የዲያሊሲስ ህክምና ማግኛ ማዕከል በድሬደዋ ከተማ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊገነባ ነው፡፡ ጥር 10 ምሽት በራስ ሆቴል የድሬደዋ አስተዳደር የድሬደዋ ተወላጆችና ወዳጆችን በአንድ መአድ ያቀረበ እራት ተደገሰ፡፡ የእራት ፕሮገራሙም አላማ በድሬዳዋ አስተዳደር በመንግስት የጤና ተቋም የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን ያለመኖሩን በማስመልከት ነበር፡፡
‹‹ድሬ ትጣራለች›› በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የእራት ግብዣ የአስር ሺ ብር ዋጋ የነበረው ሲሆን ይህ ገንዘብም የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን ለመግዣነት ለማዋል ታስቦ ነው፡፡
ታዲያ በእለቱ የተለያዩ ተቋማት ስራ አስኪያጆች፣ የድሬደዋ ባለሀብቶች፣ በውጪ ሀገር የሚኖሩ የድሬደዋ ተወላጆች ታድመው ከእራቱ በተጨማሪ ሁሉም እንደአቅሙ የራሱን አስተዋፆ ሊያበረክት ቃል መግባት ተጀመረ፡፡ ከነዚህ መሀከል ናሽናል ሲሚንቶ አንድ የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን ለመግዛት ቃል ገባ፡፡ የተለያዩ ባለሀብቶችም ይህን የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን ለመግዛት ቃል ገብተው ነበር፡፡ የተለያዩ ባለሀብቶችም ይህን የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን በመከታተል ለመግዛት ቃል ገቡ፡፡
እነዚህ የኩላሊት ማጠቢያ ማሽኖች ከተገዙም በኋላ ህክምናውን መስጫ የራሱ ማዕከል በማስፈለጉ በድሬደዋ አስተዳደር ለናሽናል ሲሚንቶ ማዕከሉን በ90 ቀን ውስጥ ሰርቶ እንዲያስረክብ ጥሪ ተደረገለት፡፡ ከዛም ይህንን ማዕከል ለመገንባት በሳቢያን ጤና ጣቢያ ውስጥ ያለ ባዶ ቦታ ተመርጦ በድሬደዋ ከተማ ውስጥ የመጀመሪያው የኩላሊት ማጠቢያ ማዕከል ሊገነባ ጉዞው ተጀመረ፡፡
እ.ኤ.አ በ2017 በአለም አቀፍ ደረጃ 697 ሚሊዮን (ሁሉም አይነት) የኩላሊት ህመምተኞች ተመዝግበዋል፡፡ ይህም በአለም አቀፍ ደረጃ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች የበሽታዉን ስርጭት 9.1% ያደርሰዋል ሲሉ የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል ባለሞያ የሆኑት አቶ አቤል ሽፈራው ገልፀዋል፡፡ እንደ አቶ አቤል ገለፃ እ.ኤ.አ በ2017 በአለም አቀፍ ደረጃ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች ስር በሰደደ የኩላሊት በሽታ ሞተዋል፡፡
በ2018 እ.ኤ.አ በወጣው አለም አቀፍ የጤና መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ 6426 ሰዎች ስር በሰደደ የኩላሊት ህመም ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ይህም በጠቅላላው በሀገሪቱ ከሚከሰተው ሞት 1.5% ነው፡፡ በድሬደዋ አስተዳደር ከሆስፒታሎች የሚገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከ600 በላይ ሰዎች በአመት የኩላሊት እጥበት እንደሚያስፈልጋቸው አቶ አቤል ተናግረዋል፡፡
ወደ አምስት መቶ ሺ ነዋሪዎች የሚገኙባት የድሬደዋ ከተማ የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን በአንድ የማሪያም ወርቅ በሚባል የግል የህክምና ተቋም ብቻ መገኘቱ ታማሚዎችን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሊከታቸው ችሏል፡፡
በከተማዋ ውስጥ ከአስተዳደሩ አልፎ ለአጎራባች ክልሎችና ከጎረቤት ሀገር ለሚመጡ ተገልጋዮች ጭምር አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት (ዲያለሲስ) አገልግሎት መስጫ ማሽን አለመኖሩ ሌላው አሳሰቢ ችግር እንደሆነም ይነገራል፡፡
በናሽናል ሲሚንቶ የህዝብ ግንኙነትና የፋብሪካው ተወካይ አቶ ወንዱ ንጉሴ ፋብሪካቸው በመጀመሪያ የዲያሊሲስ ማሽን በአንድ ሚሊየን ብር ወጪ ለድሬደዋ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ መሆኑንና ከዚያም የቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ማዕከሉን ማስገንባት እንደ ጀመሩ ገልፀዋል፡፡
ይህ በድሬደዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገነባው የዲያሊሲስ ማዕከል የ5.5 ሚሊየን በጀት ተመድቦለታል፡፡
አቶ ወንዱ የዲያሊሲስ ማዕከሉን ከጤና ቢሮ ባገኘነው ምክር መሰረት የዲያሊሲስ ማዕከሎች ከጤና ተቋም ጋር አብሮ እንዲሆን ስለተጠቆምን የሳቢያን ጤና ጣቢያ ውስጥ ባለ ባዶ ቦታ ላይ ግንባታው መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ወንዱ ገለጻ በአሁኑ ሰዓት የመሰረት ስራው አልቆ መደርደር መጀመሩን ገልፀዋል፡፡ አቶ ወንዱ ‹‹ ይህን ስራ ከመጀመራችን በፊት ተሞክሮ መውሰድ ስለነበረብን ክልል 5 በመሄድ ጂግጂጋ የሚገኘውን የዲያሊሲስ ማዕከል ተሞክሮ በመውሰድ ከድሬደዋ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲመቻች አድርገን በመስራት ላይ እንገኛለን ›› ሲል ተናግሯል፡፡ ተሞክሮውን ለመውሰድ ከጤና ቢሮ፣ ከከንቲባ ቢሮ፣ ከዲያስፖራ ኤጀንሲና የናሽናል ሲሚንቶ ስራ አስፈፃሚ በጋራ በመሆን ተሞክሮውን ወደ ድሬደዋ እንዳመጡት ገልፀዋል፡፡
እንደ የዲያሊሲስ ማዕከሉ ኮንትራክተር አቶ አብዱሰላም ኡመር ገለጻ በድሬደዋ እየተገነባ የሚገኘው ማዕከል መፀዳጃ ቤቱን ሳይጨምር በ404 ካሬ ሜትር ላይ እንዳረፈ ገልፀው ከዚህ በፊት በጂግጂጋ የዲያሊሲስ ማዕከል ተሞክሮ እንደወሰዱ ተናግረዋል፡፡
የማዕከሉ ግንባታ እስካሁን 32 በመቶ ተጠናቋል፡፡ ኮንትራክተሩም ከተሰጠው 90 ቀናት 43ቱን እንዳገባደደ ይናገራል፡፡ እንደ አብዱሰላም ገለጻ ስራው እንዲጓተት ምክንያት ከሆኑት ችግሮች ውስጥ መጀመሪያ አስበውት የነበረው የእቃዎች ዋጋ እና አሁን ያለው ዋጋ ያለመመጣጠን እና ግብዓቶች በተፈለጉበት ጊዜ ያለመገኘት ናቸው፡፡
በድሬደዋ አስተዳደር በኮንስትራክሽን ቢሮ የግንባታና ቁጥጥር ባለሞያ እየሩሳሌም በየነ በድሬደዋ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የዲያሊሲስ ማዕከል የጥራት ተቆጣጣሪ ናቸው፡፡ ወ/ሮ እየሩሳሌም እንደሚሉት ይህ ስራ ለማጠናቀቅ 90 ቀናት የተሰጣቸው እንደሆነና ከመጋቢት 19 2014 ዓ.ም ጀምሮ ግንባታ የጀመሩ ሲሆን በሶስት ወራት ውስጥ ስራው መጠናቀቅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
እንደ ወ/ሮ እየሩሳሌም ገለፃ እስካሁን በታቀደለት ቀን ስራቸውን እያስኬዱ ቢገኙም ከዚህ በኋላ የግብዓት እጥረት ካላጋጠመ በስተቀር ስራውን በጊዜው እናስረክባለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ይህ የሚገነባው ማዕከል እስከ 10 ዓመት ምንም ዓይነት እድሳት ሳያስፈልገው እንደሚቆይም ተነግሯል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በድሬደዋ ከተማ የሚገኙ ባለሀብቶች የኩላሊት ማጠቢያ ማሽኑን የመግዛት ሂደቱን የጀመሩ ሲሆን ማዕከሉ እንደተጠናቀቀ እስከ 10 የሚሆኑ የዲያሊሲስ ማሽኖችንና የመታከሚያ ክፍሎች የመያዝ አቅም ይኖረዋል፡፡