ኅዳር 18 ፣ 2014

እግረኞችን ያማረረው የመንገድ ላይ ንግድ

City: Dire Dawaኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮች

የጎዳና ላይ ንግድ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር በሚበዛባቸው አካባቢ እና ሰዎች ትራንስፖርት በሚይዙበትና በሚቀይሩበት ቦታ ላይ በይበልጥ ይከናወናል።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

እግረኞችን ያማረረው የመንገድ ላይ ንግድ

ግርግር የሚበዛባቸው የድሬዳዋ ጎዳናዎች በእግረኛ መንገዶች መጨናነቅ የጀመሩት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ። ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ የነበራት የትራፊክ ፖሊስ ዓለም ብዙነህ የመንገድ አጠቃቀም ችግሮች በስፋት እንዳስተዋለች ትናገራለች። “የእግረኛ መንገዶች የታቀደላቸውን ዓላማ ከማስፈጸም ይልቅ መነገጃ ሆነዋል” የምትለው ትራፊኳ የመንገድ ዳር ሱቆች ሸቀጦቻቸውን የእግረኛ መንገድ ላይ በሸራ ዘርግተው መሸጣቸው እግረኞች በመኪና መንገድ ላይ እንዲጓዙ ስለማስገደዱ ታብራራለች።

ያነጋገርናቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች እንደሚስማሙበት ሕገ-ወጦቹ ነጋዴዎች ከነዋሪው ቁጥር ጋር የማይመጣጠነውን ጠባብ መንገድ ይበልጥ የማጥበብ ተግባራቸው የትራፊክ ፍሰቱን ከማደናቀፉም በተጨማሪ ለትራፊክ አደጋ ምክንያት ሆኗል። ለመንገድ ላይ ንጥቂያም የራሱ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የጎዳና ላይ ንግድ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር በሚበዛባቸው አካባቢ እና ሰዎች ትራንስፖርት በሚይዙበትና በሚቀይሩበት ቦታ ላይ በይበልጥ ይከናወናል። በተለይ ሰኢዶ፣ አሸዋ፣ ሼል፣ ገንደቆሬ፣ መልካ፣ ኮኔል፣ ደቻቱ፣ ቀፊራ፣ ሳቢያን መስቀለኛ አካባቢ በስፋት ችግሩ የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ናቸው። በተለይ አመሻሽ ላይ የእግረኛ መንገዶች የሚጨናነቁ ሲሆን እግረኞችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው።

በሳቢያን ሰኢዶ አካባቢ ሸራ ወጥረው ጫማ በመሸጥ ኑሯቸውን መግፋት ከጀመሩ አራት ዓመት እንደሆናቸው የሚናገሩት አቶ አስፋው በላይ ይባላሉ። አቶ አስፋው በዚህ ስራ መተዳደር ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ የንግድ ፈቃድ አውጥተው ሕጋዊ አሰራርን ባለመከተላቸው ሕግ አስከባሪዎች ሸቀጦቻቸውን እንደሚወስዱባቸው ተናግረዋል። መንግሥት አነስተኛ ነጋዴዎችን የሚያበረታታ አሰራር ቢዘረጋ ችግራቸው ሊቀረፍ እንደሚችልም ያምናሉ። እንደ አቶ አስፋው እምነት በአሁን ሰዓት መንግሥት እየተከተለው የሚገኘው የግብይት ስርአት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች አያማክልም። ይህ መሆኑ ደግሞ ነጋዴዎቹ ሕጋዊ ያልሆነውን አማራጭ እንዲወስዱ ያስገድዳቸዋል።

የመንገድ ዳሩ ንግድ አመቺ ያልሆነና ለአደጋ የሚያጋልጥ ስለሆነ ወደፊት ወጥ በሆነ የንግድ ስርአት ውስጥ በመሰማራት የተሻለ ስራ መስራት እንደሚፈልግም አቶ አስፋው አክለው ገልፀዋል።  

አቶ ሳሊም ኢብራሂም ከእህታቸው ጋር በመሆን ሳቢያን አካባቢ መንገድ ዳር ሸራ ወጥረው በመሸጥ ይተዳደራሉ። በሥራው አራት ዓመታትን ያስቆጠሩት አቶ ሳሊም መንግሥት ቅያሪ ቦታ ቢያመቻችላቸው ወይም ወደ ሕጋዊ መንገድ የሚገቡበትን ሁኔታ ቢያመቻች ችግሩ ሊቀረፍ እንደሚችል ያስባሉ።

የሸቀጣ ሸቀጥ እና የአትክልት መሸጫ መደብር ያላቸው ነጋዴዎችም ከሱቃቸው ፊትለፊት ያለውን የእግረኛ መንገድ ዘግተው እቃቸውን ይዘረጋሉ። ሕገ-ወጦቹ ነጋዴዎች ሸቀጣቸውን በግልጽ በሚታየው የእግረኛ መንገድ ላይ ስለሚያስቀምጡ ሱቅ ገብቶ የሚገዛውን ደንበኛ እንደሚቀንስባቸው የሚናገሩት ነጋዴዎቹ “መንግሥት ሕጋዊዎቹን የሚጠብቅበት አሰራር ስላልዘረጋ ከሕገወጦቹ ጋር እየተጋፋን በመስራት ላይ ነን” ይላሉ።

ማንኛውም ሰው በፈለገው የንግድ መስክ ተሰማርቶ ንግድን ለማካሄድ እንደሚችል የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 41(1) (2) በግልፅ ይደነግጋል። በሕገ-መንግሥቱም ሆነ በሌሎች ሕጎች ዕንደሚታየው እነዚህ መብቶች ያለገደብ የተሰጡ አይደሉም። ለህዝብ ጥቅም ሲባል አንዳንድ መብቶች ሊገደቡ ይችላሉ። በፈለጉት መስክ በንግድ የመተዳደር መብትም አስገዳጅ ገደቦች (compulsory restraints) አሉበት። ነገር ግን እነዚህ ሕጎች እንደሌሎቹ በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጡ ሳይሆን በከተማዎች መስተዳደራዊ ሕግ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። በድሬደዋ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ አቶ ሱራፌል ጌታሁን እንደ ድሬደዋ በሕገ-ወጥ ንግድ ዙሪያ የወጣ ሕግ ወይም አዋጅ የለም ይላሉ። ይህንን የሕገ-ወጥ የመንገድ ላይ ንግድ ለመቆጣጠር በከተማ አስተዳደር የወጣውን መመሪያ ጥቅም ላይ እንደሚውል ገልጾአል።

መመሪያው ሕገ-ወጥ የመንገድ ዳር ግንባታዎችን ጨምሮ፣ ለመንግሥት ግብር ሳይከፍሉ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩና ያለአግባብ ሱቃቸውን የእግረኛ መንገዶች እንዲያጨናንቅ የሚያደርጉትን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው። እንደ አቶ ሱራፌል ገለፃ ሁሉም የሚያውቀውና የሚረዳው በአዋጅ የሚጠቀስ ደንብ ቢኖረው ይህ የሕገ-ወጥ ንግድ ይቀንሳል።

በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ባለሙያ የሆነው መስፍን ግዛው እግረኞችን ለትራፊክ አደጋ እያጋለጠ የሚገኘው የመንገድ ላይ ንግድ ብቻ ሳይሆን በእግረኛ እና በተሽከርካሪ መተላለፊያዎች ላይ በዘፈቀደ የሚቀመጡ የግንባታ እቃዎችም ስለመሆናቸው ነግረውናል።

አስተያየት