ጥቅምት 12 ፣ 2015

አፍሪካ አዳራሽ፡ የአርቱሮ ሜዜዲሚ ኪነ ህንጻዊ ልቀት ቋሚ ምልክት

City: Addis Ababaግለ ታሪክታሪክኪነ-ጥበብ

አርቱሮ ሜዜዲሚ በኢትዮጵያ ከተሞች ላይ ትቷቸው ያለፋቸው፣ እስካሁን የቆሙና ዘመን ተሻጋሪ የዘመናዊ ህንጻ ንድፍ ስራዎቹ በታሪክ ብዙም ሳይወሱ ደብዝዘው ቆይተዋል

Avatar: Hiwot Walelign (Ph.D.)
ህይወት ዋለልኝ

ህይወት በስነ ጽሁፍ የዶክትሬት ዲግሪ ያላት ሲሆን በአዲስ ዘይቤ ኤዲተር ነች።

አፍሪካ አዳራሽ፡ የአርቱሮ ሜዜዲሚ ኪነ ህንጻዊ ልቀት ቋሚ ምልክት
Camera Icon

አርቱሮ ሜዜዲሚ Photo credit: archnet.org

“ለአዳራሹ የሰራሁትን ንድፍ ሰባት ጊዜ ለመቀየር ተገድጄ ነበር፤ ምክንያቱም ለግንባታው የተመረጠው ቦታ ሰባት ጊዜ ስለተለወጠ ነው” ይላል አርቱሮ ሜዜዲሚ እ.አ.አ በ1979 በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ የአፍሪካ አዳራሽን ንድፍ በሰራበት ጊዜ ስላጋጠሙት ሁኔታዎች ሲያብራራ። 

የግንባታው ቦታ መቀያየርና የንድፎቹም ቅርጽ መለዋወጥ ጊዜ የወሰደበት አርክቴክቱ ሜዜዲሚ በስተመጨረሻ የጊዜ ገደብ እንደተጣለበት ያስታውሳል። 

“በወቅቱ የስራና መገናኛ ሚኒስትር የነበሩት ራስ መንገሻ ስዩም ንድፌን ለአለማቀፉ ተቋራጭ በ91 ቀናት ውስጥ ጨርሼ እንዳስረክብ አዘዙኝ። በዚህ የተነሳ ለ91 ቀናት ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ ለሊቱ 10 ሰዓት ድረስ እሰራ ነበር” ብሏል።   

የአዳራሹ ንድፍ አልቆ የግንባታ ስራው ከቀጠለ በኋላ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ ቀዳማዊ ኅይለ ስላሴ ማታ ማታ እየመጡ ይጎበኙት እንደነበርም የቬኒሱ ዩዋቭ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጃኮፖ ጋሊ የአርቱሮ ሜዜዲሚን ህይወትና ስራዎች በዳሰሱበት ጥናታዊ ጽሁፋቸው ገልጸዋል። 

ግንባታው አልቆ ከተመረቀ ድፍን ስድስት አስርት አመታት ሊያስቆጥር ትንሽ የቀረው የአፍሪካ አዳራሽ በቅርቡ እድሳት ሊደረግለት እንደሆነ ተሰምቷል። 56 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል የተባለለትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወጪውን የሚሸፍነው የእድሳት ስራ ጥቅምት 4 ቀን በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መስሪያ ቤት ባለሙያዎችና ሃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል። 

የአዳራሹ እድሳት ሲጠናቀቅ “ቱሪስቶች የሚጎበኙት፣ የፓን አፍሪካን እንቅስቃሴ ታሪክ የሚያሳይ እንዲሁም የአህጉሪቱን የባህል፣ የታሪክና የተፈጥሮ ትሩፋቶች የሚያንጸባርቅ ይሆናል” ብለዋል አንቶኒዮ ፔድሮ፣ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሃፊ በስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር።

በ1950 ዓ.ም ለአርክቴክት ሜዜዲሚ የታሪካዊውን የአፍሪካ አዳራሽ ንድፍ እንዲሰራ ሃላፊነት የሰጡት ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ነበሩ። 

የሜዜዲሚ እና የአጼ ኃይለ ስላሴ ትውውቅ ወደኋላ ከ1940ዎቹ ይጀምራል። ለትውውቃቸው መንስኤ የሆነውም በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበረው የቴክኒክ ባለሞያዎች እጥረት እንደነበር የታሪክ ጸሃፊው አንጀሎ ዴል ቦካ 'ንጉሱ' በተሰኘው መጽሃፉ ላይ አንስትቶታል።   

አርቱሮ ሜዜዲሚ የትውልድ ሃገሩን ጣልያንን ለቆ ወደ ኤርትራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጓዘው የ18 አመት ወጣት እያለ በ1932 ዓ.ም ነበር። ወቅቱ የሁለተኛው የአለም ጦርነት የተፋፋመበት፣ ሃገሩ ጣልያንም ኤርትራን ቅኝ በምትገዛበት ጊዜ ነበር። ከጀርመን ወገን ቆማ የነበረችው ጣልያን በቀጣዩ አመት፣ ማለትም በ1933 ዓ.ም እንግሊዝና ፈረንሳይ በመሩት ጥምር ጦር ተሸንፋ ኤርትራን ለቀቀች። 

በጊዜው አስመራ ውስጥ ከነበረ የቴክኒክ ተቋም በቀያሽነት የተመረቀው ሜዜዲሚም የመጀመሪያ የህንጻ ንድፎቹን የሰራው እዚያው አስመራ ውስጥ ለሚገኙ ግለሰቦች መኖሪያ ቤቶችና ተቋሞች ነበር። 

“እራሱን ያስተማረ ባለሞያ” ይሉታል ጃኮፖ ጋሊ፣ የህንጻ ንድፍ መደበኛ ትምህርት አለማጥናቱን በመጥቀስ። ጨምረውም “በእንቅስቃሴ የተሞላችውን የአስመራ ከተማ ወቅታዊ ሁኔታ በሚገባ የተጠቀመ እና በሚገርም ፍጥነት በርካታ ንድፎችን የሰራ” በማለት ይገልጹታል። 

አርቱሮ ሜዜዲሚ የመጀመሪያውን እውቅና ያገኝበትን አስመራ ከተማ ውስጥ የሚገኝ መዋኛ ገንዳ ንድፍ የሰራው ገና የ22 አመት ወጣት እያለ ነበር። ይህ የመዋኛ ስፍራ በወቅቱ የዜና አውታሮች የዘገቡለትና ዶሙስ የተሰኘው ታዋቂ የጣልያን የኪነ ህንጻ መጽሄትም በ1949 እ.ኤ.አ “ምርጥ ስራ” በማለት አሞካሽቶታል። 

ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ጋር ከተዋወቀ በኋላም ሜዜዲሚ በንጉሱ ትዕዛዝ የአስመራውን መነን ሆስፒታል፣ የአሰብን ባህር ሃይል ማሰልጠኛ እንዲሁም የደብረሲና ገዳም የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ጨምሮ የሌሎች በርካታ ህንጻዎችን ንድፍ ሰርቷል። 

አርቱሮ ሜዜዲሚ ከ1940ዎቹ እስከ 60ዎቹ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ፣ በጅቡቲና በየመን ከ1000 በላይ የንድፍ ስራዎችን ሰርቷል ተብሎ እንደሚገመት መምህር ዳዊት በንቲ ይናገራሉ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የኪነ ህንጻ፣ ግንባታና ከተማ ልማት ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ዳዊት እንደሚያስረዱት ይህ ማለት ሜዜዲሚ በስራው ውጤታማ በነበረበት ጊዜ በሳምንት አንድ ንድፍ ሰርቷል እንደማለት ነው።

ከሜዜዲሚ ዋነኛ ንድፎች መካከል አንዱ የሆነው የአፍሪካ አዳራሽ በይፋ የተመረቀው በ1956 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደውና 32 ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች በተሰበሰቡበት ኮንፈረንስ ላይ ነበር። አጼ ኃይለ ስላሴም እንግዶቻቸው የሆኑትን የአፍሪካ መሪዎች የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የምስረታ ቻርተር ላይ ፊርማቸውን እንዲያስቀምጡ የጠየቁትም በዚሁ ኮንፍረንስ ላይ ነበር። በዚሁ የአፍሪካ አዳራሽ ጣሪያ ስር ታሪካዊው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሰረተ። 

በ1950 ዓ.ም የአፍሪካ አዳራሽን ንድፍ ከመስራቱ በፊት፣ አርቱሮ ሜዜዲሚ ኒው ዮርክ የሚገኘውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጽ/ቤት፣ ሮም የሚገኘውን የአለም የምግብ እና ግብርና ድርጅት (ፋኦ) ዋና መስሪያ ቤት እንዲሁም ፓሪስ ያለውን የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት ህንጻ ጎብኝቷል። ይህንንም ያደረገው ለአፍሪካ አዳራሽ ንድፉ የአለማቀፍ ድርጅቶች ህንጻዎችን አሰራር ልምድ ለመውሰድ ነበር።   

መምህር ዳዊት እንደሚሉት አርቱሮ “በእይታው ከጊዜው የቀደመ፣ ስራዎቹም ዘመን ተሻጋሪ ናቸው። ንድፎቹ ዘመናዊ ቢሆኑም ኢትዮጵያዊ ቀለም ነበራቸው። የኢትዮጵያን ጥንታዊ የኪነ ህንጻ ምልክቶች በዘመናዊው ኪነ ህንጻ ቅርጽና ቦታ ላይ በማካተት የንድፍ ስራውን ያከናወነ ባለሙያ ነበር።”

የአፍሪካ አዳራሽ ህንጻ 75 ሺ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን 260 ቢሮዎች አሉት ። መሰብሰቢያ አዳራሹ 800 መቀመጫዎችን የያዘና ጎን ለጎን የሚገኙ ከ30 እስከ 60 መቀመጫዎች ያሏቸው የኮሚቴዎች ክፍሎች ይገኙበታል። ቤተ መጻህፍት፣ አውደ ርዕይ ማሳያና የበዓል ማዘጋጃ ክፍሎች ሲኖሩት ማንኛውም ሰው ሊዝናና የሚችልበት ገላጣ አዳራሽ እንዲሁም የባንክ፣ አየር መንገድ ትኬት ሽያጭና አስጎብኚ ድርጅቶች ቢሮዎች ይዟል።

በተጨማሪም “ክቡ አዳራሽ ውብና ለየትኛውም የአየር ሁኔታ ተስማሚ ተደርጎ የተሰራ፣ የጸሃይ ብርሃንን በመጠቀም የፈካ እንዲሁም ተፈጥሮአዊ አየር እንደልብ የሚተላለፍበት ክፍል ነው” ይላሉ ፕሮፌሰሩ፣ አርቱሮ ሜዜዲሚ በንድፎቹ ላይ ለጥቃቅንና ዝርዝር ገፅታዎች ትኩረት እንደሚሰጥ ሲያስረዱ።

ይህን ሃሳብ የሚጋሩት መምህር ዳዊት ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ “የሚገርመው ነገር የአፍሪካ አዳራሽ ተሰብሳቢዎች አዳራሹን ለቀው ሳይወጡ እዚያው የቡና እረፍት መውሰድ ያስችላቸዋል። ትንሽ ለማረፍ ብለው ወጣ ቢሉም በአዳራሹ ውስጥ የሚደረገው ውይይት አያመልጣቸውም፣ ይሰማቸዋል። ለዚህ ነው የሜዜዲሚ ስራዎች ዘመን ተሻጋሪ ናቸው የሚባሉት” ይላሉ። 

የጣልያኑ ዶሙስ መጽሄትም በ1956 ዓ.ም እትሙ አዳራሹን “የተራቀቀ፣ ውብና ጽዱ እንዲሁም ግርማ ሞገስ የተላበሰ” ሲል ገልጾታል። 

ንድፉ መሬት ላይ አርፎ የህንጻው ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የአዳራሹን ውስጣዊ ክፍል የማስዋብ ስራ ላይ ከተሳተፉት ባለሙያዎች አንዱ የአለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ነበሩ። በመስታወት ላይ የሰሩት የቅብ ስራም እስከዛሬ ድረስ ውበቱ የሚደነቅና “አፍሪካውያን ለነጻነት ያደረጉትን ትግልና እድገት የሚያሳይ” ተብሎለታል።

በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የአዳራሹ የእድሳት ስራ የመጀመሪያው አይደለም። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወጪ ከ1963-67 ዓ.ም የቆየ የእድሳትና ማስፋፊያ ስራ ተሰርቶለት ነበር።  

ከአፍሪካ አዳራሽ በተጨማሪ፣ አርቱሮ ሜዜዲሚ በአዲስ አበባ ብቻ ከ20 ያላነሱ ዋና ዋና ህንጻዎችን ንድፍ ሰርቷል። ከነዚህም ውስጥ የዘውዲቱ ህንጻ፣ ፊንፊኔ ህንጻና የንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ይገኙበታል። 

ከሁሉም በላይ ግን የአርቱሮን የኪነ ህንጻ ጉምቱ ባለሞያነት ያስመሰከረለት የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ህንጻ ነበር። የህንጻው ንድፍ በ1950ዎቹ የመጀመሪያ አመታት የተሰራ ሲሆን ህንጻው በ1953 ተጀምሮ በ1956 ዓ.ም ተጠናቆ ተመርቋል። 

ከእነዚህ በተጨማሪም ባህር ዳር ከተማ የሚገኘው የጣና ቤተ መንግስት ህንጻ ንድፍም የሜዜዲሚ ስራ ነው። 

አርክቴክቱ በወቅቱ የሚገባውን ዝና እና እውቅና አላገኘም የሚሉት አቶ ዳዊት ምናልባትም የውጪ ዜጋ መሆኑ አንድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል። “በቅኝ ግዛት በተያዘች ሃገር ውስጥ የኖረና የሰራ ቢሆን ቅኝ ገዢዎቹ በደንብ ይዘክሩት ነበር። እሱ ግን አብዛኛዎቹን ታዋቂ ንድፎቹን የሰራው በነጻነቷ በምትኮራው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ይህም ዝናውን ያደበዘዘው ይመስለኛል” በማለት ግምታቸውን ይናገራሉ። 

የአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በአብዮታዊው ደርግ መተካቱ ሌላው የአርቱሮን ስራዎች እንደሚገባቸው ሳይሰነዱና ሳይዘመርላቸው እንዲቀሩ ያደረገ ታሪካዊ ክስተት ነው ይላሉ መምህር ዳዊት። ተተኪው ደርግ፣ ንጉሰ ነገስቱ ለሃገራቸው ያበረከቷቸው መልካም ስራዎች ጎልተው እንዲታወቁና እንዲወደሱ አልፈለገም፣ አልሰራምም። 

በእነዚህና መሰል ምክንያቶች አርቱሮ ሜዜዲሚ በኢትዮጵያ ከተሞች ላይ ትቷቸው ያለፋቸው፣ እስካሁን የቆሙና ዘመን ተሻጋሪ የዘመናዊ ህንጻ ንድፍ ስራዎቹ በታሪክ ብዙም ሳይወሱ ደብዝዘው ቆይተዋል። 

ሆኖም ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የኢትዮጵያ የኪነ ህንጻ ባለሙያዎች ከአለማቀፍ አቻዎቻቸው ጋር በመተባበር የአርቱሮ ሜዜዲሚን 100ኛ አመት የልደት በዓል አስበውት ውለዋል። በአካልና በበይነ መረብ ከተለያዩ የአለም ሃገራት በመሰባሰብ ህይወቱንና ስራዎቹን የሚያትቱ ጥናታዊ ጽሁፎችን በማቅረብ የተዘነጋውን ታላቅ ባለሞያ አክብረውታል። 

ይህ በቬኒሱ ዩዋቭ ዩኒቨርሲቲ፣ በጣልያን ኤምባሲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የህንጻ ንድፍ፣ ግንባታና ከተማ ልማት ትምህርት ቤት ትብብር የተካሄደው ኮንፈረንስ ለብዙዎች የአርኪቴክቱን ማንነት ማጠያየቅ እንዲጀምሩና የዜና አውታሮችም ስራዎቹን እንዲዘክሩ በር የከፈተ ነበር። 

በ1984 ዓ.ም አርቱሮ ሜዜዲሚ በጻፈውና 'ኃይለ ስላሴ፡ ማስታወሻና ምስክርነት' በተሰኘው ደብዳቤው ላይ “አብሬአቸው በሰራሁባቸው 23 አመታት አንድም ጊዜ የመንግስታቸው አባል እንድሆንም ሆነ ስራዎቼን በግዛታቸው ብቻ እንድወስን አልጠበቁም” ብሏል። 

ስለ ንጉሰ ነገስቱ የግል ባህርይ ሲገልጽም በወግ አጥባቂነትና በተራማጅነት መሃል አጣብቂኝ ውስጥ የነበሩ እንዲሁም “እንደ አቢሲኒያ አይነት ጥንታዊት ሃገር እንድታንሰራራ እና እንድትዘምን ለማድረግ የተፈተኑ” ሲል ገልጿቸዋል።   

አጼ ሃይለስላሴ ለአርቱሮ ሜዜዲሚ ሶስት የክብር ኒሻኖች አበርክተውለታል። እነዚህም የኢትዮጵያ ከፍተኛ መኮንንነት የክብር ኒሻን፣ የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ የክብር ኒሻን እና የዳግማዊ ምንሊክ መስቀል የክብር ኒሻን ናቸው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፖስታ ቤት አስተዳደር የአርኪቴክቱን ዋና ዋና ስራዎች በአምስት ቴምብሮች ላይ ያተመ ሲሆን ይህን ተከትሎም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሶስት ስራዎቹን የሚዘክሩ ቴምብሮች አትሞለታል። 

አርቱሮ ሜዜዲሚ በ2001 ዓ.ም በ87 አመቱ በትውልድ ስፍራው ሲየና፣ ጣልያን ህይወቱ አልፏል። የአፍሪካ አዳራሽ ግን ዘመን ተሻጋሪ፣ ቋሚ መታሰቢያው ሆኖ እስካሁን አለ።  

አስተያየት