ምንም እንኳን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከተማቸው እንደ ስሟ አዲስ እና ውብ ሆና እንድትታይ ቢመኙም፣ ቆሻሻ እና መጥፎ ጠረን ከስሟ ጋር አብረው መነሳታቸው አልቀረም። በተለይ ክረምት መጣሁ መጣሁ ባለ ቁጥር የጎርፍ ስጋት ከሚሆኑት እና ከተማዋን ከሚያቋርጡ በርካታ ጅረቶች በተጨማሪ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎቿ ጥራታቸውን ጠብቀው የተሰሩ ባለመሆናቸው የከተማዋን አንዳንድ ዋና መንገዶች ሳይቀሩ በቆሻሻ ፍሳሽ ይበከላሉ።
ለዚህ ችግር ከሚጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ ቱቦዎቹ በደረቅ ቆሻሻ ተሞልተው መደፈናቸው ነው። አንዳንዶቹ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በትክክለኛ ተዳፋት ባለመሰረታችው በሚፈጠረው መፈራረስ በቱቦዎቹ ውስጥ ማለፍ የነበረበት ፍሳሽ በመኪና መንገዶች ላይ ይፈሳል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከሚገኙ ህንፃዎች ወደ አስፓልት የሚለቀቁ ፍሳሾች ደግሞ ሌላው የከተማ ሽታ ጠንቅ ናቸው። የሚፈጥሩት መጥፎ ሽታም ንጹህ አየር መተንፈስን አዳጋች ያደርገዋል። ይህም ማህበረሰቡን ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እየዳረገው ይገኛል። ይህ ችግር በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ላይ እንደሚስተዋል የሚታወቅ ሲሆን አዲስ ዘይቤ የተወሰኑትን ቃኝታለች።
በአዲስ አበባ አያት አካባቢ፣ ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ አደባባይ ዙሪያ በሚገኝ ከስስ ቆርቆሮ እና ካርቶኖች በተሰራ ትንሽ ዳስ ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦች የዚህ ገፈት ቀማሾች ናቸው። በዚህ ቤት ውስጥ ባለቤቱን እና ሁለት ህጻናት ልጆቹን ይዞ የሚኖረው አበረ ገበያው ምንም ማድረግ ባለመቻሉ ሽታው ከሚያመጣቸው በሽታዎች ጋር እየተጋፉ መኖር እጣቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ከዛች ደሳሳ ቤታቸው ጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ በተለያዩ ቆሻሻዎች የተሞላ ቱቦ አለ። ይሄው ቱቦ በዝናብ ወቅት ከተለያዩ ህንፃዎች እና መኖሪያ ቦታዎች በሚወጣው ቆሻሻ እና ፍሳሽ ሲሞላ ጅረቱ በነፃነት ወደ ቤቱ ወለል ይፈስሳል። ይህ ሁኔታ በብዙዎቹ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ ውስጥ ባሉ ግንብ ተጠግተው በቆሙ ቤቶች ውስጥ የተለመደ ሲሆን ለአልፎ ሂያጁ ሳይቀር ከባድ ነው።
በዚሁ መንደር ከነአበረ ቤተሰብ መኖሪያ የተሻለ የግንብ ቤት ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚኖሩት አቶ ከተማም ከስጋት እንደማይድኑ ይናገራሉ። ከተማ በቱቦው ከሚወጣው አስከፊ ጠረን በተጨማሪም የጎርፍ ስጋት አለባቸው። በክረምት የሚጥለው ዝናብ ጎርፍ ሆኖ ከተለያዩ ቦታዎች አሸዋና ጠጠር ተሸክሞ ሲወርድ በደረቅ ቆሻሻ የተደፈነውን ቱቦ አልፎ መንደሩ ውስጥ ይተኛል፡፡ አንዳንዴም እስከ ዋናው መንገድ ድረስ አልፎ እንደሚሄድ እና ቤታቸው ላይ አደጋ እንደሚያስከትሉ ይናገራሉ፡
ከአመት በፊት በተመሳሳይ ወቅት የጎርፍ ስጋት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ከተማ፣ ለሚመለከተው አካል ስጋታቸውን በተደጋጋሚ ቢናገሩም እስካሁን የተደረገላቸው ነገር እንደሌለ ሲገልፁ “እኛን የሚሰማን የለም፣ ቢያንስ እዚህ መንደር ከኛ ጋር የሰማይ እና የምድር በሚያህል ልዩነት እጅግ ጥሩ ኑሮ የሚኖሩ ግለሰቦች አሉ መንግስት ላይ ተጽዕኖ ፈጥረው ከችግር እንድንላቀቅ ለምናደርገው አቤቱታ አጋዥ ቢሆኑን ችላ ባይሉን መልካም ነው” በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በዚህ አያት አካባቢ የሚገኙት ቦዮች በየጊዜው በደረቅ ቆሻሻ በመደፈናቸው፣ በትክክል ባለመሰራታቸው እና በመንገድ ስራ ወቅት በመሰባበራቸው ምክንያት የሚተላለፉት ፍሳሾች ወደ ዋና መንገድ ላይ ሲወጡ ለእይታም ሆነ ለሽታ ያስጸይፋሉ። ይሄ ቦታ ታክሲ መያዣ በመሆኑ እና ታክሲዎች እንዲሁም ተሳፋሪዎች ላልተወሰኑ ደቂቃዎች የሚቆሙበት በመሆኑ የተለያዩ የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ምሬታቸውን ይናገራሉ።
ክብሩይስፋ ጌታቸው የተባለ የታክሲ ተራ አስከባሪ “ለታክሲ መቆሚያ ይመቻል ተብሎ የተመረጠው ቦታ ይሄ ነው፣ እዚህ ከስራችን ያለው ቱቦ ደግሞ በተደጋጋሚ ነው ሲፈነዳ ከባድ ሽታ ነው የሚፈጥረው፣ ለመዘጋጃ ቤት እንጮሃለን ግን ሰሚ የለም” በማለት ቅሬታውን ተናግሯል። በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ሌሎች ባለታክሲዎች እና መንገደኞችም ይህንኑ ቅሬታ ያጠናክራሉ።
ሌላኛው የዚህ አይነት እጣ የገጠመው ሰፈር ደግሞ በአቃቂ ቃሊቲ የሚገኘው አባ ሃና ሰፈር ነው። በዛ አካባቢ የሚገኘው የፍሳሽ ማስተላለፊያ ቱቦ ፍሳሽ ማስተላለፉን ትቶ በውስጡ የተለያዩ ደረቅ ቆሻሻዎች ተሞልተውበት ይታያል። የአካባቢው ነዋሪዎችና አንዳንድ መንገደኞች እንደ መፀዳጃ ሲጠቀሙትም ይስተዋላል።
ባለው አስከፊ ጠረን ምክንያት እዚህ አባ ሃና አካባቢ ለጥቂት ደቂቃ መቆም አስቸጋሪ ነው። ዙሪያ ገባውን ወደ ዝንብ መናኸሪያነት የቀየረው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ የሆነው ቱቦ የዝናብ ውሃ ሲያርፍበት ምን አይነት የከፋ ጠረን ሊፈጥር እንደሚችል ማሰብ አይከብድም። በዚህ ቱቦ ዙሪያ የመንገድ ላይ ንግድ ለሚሰሩ እንደ ሂክማ አብደላ ያሉ ሰዎች ደግሞ ይህን ችለው እንዲቆዩ ይገደዳሉ።
“እኔ የምተዳደረው ጥቃቅን ሸቀጦችን በመሸጥ ነው፣ መኖሪያዬ እዚሁ አካባቢ በመሆኑ ከዚህ ሰፈር ራቅ ብዬ ልስራ ብል የትራንስፖርት ወጪውን አልችለውም። ከዚህ ሰፈር ደግሞ ከሁሉም አቅጣጫ የሚመጣ ሰው የሚተላለፍበት አዋሳኝ መንገድ ይሄ ቦታ በመሆኑ ለገበያው ከዚህ የተሻለ ቦታ አላገኝም” የምትለው ሂክማ ስጋቱ ለመኖሪያ ቤቷም ጭምር እንደሆነ ትናገራለች።
በአካባቢው የተሠራው ቱቦ ከመንገድ በላይና በታች በኩል የሚኖሩትን ያላገናዘበና ለጎርፍ አደጋ በሚያጋልጥ መልኩ መሆኑን ስትናገር ከሶስት አመት በፊት እንዲህ ባለ ሁኔታ ሲኖሩ የጎርፍ አደጋ ላጋጠማቸው የመንደሩ ነዋሪዎች የኮንዶሚኒየም ቤት እንደተሰጣቸው በማስታወስ፣ ቀሪዎቹ ተጋላጭ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችን ሊከሰቱ ከሚችሉ የጎርፍ አደጋዎች ለማዳን የሚሰራው ቅድመ መከላከል ሥራ ግን ደካማ መሆኑን ጠቁማለች።
በአዋጅ ቁጥር 68/1963 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ፤ በድጋሚ በአዋጅ ቁጥር 10/87 መሰረት የተቋቋመው የአዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን ከስራዎቹ አንዱ የተስተካከለ የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓትን መዘርጋት መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም የሰማናቸውን ቅሬታዎች ይዘን ያነጋገርናቸው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሰርካለም ጌታቸው በከተማዋ በጎርፍ ምክንያት የመንገዶች መጨናነቅና ምቾት ማጣት እንደሚስተዋል አምነዋል።
ለችግሩ የተለያዩ ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ የገለፁት ዳይሬክተሯ የውኃ ማፍሰሻ መስመሮች በቆሻሻ መደፈናቸው ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል። “በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በውኃ መፍሰሻ ፉካዎች ውስጥ ቆሻሻዎች በመጣል ቱቦው እንዲደፈን የሚያደርጉ ነዋሪዎችና ድርጅቶች ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው” በማለት የቱቦው በቆሻሻ መደፈን ጎርፍ መንገዱን እንዲያጥለቀልቅና ውኃ መንገድ ላይ እንዲተኛ የሚያደርግ ሲሆን፣ በዚህም ጊዜ መንገዱን በመቦርቦር ለጉዳት በመዳረግ የመንገዱን የአገልግሎት ዕድሜ እንደሚያሳጥር ገልጸዋል።
በመሆኑም በክረምት ለሚፈጠረው የመንገዶች በጎርፍ መጥለቅለቅ መፍትሔ ያለው በነዋሪዎች እጅ መሆኑን በመጠቆም የከተማዋ ነዋሪና ድርጅቶች ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ ከቻሉ የውኃ ማስወገጃ መስመሮች መደፈናቸው ያቆማል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ማህበረሰቡ ምናገባኝ ሳይል የውኃ ማስወገጃ መስመሮችንና ፉካዎችን ቢያፀዳ መንገዱ ላይ ውኃ እንዳይተኛ በማድረግ ሰላማዊ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር ያግዛል ሲሉ ባለስልጣን መስርያ ቤቱም ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የውኃ መውረጃ መስመሮች የውኃውን መጠን በአግባቡ ማስተናገድ እንዲችሉ መልሶ ግንባታ እያከናወነባቸው እንደሚገኝ ተበላሽተው አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የመንገድ ዳር የዝናብ ውኃ መፍሰሻዎችንም እንደሚቀይሩ ገልጸዋል።
የኢፌድሪ ሕገመንግስት ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጆች ተፈጥሮ የሚመነጩ የማይጣሱና የማይገፈፉ መሆናቸውን፣ እንዲሁም የዜጎች እና የሕዝቦች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንደሚከበሩ በአንቀጽ 10 መደንገጉ የሚታወቅ ሲሆን ዲሞክራሲያዊ መብቶች በሚለው ክፍል በአንቀጽ 44 ‹‹የአካባቢ ደህንነት መብት›› በሚለው ሥር ‹‹ሁሉም ሰዎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው›› በሚል ተደንግጓል፡፡
የሕግ አንደኛው ዓላማ የሕዝቦቹን፣ የነዋሪዎቹን ሰላም፣ ደህንነት፣ ሥርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ከመሆኑ አንፃር የአካባቢን ደህንነት ጉዳይ በዝምታ አላለፈውም፡፡ የሕዝብ ወይም የነዋሪዎች ሰላምና ደህንነት ከሚያውኩ ሁነቶች መካከል የተበከለ አካባቢ መሆኑ አያጠያይቅም።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የቆሻሻ አያያዝ፣ አሰባሰብና አወጋገድ በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያወጣውን ሕግ ደንብ ቁጥር 13/1996 ላይ በህግ ከተደነገጉ ተግባራት መካከል ማንኛውም ሰው ከመኖሪያ ቤት ወይም ከድርጅት የሚወጣውን ቆሻሻ በአግባቡ መያዝ ግዴታው መሆኑ፣ ማንኛውም ሰው ከመፀዳጃ ቤት ውጭ መሽናት ወይም መፀዳዳትና የሰው ዓይነምድርን በፌስታልና በወረቀት ወይም በሌላ ነገር በመጠቅለል ወይም ክፍት ወይም ዝግ በሆነ ዕቃ ውስጥ በማስቀመጥ በመንገድ፣ በአደበባይ ወይም በሌሎች ባልተፈቀዱ ቦታዎች መጣል ወይም ከደረቅ ቆሻሻ ጋር በማደባለቅ ማስወገድ የተከለከለ መሆኑ፣ ማንም ሰው እጣቢ ወይም ሌሎች ማናቸውንም ፍሳሾች ከተፈቀደ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ውጭ ወደ መንገድ ወይም አካባቢው ማፍሰስ ወይም እንዲፈስ ማድረግ የተከለከለ መሆኑ፣ እንዲሁም ማንኛውም ሰው የመኖሪያ ቤት፡ የድርጅት ወይም የመሥሪያ ቤት ይዞታው አጥር ጀምሮ ፊት ለፊቱ 10 ሜትር ባለው ርቀት ድረስ ፍሳሽ ቆሻሻ የማጽዳት፣ እንዳይቆሽሽም የመቆጣጠር ኃላፊነትና ከአቅሙ በላይ ከሆነ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንዳለበት ከተዘረዘሩት ጥቂቶቹ ናቸው።
እነዚህን ህግጋት የማስፈፀምን ኃላፊነት በተመለከተ የጽዳት፣ ውበትና መናፈሻ ልማት ኤጀንሲው የተለያዩ ዝርዝር ሥልጣንና ተግባራት የተሰጠው ሲሆን ሌሎች አካላትም ለምሳሌ ደንብ የማስከበር አገልግሎት፣ መደበኛና ትራፊክ ፖሊስ፣ ክፍለ ከተሞች፣ ቀበሌ/ወረዳ አስተዳደሮች፣ ት/ቤቶች፣ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ መ/ቤቶች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት አንፃራዊ የሕግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ህግጋት ከወረቀት ያለፉ አለመሆናቸውን መረዳት ከባድ አይደለም።
የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ የመንገዶች ባለስልጣን እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በየዓመቱ ማስተካከያ እንደሚያደርጉ እና እንዳደረጉ ሲገልጹ ቢስተዋልም፣ ነዋሪዎቹ ግን ዘላቂ መፍትሄ እንዳልተሰጣቸው ሲናገሩ ይደመጣል።
ከስልጡንነት እና ከምቹነት ጋር ስትነሳ የምንሰማት አዲስ አበባ ከተማ በዚህ በኩል ድግሞ አሳፋሪ መገለጫ ይዛ መገኘቷ ለብዙ ትዝብት ይዳርጋል።