ኅዳር 20 ፣ 2014

ለዩቲዩብ ተብለው የሚሰሩ የኢትዮጵያ ፊልሞች ዘርፉ ላይ የፈጠሩት ተጽእኖ

City: Addis Ababaመዝናኛየጥበብ ዐውድፊልም

በኢትዮጵያ ደረጃ የፊልም ዘርፉ ላይ የደረሰው ጫና ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ያነሳሉ።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ለዩቲዩብ ተብለው የሚሰሩ የኢትዮጵያ ፊልሞች ዘርፉ ላይ የፈጠሩት ተጽእኖ

የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ እና ወረርሺኙን ተከትለው የተወሰዱ እርምጃዎች በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ምስቅልቅል ፈጥሯል። በወረርሺኙ ክፉኛ ከተጎዱ ዘርፎች መካከል የንግድ ሰንሰለት፣ የቱሪዝም ገበያ፣ የአየር መንገድ ዘርፍ በጥቅሉ የምጣኔ ሀብት ላይ እንደየሀገራቱ የመቋቋም ደረጃ ጉዳቶችን እያደረሰ ይገኛል።

እነዚህ ዘርፎች እንደተጠበቁ ሆነው በኢትዮጵያ ደረጃ የፊልም ዘርፉ ላይ የደረሰው ጫና ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ያነሳሉ። የፊልም ዘርፋቸው ያደገ፤ የተመነደገ የሚባሉት ሀገራትም ቢሆን ከገፈቱ በጥቂቱ ቢቀምሱም፤ የፊልም ዘርፋቸውን ወደ ዲጂታል ሲኒማ ለማስገባት ከኮሮና ቫይረስ በፊትም እርምጃ ላይ የነበሩና እንደ አሜሪካ ያሉ በዘርፉ ስማቸው የገነኑ ሀገራት ደግሞ ከሲኒማ ባልተናነሰ ደረጃ የዲጂታል ማሳያዎችን መተግበር ከጀመሩ የሰነባበቱ በመሆኑ መሰናክሎች አልበዙባቸዉም።

ኢትዮጵያ ወረርሺኙ ከተከሰተባት ጀምሮ የህዝብ መሰባሰቦችን ለመቀነስ የተወሰደው እርምጃ በቀዳሚነት የጎዳው፤ ለኢትዮጵያ የፊልም ዘርፍ መደበኛ የመሸጫ መንገድ ሆነዉ ለዓመታት የዘለቁትን ሲኒማ ቤቶች ነው። በእዚህ ጊዜ ነበር የፊልም ሙያተኞች ለህልውናቸው ሲሉ እንደዩቲዩብ ያሉ የኦንላይን ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ተገደዋል።

ምናልባትም በህብረተሰቡ ዘንድ አሁን ላይ የተዋናዮች ድርሻና ብቃት በሁለት ተከፍሎ የሲኒማ ተዋናዮች እና የዩቲዩብ ተዋናዮች ተብሎ እስከመሰየም ደርሰዋል።

ሶደሬ ቲቪ፣ ነጸብራቅ ቲቪ፣ አራዳ ፊልሞች፣ ድሬ ቲዩብ በስፋት የአማርኛ ፊልሞችን በቪድዮ መረብ ላይ ከሚያሰራጩ የዩቲዩብ መድረኮች ጥቂቶቹ ናቸው። አዲስ ዘይቤ ከወረርሺኙ በኋላ እየተለመደ የመጣዉን ይህን አሰራር በተመለከተ ከፊልም ዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርጋለች።

የባለሙያዎች እይታ

የፊልም ዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ከሲኒማ ደረጃ የወረደው ፊልም በይዘቱም፣ በጥራቱም ሆነ ለባለሙያዎች ከሚኖረው ጥቅም አንጻር በዩቲዩብ የሚጫኑት ፊልሞች ሙያዉንም ባለሙያዉንም ተጠቃሚ እያደረጉ አይደለም።

የፊልም ተመልካቾችም ቢሆኑ ይህን ችግር ተገንዝበው ይመስላል “የዩቲዩብ አክተሮች እና የሲኒማ አክተሮች” እያሉ ባለሙያዎችን ሲሰይሙ፤ አልፎ አልፎም ሲተቹ ይስተዋላል። በእዚህ የሚስማሙ የዘርፉ ባለሙያዎችም ጥቂት አይደሉም።

ጌትሽ መስፍን የሐበሻ ትሪል ኢንተርቴንመንት መስራችና የፕሮዳክሽን ባለሙያ ነው። ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በተከሰተበት ጊዜ ከደራሲ እስከ ተዋናይ፤ ከቀረጻ ቦታ ባለሙያዎች እስከ ፕሮዳክሽን ባለሙያዎች ድረስ ሁሉም የፊልም ሙያተኞች በሚባል ደረጃ ችግር ውስጥ የገቡበት ጊዜ እንደሆነ ያስታውሳል።

ህዝባዊ መሰባሰቦችን ለመቀነስ የተወሰዱት እርምጃዎች ሲኒማ ቤቶች ረጭ አድርገው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሀገርኛ ፊልሞች በዲጂታል አዉታሮች እና መተግበሪያዎች እንዲጫኑ እድል መፍጠሩ ግልጽ ቢሆንም ክፍተቶቹ ብዙ ናቸው።

በመሰባሰብ እገዳዎች የተነሳ በፊልሙ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ዘርፎች ህብረተሰቡ በቤቱ ተቀምጦ የሚዝናናባቸው አማራጮች በማህበራዊ ትስስር አዉታሮች እና በእጅ ስልኮች አማካይነት መለመዳቸው ዓለም አቀፍ እውነታ ነው።

ፍሬዘር ተሾመ የፊልም ፕሮዲዩሰር እና ፕሮሞተር በመሆን በዘርፉ ከ10 ዓመታት በላይ ቆይቷል። ከ2003 ዓ.ም. በኋላ ብቻ እንደ ረቡኒ እና ላምባ የመሳሰሉ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያገኙ ፊልሞችን ጨምሮ ከ28 የሚበልጡ የፊልም ስራዎችን ከ80 በላይ በሆኑ የተለያዩ ከተማዎች ተንቀሳቅሶ በፕሮሞተርነት ለማሳየት ችሏል።

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በኋላ የተለመዱት ፊልሞችን ገዝተው በዩቲዩብ ቻናላቸው አማካይነት የሚጭኑ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሙያዉን ከማሳደግ ይልቅ የራሳቸውን ሳንቲም መሰብሰብ ላይ ያተኮሩ መሆናቸው የፊልም ዘርፉን እንደጎዳው ታዝቧል።

ተዋናይ እና የተውኔት ባለሙያ ቸርነት ነጋሽ እንደሚገልጹት ደግሞ ወረርሺኙ የባለሙያውንም የተመልካቹንም እንቅስቃሴ የገደበ ስለነበር የዩቲዩብ ገጾቹ ለሁለቱም ጥሩ አማራጭ ሆነው ብቅ ብለዋል።

ወረርሺኙን ተከትለው የተወሰዱ ክልከላዎች ከተነሱ በኋላም ቢሆን ወደ ሲኒማ የሚገባውን የተመልካች ቁጥር ቀንሶታል። ይህ ደግሞ የፊልም ዘርፉ ላይ በተለይም ዲጂታል ሲኒማ ባልተለመደባት ኢትዮጵያ ጉዳቱ የባሰ እንደሆነ ቸርነት ነጋሽ ይገልጻሉ። ይህን ታሳቢ በማድረግ ቸርነት ነጋሽ ከእነክፍተቶቻቸውም ቢሆን የዩቲዩብ ቻናሎች ጅማሪ መበረታታት አለበት ባይ ናቸው።

ክፍተቱ የት ነው ያለው?

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በዩቲዩብ ቻናሎቻቸው ላይ ፊልሞችን ለመጫን የሚገዙት የቻናል ባለቤቶች (ዩቲዩበር) ለፊልሞች የሚያቀርቡት ክፍያ በፍጹም ፊልሞችንም ሆነ ባለሙያዎቹን የማይመጥኑ ናቸው። ፊልም ለመስራት የሚያስፈልጉ ሂደቶችንም ባልተከተለ መልኩ የለብ ለብ የሚሰሩት ስራዎች ችግር ሆነዋል። በባለሙያዎቹ ምልከታ የኢትዮጵያ የፊልም ተመልካች አመለካከቱ እና ፊልሞችን የሚመዝንበት ደረጃ እያደገ በመምጣቱ በርካታ ታዳሚዎች ይህን ታዝበዋል።

ፍሬዘር ተሾመ እንደባለሙያ የታዘባቸዉን ሲያጋራን ባለሙያዎች ለሲኒማም ሆነ ለዩቲዩብ ብለው የሚሰሯቸው ፊልሞች የሚገዙበት ብር እጅግ አናሳ ነው። “ዩቲዩበሮች ለአንድ ፊልም የሚመድቡት በጀት በሲኒማ ስታንዳርድ ለአንድ ተዋናይ የማይከፈል ነው፤ ይህም በዛ ቢባል ከ80 ሺህ እስከ 150 ሺህ ድርስ የሚሆን ማለት ነው።” ሲል ፍሬዘር ይገልጻል።

እንደ ጌትሽ መስፍን እይታ ደግሞ “ፊልሞችን ፕሮዲዩስ የሚያደርጉት ሰዎች በብዛት እንደቢዝነስ የሚመለከቱት እና በትንሽ ወጪ ብዙ ትርፍ ለማግኘት መስራታቸዉ እነሱን ተጠቃሚ፤ ባለሙያውን እና ዘርፉን ደግሞ የጎዳ” መሆኑን ይናገራል።

በይዘትስ ፊልሞችን ምን ያህል ጎድቷቸዋል?

የዩቲዩብ ቻናል ባለቤቶች የፊልሞችን ዋጋ መተምንንም ራሳቸው የሚሰሩ መሆናቸው የተሻሉ ስራዎች መጥተው በዝቅተኛ ዋጋ የሚገዙበትን ሁኔታ እንደፈጠረ የገለጸልን የተውኔት ባለሙያው ቸርነት ነጋሽ ነው። ጥራት ያላቸው ስራቸው ምንጊዜም ከፍ ያለ ወጪና ልፋት የሚጠይቁ ናቸው ያለው ባለሙያው “ለቆንጆ ስራ ቆንጆ ክፍያ የሚሰጡ ከሆነ ሙያተኛው የተሻለ ስራ ይዞ ይመጣል።” ብለዋል። የዩቲዩብ ገጽ ባለቤቶች ይህን ካደረጉ የተሻለ ፉክክር ውስጥ የሚገቡና የተሻሉ ስራዎችን ማስመልከት እንደሚችሉ ቸርነት ይመክራል።

ባለሙያዎቹ በሰጡት አስተያየት የፊልም ዘርፍ ባለሙያዎች ፊልሞችን ሲሰሩ ጊዜያቸዉን እና ገንዘባቸዉን ሳይሰስቱ የፊልሙ የሚያጠነጥንበት ጭብጥ የሚገባዉን በሙሉ ለማድረግ መጣር ሙያዊ ግዴታቸው ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ፊልሞቹን የሚገዙት አካላት የገንዘብ ጉዳይ እንጂ ለሙያው ያን ያህል ትኩረት አለመስጠታቸው ዋነኛው ክፍተት ነው።

በሀበሻ ትሪል ኢንተርቴይመንትም በመሰባሰብ እገዳዎቹ ወቅት በሲኒማ ቤቶች ለማሳየት አቅደዉ የሰሩት ፊልም ለፊልሙ ያወጡትን ወጪ እንኳን መመልስ ባልቻለ ገንዘብ በዩቲዩብ ለመጫን መገደዳቸዉን ፕሮዲዩሰሩ ጌትሽ መስፍን ይናገራል። “እንደባለሙያ ስመለከተው ይህ አዲስ አሰራር ትርፉ ድካም እና የፊልም ዘርፉን ማበላሸት ነው። ትንሽ ነገር ለማግኘት ብዙ ነገር እያጣን ነው።” ብሎ እንደሚያስብም ገልጾልናል።

የዲጂታል ሲኒማ መተግበሪያዎችስ በምን ይለያሉ?

የአማርኛ ፊልሞችን በክፍያ አማራጭ በመተግበሪያዎች የማቅረብ ጅማሪዎች ይታያሉ። በባለሙያዎች እይታ እዚህ ላይም ዩቲዩቦች ጫና ፈጥረዋል። የዩቲዩብ ቻናሎች ከሚሰጡት አነስተኛ ክፍያ ባለፈ ክፍያዉን ለመፈጸም በተቆራረጠ መልኩ የሚከፍሉ መሆኑም የሙያተኛውን ተነሳሽነት እየጎዳ ይገኛል። ፊልሞች ወደ ዩቲዩብ እንዲሄዱ ያደረገው ዋነኛ ሰበብ የዲጂታል ሲኒማ አለመለመድ መሆኑ ባለሙያዎቹን ያስማማል። በጥቅሉ ሲታይ የዲጂታል ዘመን እንደመሆኑ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው።

ፍሬዘር ከእዚህ ቀደም ፊልም ሰርተው በዩቲዮቦች ምክንያት በመክሰራቸው ከባልደረቦቹ ጋር ‘ጎፍሊክ’ የተሰኘ የኦንላይን ሲኒማ መጀመራቸውን ነግሮናል። እንደ ፍሪዘር ተሾመ ገለጻ የዲጂታል ሲኒማ መተግበሪያዎች በዓለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ምቹ የክፍያ ዘዴዎች የመጡ ናቸው። በተጨማሪም “መተግበሪያዎቹ 80 በመቶ የፊልም ባለሙያዎችን 20 በመቶ ደግሞ መተግበሪያዎቹን ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው።” ብሏል። ተመልካቾች ለፊልሞቹ የሚከፍሉት በፊልሙ ጥራት፣ ወጪ የተደረገበት ገንዘብ እንዲሁም በሲኒማ ያገኙት ተመልካችን መሰረት በማድረግ መሆኑ አበረታች ነው።

ፊልሞች ሲኒማ ቤት ታይተው ሲጨርሱ አልያም ከሲኒማ ቤቶች ጎን ለጎን የሚታዩበት አማራጭ መሆኑ የተሻለ ያደርጋቸዋል።

ቀጣይ የመፍትሄ ሐሳቦች ምን መሆን አለባቸው?

እንደሀገር ፊልሞችን በባለሙያ እይታ የሚመዝን ተቋም ወይም ማህበር ያስፈልጋል የሚለዉ ጌትሽ መስፍን የዩቲዩብ ቻናል ባለቤቶች ፊልሞችን ሲቀበሉ ቀረጻቸዉን፣ ይዘታቸውን እና ድካማቸዉን የሚመጥን ክፍያ ማሰብ አስፈላጊ ነው ይላል።

ፍሬዘር ተሾመ በበኩሉ “በእኔ እይታ ፊልሞች ሲኒማ እና ኦንላይን መደቦች ላይ ታይተው ባለሙያዎች ማግኘት ያለባቸዉን ጥቅምና ክብር ካገኙ በኋላ ዩቲዩብ ላይ ቢጫኑ ለተመልካቾች አማራጭ ስለሚሆን የተሻለ መንገድ ነው።” ብሏል። አክሎም የባለሙያውን ጥቅም የሚያስከብሩ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው ያለው ፍሬዘር “ተመልካቹ ፊልም ያውቃል፤ ባለሙያው ፊልም ተመልካቹን ያክብር፤ ተመልካቹም ሙያተኛዉን ያክብር” ይላል።

ዩቲዩቦች የመጀመሪያ መታያ መሆን ካለባቸው የተሻለ ጥራትና በጀት መድበው የተሻለ ተመልካች ማግኘት ሌላኛው የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ዘመኑ የዲጂታል በመሆኑ የተወሰኑ ነገሮችን ማስተካከል ከቻሉ ዩቲዩቦችም እንደአማራጭ ቢቀጥሉ መልካም ነው የሚሉት ተዋናይ ቸርነት “ፊልሞችን የሚገዙ ባለዩቲዩብ ቻናሎች ተገቢዉን ክፍያ መክፈል ከቻሉ ሙያዉን የማያሳድጉበት ምክንያት አይኖርም” ሲሉም ይሞግታሉ።

የዲጂታል ሲኒማን ማበረታት እና የዩቲዩብ ቻናሎች ሙያውን የሚመጥን አሰራር ከተከተሉ ሙያውን በጋራ ማሳደግ ይቻላል የሚለው የባለሙያዎቹ መልእክት ነው።

አስተያየት