ጥቅምት 17 ፣ 2015

የክፍያ መንገዶች ታሪፍ እስከ 90 በመቶ ሊጨምር ነው

City: Adamaዜናኢኮኖሚወቅታዊ ጉዳዮች

በአራት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ከ57 በመቶ እስከ 90 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ አለው።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የክፍያ መንገዶች ታሪፍ እስከ 90 በመቶ ሊጨምር ነው
Camera Icon

Credit: Social Media

የኢትዮጵያ  የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ እንዳስታወቀው ከጥቅምት 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የመንገድ ክፍያ ታሪፍ ማሻሻያ እንደሚያደርግ አስታወቀ። 

የኢንርፕራይዙ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ ዘሃራ መሃመድ በተለየ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለጹት የታሪፍ ማሻሻው ዝቅተኛው 57 በመቶ ሲሆን እስከ 90 በመቶ የሚጨምር ሲሆን የተሸከርካረዎች ዓይነት በአራት ደረጃዎች የተከፈሉ እንደሆኑ ገልጸዋል። 

በምድብ አንድ ተሽከርካሪዎች ላይ በኪሎ ሜትር 76 ሳንቲም ከነበረው ዋጋ ወደ 1 ብር 19 ሳንቲም ከፍ ያለ ሲሆን ከከባድ መኪኖች ምድብ አራት ደግሞ ከ1 ብር 05 ሳንቲም ወደ 1 ብር ከ99 ሳንቲም ከፍ  ማለቱን የገለጹት የኮሚኒኬሽን ኃላፊዋ ታሪፉ በጉዞ ርቀት እንዲሁም በመኪኖች መጠን እና የመንገድ ጫና ላይ ተመስርቶ የተሰላ ሲሆን በአራት የክፍያ መደቦች ተሽከርካሪዎች መመደባቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከ2011 ዓ.ም ወዲህ በአራት ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው ማሻሻያ በወቅቱ ያልነበሩትን የሞጆ ባቱ እና የድሬዳዋ ደወሌ መንገዶች ማካተቱን ማወቅ ችለናል።

አሽከርካሪዎች የክፍያ መንገዶችን በመጠቀማቸው የሚያገኙት ትርፍ አለ የሚሉት የኮሚኒኬሽን ኃላፊዋ ድርጅቱ በሰራው ጥናት መሰረት በአሁን ወቅት እያስከፈለ ያለው የዚህን ትርፍ 36 በመቶ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከተደረገው የመንገድ ታሪፍ ጭማሪ ጋር በተያያዘ የቀድሞው የአዲስ-አዳማ መንገድ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ የተጎዳ እና ከፍተኛ ጥገና የሚፈልግ መሆኑ ይታወቃል። 

ይህ ባለበት ሁኔታ እንደብቸኛ የሚታየው የክፍያ መንገድ ተደጋጋሚ የሚነሱበት እንደ መኪና ዝርፊያ፣ በተከለለ የመንገዱ ክልል ውስጥ ያለ የሰው እና የእንስሳት  እንቅስቃሴ  ለማሻሻል ምን እየተሰራ ነው ያልናቸው የኮሚኒኬሽን ኃላፊዋ የችግሩን መኖር አምነው መሻሻል እንዳለውና በቅርቡ በአስተዳር አካላት እና ከጸጥታ አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዋጅ ቁጥር  843/2007 ዓ.ም የተቋቋመውና የክፍያ መንገዶችን እንዲያስተዳድር ስልጣን የተሰጠው  የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉተ 8 አመታት የክፍያ መንገዶችን እያስተዳደረ ይገኛል። 

በስሩ አዲስ-አዳማ፣ የድሬደዋ-ደወሌ እና  የሞጆ-ባቱ የፈጣንና የክፍያ መንገዶችን ያስተደድራል፡፡

አስተያየት