ግንቦት 17 ፣ 2014

ኢትዮጵያ የተቃወመችው የዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ዳግም የሊቀ መንበርነት ሹመት

City: Addis Ababaዜናወቅታዊ ጉዳዮች

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ጤና ድርጅት ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው 75ተኛው የዓለም ጤና ጉባኤ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለሁለተኛ ጊዜ ድርጅቱን እንዲመሩ ተመርጠዋል።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ኢትዮጵያ የተቃወመችው የዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ዳግም የሊቀ መንበርነት ሹመት
Camera Icon

Credit: Social Media

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ጤና ድርጅት ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው 75ተኛው የዓለም ጤና ጉባኤ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለሁለተኛ ጊዜ ድርጅቱን እንዲመሩ ተመርጠዋል። በስዊዘርላንድ ጄኔቭ በተካሄደው የምርጫ ስነ ስርዓት ላይ ከተሰጡ 160 ድምፆች 155ቱ የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን በድጋሜ መመረጥ ደግፈዋል። 

የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን መመረጥ ካልደገፉት 5 ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች። ከሚያዝያ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የመንግስታቱ ድርጅት አባል ሀገራት ለዓለም ጤና ድርጅት እጩ ሊቀ መንበሮችን እንዲያቀርቡ ሲጋበዙ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ በእዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ ባደረጉት ስብሰባ የወቅቱን ሊቀ መንበር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለሁለተኛ ዙር ምርጫ ብቸኛ እጩ እንደሆኑ ገልጾ ነበር።

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም እስከ ህዳር 2014 ዓ.ም. ድረስ በ28 ሀገራት በእጩነት ቀርበው ነበር። እንደ እጩነት ካቀርቧቸው ውስጥ 17ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ሲሆኑ የወቅቱን ሊቀ መንበር ለዳግም ስልጣን በማጨት ቦትስዋና፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ ከፍሪካ ሀገራት በቀዳሚነት ተቀምጠዋል። ይሁን እንጂ የተ.መ.ድ አባል ሀገራት እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ ከዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በስተቀር አዲስ እጩ ባለማስመዝገባቸው ዶ/ር ቴድሮስ ብቸኛ እጩ ሆነው ቀርበዋል።

በጄኔቭ በተደረገው ድምፅ አሰጣጥ ቦትስዋና የአፍሪካ ቀጠናን በመወከል ለሊቀ መንበሩ መመረጥ ድጋፍ እንሰጣለን በማለት አስተያየት ብትሰጥም በኢትዮጵያ ተወካይ ቦትስዋና አፍሪካን መወከል አትችልም በማለት ተሟግተዋል። ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከአፍሪካ የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ድጋፍ ቢያጡም በአብላጫ ድምፅ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የዓለም ጤና ድርጅትን እንዲመሩ ተመርጠው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።          

በጥር ወር 2014 ዓ.ም. የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የድርጅቱን መርህ ጥሰዋል በማለት ለዓለም ጤና ድርጅት የስራ አስፈፃሚ ቦርድ አቤቱታ አስገብቶ ነበር። 

ሚኒስቴሩ እንደገልፀው “የዓለም ጤና ድርጅት የሰራ አስፈፃሚ ቦርድ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር፤ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የድርጅቱን መርህን በመጣስ እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ ቦርዱ ምርመራ እንዲካሄድ በደብዳቤ ተጠይቋል” ሲል አስታውቋል። ይሁን እንጂ ከቀናት በኋላ ዶ/ር ቴድሮስ ለሁለተኛ ዙር ኃላፊነት እንዲታጩ ለመምከር የተሰበሰበው የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አመራር ቦርድ የኢትዮጵያ መንግሥት በድርጅቱ ሊቀ መንበር ላይ ያቀረበውን አቤቱታ ላለማየት በመወሰን በዛው እለት ዶ/ር ቴድሮስ እጩ እንዲሆኑ ተወስኗል።

በስራ አመራር ቦርዱ ስብሰባ ላይ ኬንያዊው የድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቢ ፓትሪክ አሞት “ጉዳዩ ውስብስብ፣ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው እና ከቦርዱ አሠራር ውጭ እንደሆነ” 34 አባላት ላሉት ቦርድ ገልፀው ጉዳዩን ከቦርዱ ይልቅ ሌላ የሚመለከተው አካል ቢመለከተው ይሻላል በማለት ያቀረቡትን ሃሳብ ቦርዱ ያለተቃውሞ ተቀብሎታል።

በዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ላይ ቅሬታ ያሰማችው ሌላኛዋ ሀገር ኤርትራ ናት። የኤርትራ የመረጃ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ህዳር 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በይፋዊ የትዊተር ገፃቸው “የዓለም ጤና ድርጅት ሊቀ መንበር በሚልየኖች ፊት ህግ እየጣሱ ነው፤ በተጨማሪም ግለሰቡ የኤርትራ መንግስትን በሀሰት ለመውቀስ የመንግስታቱ ድርጅት መድረኮችን ያለአግባብ መጠቀም አይችሉም” በማለት አስፍረዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ መንግስት ተደጋጋሚ ትችት የቀረበባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ ለተፈረጀው ህወሓት ያደሉ መረጃዎችን በአድሎኣዊነት ማሰራጨታቸው ነው። ከኤርትራ በኩል ለተሰነዘረባቸው ትችት ደግሞ የትግራይ ክልል በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ጦር ከበባ ውስጥ ሆና ረጅም ጊዜ እያሳለፈች ነው በማለት መግለፃቸው ዋነኛው ምክንያት ነበር።

በእዚሁ ዓመት ባለፈዉ ሚያዝያ ወር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው እንዳሰፈሩት “የህክምና ተቋም ሰዎች ታመው ገብተው እየታከሙ የህክምና ተቋሙ ምግብ ስለጨረሰ ዉጡ መባልን አስባችሁታል? በትግራይ ክልል 240 ታካሚዎች የገጠማቸው እውነታ ግን ይህ ነው” ብለው “የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መንግስታት ከበባውን እንድታቆሙ እንጠይቃለን” ብለዋል።

ሊቀ መንበሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ጤና ድርጅትን የመራ አፍሪካዊ ሆነው የተሾሙት ከአምስት ዓመታት በፊት ሲሆን በስልጣን ዘመናቸው እንደ ኢቦላ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ እና በተለያዩ ክፍለ ዓለማት በተፈጠሩ ቀውሶች እና ጦርነቶች የተጎዳውን የጤና ዘርፍ የመምራት ሀላፊነት አርፎባቸዋል። የዓለም ጤና ድርጅትን ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስትር እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅትን መምራት ከጀመሩበት ጊዜ በኋላ ከላይ የተጠቀሱ ወቀሳዎች ቢሰነዘሩም የ2020 የታይም መፅሄት ተፅዕኖ ፈጣሪ ዝርዝር ውስጥ መካተትን ጨምሮ ከሰባት የሚበልጡ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ እውቅናዎችን ማግኘት ችለዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ሁለተኛ ዙር የሊቀ መንበርነት ዘመናቸውን ከነሐሴ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በይፋ ይጀምራሉ።

አስተያየት