ጥር 15 ፣ 2014

“አሆለሌ” በወርሃ ጥር በደሴ ወጣቶች የሚዘወተር ጨዋታ

City: Dessieየአኗኗር ዘይቤ

በዚህ የደስታ ወር ታዲያ ከሰርግና ግርግሩም በላይ የከተራና የጥምቀት በዓላት፣ የአስቴርዮ ማርያምና ሌሎችም የአደባባይ ትዕይንቶች ይስተናገዳሉ።

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

“አሆለሌ” በወርሃ ጥር በደሴ ወጣቶች የሚዘወተር ጨዋታ
Camera Icon

Photo Credit: idris abdu

የወርሃ ጥር ንግስና፣ ከላይ የሰማይ ሲሳይ አንጋጦ፣ ከታች በመሬቱ ርዚቅ ተማምኖ ለሚያድረው አርሶ አደር የተለየ ነው። ይህ ሲባል ወዲህ በአስረጅነት የሚቀርቡ ጥቂቶች አይደሉም።

አርሶ አደሩ ጐተራው ይሞላል፣ ጨዋታው ይደራል። በዚህ ወር ቀጠሮ መያዙ አግባብ ነው። አዲስ ይለብሳል፣ ሰርግ ይሰርጋል፣ በዓላትን ያከብራል፣ ይደምቃልም።

በዚህ የደስታ ወር ታዲያ ከሰርግና ግርግሩም በላይ የከተራና የጥምቀት በዓላት፣ የአስቴርዮ ማርያምና ሌሎችም የአደባባይ ትዕይንቶች ይስተናገዳሉ።

ከእነዚህ የደመቁ ባህላዊ እሴቶች መካከል ታዲያ በደቡቡ ወሎ ዞን በተሁለደሬ ወረዳ በተለየ መንገድ በልጃገረዶችና ወጣት ወንዶች የሚከበረው ሆላሌ /አሆላሌ/ ጨዋታ አንዱ ነው።

ለመሆኑ ሆለሌ ምንድን ነው? የሚከበርበትስ የተለየ አውድ አለው? ስንል በተሁለደሬ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት የሆለሌ ኪነ-ጥበበ ቡድን የሙዚቃና ውዝዋዜ ባለሙያ የሆኑትን አቶ አስረስ አማረን ጠይቀናል።

አቶ አማረ ሲመልሱ “የሆለሌ በተለያዩ አካባቢዎችም አለ። ነገር ግን በተሁለደሬ ወረዳ የራሱ የሆነ አተገባበር አለው። ተሁለደሬ ወረዳ ካሏት ባህሎች ውስጥ ሆለሌ አንዱ ነው። በጥምቀት፣ በአረፋ፣ በአሹራ፣ በአስቴርዮ ማርያም እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች በሰርግና በእንጨት ሰበራ ጊዜም የሚጫወቱት ባህላዊ ጨዋታ ነው” ብለዋል።

በተቀራረበ የእድሜ እርከን ላይ የሚገኙ ወጣቶች የሚንቀለቀል ስሜታቸውን፣ መፈላለግ መሻታቸውን፣ አንዱ ከሌላው የተሻለ መሆኑን ለማሳየት የሚሞክሩበት የሆላሌ መድረክ የፍቅር፣ የአብሮነትና የመቻቻል ተምሳሌት ተደርጋ በምትጠራው ወሎ ሲተገበር የአደባባይ በዓላትን ተንተርሶ ነው።

አቶ አስረስ አክለውም ”ኮረዳዎቹ በበዓላት ቀን እጮኛ ይመርጡበታል፣ የትዳር አጋራቸውንም ያገኙበታል፣ የራሳቸው የሆነ መጫወቻ ቦታ አላቸው። ወደ ሜዳው እንዲሄዱ ይጠራራሉ። ጐረምሶችም ሳዱላዎችም ተጠራርተው ቦታው ላይ ይሰበሰባሉ። ሴቶቹ “ና ሆለሌ” እየሉ ወንዶቹ በጭፈራ ወደነርሱ ይሄዱሉ። የሐይማኖት ልዩነት ሳይኖር ክርስቲንም ሙስሊምም በዚያ በዓል ላይ ተገኝተው ይጫወታሉ። በዚህ አጋጣሚ እጮኛ የሌላት ባል ታገኛለች ማለት ነው።”

 ሴቶቹ

ኦሆ… ሆላሎ…. ኦሆ ሆላሎ

ና እንሂድ ሲሉት ኦሆ… ሆላሎ አሞኛል ይላል ኦሆ… ሆላሎ

ገለው ሲመጡ  ኦሆ… ሆላሎ በሞትኩኝ ይላል ኦሆ… ሆላሎ

ምን ይላል ኦሆ… ሆላሎ ጉተናው እንቅብ ኦሆ… ሆላሎ

ሲሸሽ አየነው ኦሆ… ሆላሎ ቅብቅብ ለቅብቅብ ኦሆ… ሆላሎ

እያሉ ያዜማሉ።

 የእውነተኛ ፍቅርና አብሮነት መገለጫው “ሆላሌ” ባህልና ወጉን ያልሳተ ይሁን እንጅ፤ በዚያ በጨዋታ መካከል የሚፈጠረው መተፋፈር ቢኖር የሆለሌ ሕግጋት ራሱ ዳኛ ነው። ጐራን ለይቶ ሆታና ጭፈራ ማውረድ፣ ሚናን ለይቶ የታዳሚውን ቀልብ መግዛት መተጫጨት የሆለሌ ጨዋታ ሁነኛ መገለጫዎች ናቸው።

አቶ አስረስ አማረ ስለ ሁኔታው ሲያብራሩ “ወደ ጭፈራው ከሄዱ በኋላ እጮኛ የያዙም ይጫወቱታል። እጮኛ ያልያዙም በጋራ ይጫወታሉ። ወጣቶቹ ወደ ጨዋታ የሚሄዱት እጮኛቸውን ለመጠበቅ ወይም እጨኛ ለማግኘት ሊሆን ይችላል። ሴቶቹ ሆላሌ እያሉ በዜማ ሲገጥሙ ወንዶችም ምላሽ አላቸው።

እባክሽ እቴ በጀግና ሞት፣ ባኮራሽ…. እባክሽ እያሉ ይለምናሉ።

እንቺ ውሰጅ እያሉ ከተሰበሰቡት ሴቶች ለሚፈልጓት ልጃገረድ ሎሚ ዱላ ላይ ሰክተው ያቀብላሉ።

መልጐሜ እባክሽ፣ ….. ባኮራሽ….. ባንቀባረረሽ…. እሾህን ጥሶ በመጣው በኮራው ወዳጅሽ…. እባክሽ ውሰጅ እያለ ይለምናታል።

ከጥር ሰማይ ስር ያለው ትዕይንት አሁንም እንደቀጠለ ነው። በሆለሌ ጨዋታ ጊዜ ተጫጭተውና ተጋብተው፣ ወልደው የከበዱ ጥቂቶች አይደሉም።

ሥርአት ባለው የጨዋታ ሂደት ልብ የፈቀዳትን ከመመኘት ባለፈ የራስን፣ የግልን ለመጠበቅ፣ ሌላ እንዳይወስዳት ለመከላከል የትዕይንቱ ፊት አውራሪ መሆን የግድ ነው።

ታዲያ ወጉ ሆኖ ወንዱ የወደዳትን ጉብል ቃል አውጥቶ ከማሽሞንሞን፣ ከማወደስም በላይ የልመና ሀድራን ያወርዳሉ።

እባክሽ እያለ በሚለምንበትም ሰዓት አሷ የያዘችውን “አሪቲ” (ጥሩ መአዛ ያለው ቅጠል) ለመረጠችው ጉብል ሰጥታ ሎሚውን ትቀበለዋለች። ሆላሌ ትውፊቱን እንደጠበቀ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ ያለ የወሎ ድንቅ ባህል ሆኖም ቀጥሏል።

አስተያየት