕድሜ ጠገብ ዋርካዎች ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል ረዥም ጊዜን በመቆየትና ታሪካዊ ክንዋኔዎቹን በማስተናገድ “ጃን ተከል” ዋርካ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። እነዚህ ዋርካዎች አንደኛው በፋሲል አብያተ መንግስታት በስተ ደቡብ አቅጣጫ የሚገኘው አሁን “ጃንተከል መናፈሻ” የሚል ስያሜ ያገኘው ሲሆን ሌላኛው በአራዳ እና በፒያሳ መንደሮች በቀበሌ 16  አማካይ ላይ ተንሰራፍቶ ይገኛል።

የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል እሴት ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ አቶ ልዕልና አበበ “ጃንተከል” ዋርካ በጎንደር ከተማ ከ400 ዓመት በላይ ያስቆጠረ የእድሜ ባለፀጋ የዋርካ ተክል ሲሆን በ1628 ዓ.ም. በአፄ ፋሲለደስ የተገነባውን የፋሲል አብያተመንግስትን ከ100 ዓመታት በላይ እንደሚቀድም ይናገራሉ። የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት “ጃን” ትልቅ የሚል ትርጓሜ ሲኖረው “ተከል” ደግሞ ተከለው ከሚለው ቃል የተገኘ ነው። “ጃንተከል” ትልቅ ሰው የተከለው የሚል አጠቃላይ ትርጓሜ አለው።

ጃንተከል ዋርካ ከሦስት ክፍለ-ዘመን በላይ እንደመቆየቱ በእነዚህ ጊዜያቶች በርካታ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፓለቲካዊና የተለያዩ ኩነቶችን አስተናግዷል። አሁን ወደ ከተማዋ አደባባይ የዞረው የመስቀል በዓል ቀደም ባሉ ጊዜያት ደመራው ይደመር የነበረው በንጉሡ አደባባይ “ጃንተከል ዋርካ” ወይም “ፊት በር” እንደ ነበርና አጼ ቴዎድሮስ ደጃዝማች ውቤን ድል አድርገው ደረስጌ ማርያም የንግሥና ሥርዓታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ ጎንደር መጥተው የንግሥና በዓላቸውን ባከበሩበት ወቅት ካህናት የቴዎድሮስን የትውልድ ሐረግ በመቁጠር “መንገሥ የሚችለው ከነገሥታት የሚወለድ ነው” በማለት በቴዎድሮስና በካህናቱ መካከል የተነሳው ክርክር የተካሄደው በዚህ ታሪካዊ ቦታ እንደሆነ ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ ቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ ዓይቸው አዲሱ እንደሚሉት “ጃንተከል” ዋርካ ዛፍ ብቻ አይደለም፣ ለጎንደር ከተማ ህዝብ ለየት ያለ ትርጉም ያለው ነው።  በርካታ አገራዊ ጉዳዮች ይመከሩበት የነበረ፣  የሀገር እድገት መሰረት የሆኑ ሀሳቦች ይነሱበት የነበረ፣  ቅኔ የሚዘረፍበት፣ ግዕዝ የሚቀኝበት፣  ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ወንጀለኛን ወይም ሌባን ያጋልጥበት የነበረና  እጅግ ውብና ማራኪ ስነ-ቃል መፍለቂያ የነበረ፣ እጅግ ገራሚ የፍርድ ሂደቶች የተከናወኑበት፣ ፍቅረኛሞች ፍቅራቸውን የሚያጸኑበት፣ ቃል የሚገባቡበት፣ አዋጅ የሚነገርበት፣ ገበያተኛ የሚገበያይበት፣ ሹም ሽር የሚፈጸምበት፣ ለነገስታት ደጅ የሚጸናበት፣ ነገስታት ወታደሮቻቸውን የሚመለምሉበትና ሹመት የሚሰጡበት፣ የተጣሉ ደም የተፋሰሱ የሚታረቁበት፣ እና የመሳሰሉት ማኅበራዊ፣ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የሚከናወንበት ሥፍራ ነበር።

ስለ”ጃንተከል” ዋርካ ገጣሚው ቢገጥምለት፣ ደራሲው የድርሰቱ አንጓ ቢያደርገው፣ ሊቃውንቱ ቢያወዱሱት፣ ሕብረተሰቡ ቢሰበሰቡበት፣ አዕዋፍ ዝማሪያቸውን ቢያንቆረቁሩበት ያንሰዋል ይባልለታል።

ዋርካው እጅግ ሰፊ፣ ውስብስብና ታላቅ ነው። በላዩ ላይ አዕዋፍ ከፊሉ ፍሬውን ከፊሉም ቅጠሉን ይመገባሉ። እላዩ ላይ የንብ ቀፎ ተሰቅሎበት ንቦች የሚኖሩበት፣ በሥሩም ሰዎች  ይጠለሉበታል። መናፈሻ ሆኖ ሰዎች ይገባበዙበታል። በዋርካው ዙሪያ ያሉት ቅርጻቅርጾች ሀገርን ይወክላሉ። እንደ አክሱም ሃውልት፣ እንደ ላሊበላ፣ እንደ ዓባይ ግድብ፣ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን ሊገልጹ የሚችሉ እና ሁሉንም የሃገራችን ክፍሎች ሊወክሉ የሚችሉ ቅርሶች በዋርካው ዙሪያ ይገኛሉ።

የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ እማዋይሽ ደበበ

"ጃንተከል ዋርካ መሬት ሲነካ፣

ወንዱ እምብኝ እምብኝ ሴቱ እንካ እንካ" ተብሎ እንደተገጠመለት ነግረውናል። ሰምና ወርቅ ያለው ግጥም ትክክለኛ ትርጉም ዋርካው መሬት ከነካ የሴት ሞት ይበዛል፣ ሴቶች ያልቃሉ እንደማለት ነው ይላሉ። አባባሉ እንደ ትንቢት ይቆጠራል። በአካባቢው የሚኖሩ ሴቶች ዋርካው ወደ መሬት ሲጠጋ በእንጨት ባላ አስደግፈውት ይሄዳሉ። አለበለዚያ ጫፉን ቆርጠውት ይሄዱ እንደነበር ይገልጻሉ።

“ዋርካው ባለቤት አልባ በመሆኑ፣ ትኩረት የሚሰጠው አካል በማጣቱ፣ እንደ ሌሎች የጎንደር አብያተ ቤተመንግስታቶች ጎብኚዎች  በዚህ ቦታ የማይታዩበት፣ ታሪኩ ሊጠፋ ያንሰራራበት ዘመን ላይ ሰርሰናል” የሚሉት ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ አቶ የወንድወሰን አንዳርጌ ናቸው። “ቦታውና ዋርካው የተባረከ አባቶቻችን ያስረከቡን ነበር፣ ግን በአሁኑ ሰዓት የመጨፈሪያ እና የቢራ መጠጫ  ቦታ መሆን የለበትም” የሚል አስተያየታቸውን  ያስቀምጣሉ።

በታሪካዊው እድሜ ጠገብ “ጃንተከል” ዋርካ አጼ ፋሲል ቤተመንግስት ከማሳነጻቸው በፊት ድንኳን አስተክለው ተቀምጠውበት እንደነበር ይነገራል። በጎንደር በርካታ ዋርካዎች እንዳሉ ቢታወቅም ይህ ዋርካ ግን ከሌሎች ዋርካዎች የተለየና ብዙ ታሪካዊ ክንዋኔዎች የተካሄዱበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። 12ቱ ሊቃነ መናብርት ፍትሀ ነገስትን ገልጠው የሞገቱበት፣ የሃይማኖት ክርክር ጉባኤዎች የተዘጋጁበት፣ ቅኔዎች የተዘረፉበት ለተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎት ሃገራዊ ስብሰባዎች ይካሄዱበት ነበር።

ዋርካውን አቅፈው የያዙት የተለያዩ ቅርጻቅርጾች የተሰራላቸው ቢሆንም ስለነዛ ቅርጻቅርጾች ምንነትና ትርጉም የሚያስረዳ ምንም ነገር አልተቀመጠላቸውም።

አስተያየት