ግንቦት 16 ፣ 2014

ለደሴ ወጣቶች በብድር ተሰጥቶ ያልተመለሰው 29 ሚሊየን ብር

City: Dessieኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮች

በደሴ ከተማ ውስጥ የሚገኙ 88 ኢንተርፕራይዞች የወሰዱትን የተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር መክፈል አልቻሉም።

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ለደሴ ወጣቶች በብድር ተሰጥቶ ያልተመለሰው 29 ሚሊየን ብር
Camera Icon

Credit: Social Media

በኢትዮጵያ ወጣቶች እየተጋፈጡ ያሉት አንዱና ዋነኛው ችግር ሥራ አጥነት ነው። በዓለም ባንክ በ2017 እ.ኤ.አ የታተመ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው ወደ 100 ሚሊዮን ከሚጠጋው የአገሪቱ ሕዝብ ከ70 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ከ30 ዓመት በታች ነው። 

በየዓመቱም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ሥራ ፍለጋን ይቀላቀላሉ። የኢትዮጵያ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን እንደገለፀው ሀገሪቱ የስራ እድል የመፍጠር አቅሟ በአመት አንድ ሚሊዮን ገደማ ነው።

ደሴ ከተማ ውስጥ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን ለይቶ ከመመዝገብ ጀምሮ ለተደራጁ ወጣቶች ብድር የሚያቀርቡት ተቋማት አሰራራቸው ችግር ያለበት ለመሆኑ ማሳያው ብዙ ነው። ለዚህም ነው ስራ ፈላጊዎች በምሬት ቅሬታቸውን የሚያሰሙት።

የደሴ ከተማ ነዋሪ የሆነው አንድነት አሰፋ የ26 ዓመት ወጣት ሲሆን በግሉ ተበድሮ መስራት ቢፈልግም እንዳልቻለ ገልጾልናል። “ከተማ አስተዳደሩ ለግለሰብ ማበደር ስለከለከለ በግሌ መስራት አልቻልኩም፤ ከሌሎች 5 ጓደኞቼ ጋር በማሕበር ብንደራጅም አሁንም ብድር ማግኘት አልቻልንም” ብሏል።

በደሴ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ያለው የስራ ፈላጊ ቁጥርና የሚፈጠረው የስራ እድል ባለመመጣጠኑ ምክንያት ስራ አጥነት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ለዚህ አንዱ ማሳያ የብድር  አቅርቦት ችግር ነው።

ቅድስት በላይ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ ስራ በመፈለግ ላይ የምትገኝ የ25 ዓመት ወጣት ናት። ከፌደራል እና ከክልል መንግስት ለደሴ ከተማ ወጣቶች ስራ እድል መፍጠሪያ ተብሎ የሚመጣው ብድር “ብዙ ጊዜ ለግለሰብ ባለሀብቶች ነው የሚሰጠው” ትላለች። ከሌሎች ሁለት ጓደኞቿ ጋር እንጀራ ጋግረው ለመሸጥ የብድር ጥያቄ ቢያቀርቡም “ከዚህ በፊት ብድር የወሰዱ ወጣቶች በአግባቡ መመለስ ባለመቻላቸው ላልተወሰነ ጊዜ ብድር ማበደር አቁመናል” የሚል መልስ ተሰጥቷቸው ብድር የሚጀመርበትን ቀን እየጠበቁ እንደሚገኙ ጨምራ ገልጻለች።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ ዋና ተግባሩ የስራ ፈላጊዎችን መረጃ መሰብሰብ፣ ብድር ማመቻቸት፣ ስራ እድል የተፈጠረላቸውን ወጣቶች መከታተል እና መደገፍ ነው። 

የብድር አቅርቦት ውስንነት ላይ ወጣቶች የሚያነሱትን ቅሬታ ለመምሪያው ምክትል ኃላፊ ለአቶ ምንይሻው በሪሁን አቅርበንላቸው ሲመልሱ "በወጣት ፈንድ ብድር ከ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ 51 ሚሊዮን ብር ማበደር ብንችልም እስከ አሁን ድረስ ሊመለስ የቻለው 22 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው። ቀጣይ ብድር ለተጠቃሚ ወጣቶች ለማቅረብ ያስችል ዘንድ ከተሰራጨው ብር 97% ያህሉ መመለስ አለበት" ብለዋል።

ዳንኤል መንገሻ የደሴ ከተማ ነዋሪ ሲሆን እሱም ስራ ፈላጊ ነው። “እኔና አምስት ጓደኞቼ በማህበር ተደራጅተን ከደሴ ከተማ የስራ እድል ፈጠራ መምሪያ ብድር ወስደን እንጀራ ጋግረን መሸጥ እየሰራንና እዳችንን በአግባቡ እየከፈልን ነበር። ነገር ግን በደሴ ጦርነት በነበረበት ወቅት ማሽኖቻችን ሰለተዘረፉና ስለወደሙብን ወደ ቀድሞ ስራችን እንድንመለስ አበዳሪ ተቋሙን ተጨማሪ ብድር እንዲሰጠን ጠይቀን እስከአሁን ምንም አይነት ምላሽ አላገኘንም" ብሏል።

በደሴና አካባቢው ተፈጥሮ የነበረው ግጭት የበርካቶችን ህይወት ጎድቷል። ግለሰቦች እና ተቋማት ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባቸዋል ይላሉ አቶ ምንይሻው። በወረራ ምክንያት ንብረታቸው የተዘረፈባቸውን ኢንተርፕራይዞች በተመለከተ ሲገልጹ "ከፖሊስ ጽ/ቤት እና ከገቢዎች ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ንብረት የጠፋበት በገቢዎች ቢሮ የተረጋገጠ ህጋዊ የግዥ ደረሰኝ ማቅረብ ከቻለና ፖሊስ ጽ/ቤት ማረጋገጫ ከሰጠን መምሪያችን ድጋፍ እያደረገለት ብድሩን እንዲመልስ ይደረጋል" ብለዋል።

በደሴ 3600 ኢንተርፕራይዞች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ 200 ያህሉ ኢንተርፕራይዞች በቅርቡ በደሴ ከተማ በተፈጠረው ግጭት ተዘርፈዋል ይባላል። በዚህም የተነሳ 88 ኢንተርፕራይዞች ብድር መክፈል አልቻሉም።

አቶ ምንይሻው ተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር ምን እንደሆነ ያለመረዳት ችግርም አለ ይላሉ። “ከዚህ ቀደም ብድር የወሰዱ አብዛኞቹ ግለሰቦች እየከፈሉ አለመሆኑን አረጋግጠናል፣ ገንዘቡን ለሌላ ዓላማ አውለውታል” በማለት አብዛኞቹ ተበዳሪዎች ብድራቸውን መክፈል ያልቻሉበትን ምክንያት አብራርተዋል።

“ኢንተርፕራይዞቹ በቅርቡ በተፈጠረው ግጭት ተጠቅመው ብድር ላለመክፈል እየሞከሩ ነው። ነገር ግን የሌሎች ወጣቶችን ስራ እየዘጉ መሆኑን ማወቅ አለባቸው። እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ሲል ምንይሻው ተናግሯል።

ተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር ማለት እድሜያቸው ከ18 እና 34 ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች በማህበር በመደራጀት የንብረት ዋስትና ማስያዝ ሳያስፈልጋቸው እርስ በእርሳቸው ዋስ በመሆን የሚወስዱት ብድር ነው። የብድሩ ዋና አላማ  በሀገራችን ከጠቅላላው ህዝብ ቁጥራቸው 70 ከመቶ የሚሆኑትን ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ማስቻል ነው።

አስተያየት