የቅርብ ወዳጃቸዉ የኩላሊት ጤና እክል አጋጠሟቸው ወደ ሀኪም ቤት በመሄድ ለሁለት ሳምንታት የዲያሊሲስ ሀክምና እያደርጉና ታካሚዉ የህክምና ወጫችዉን በግላቸዉ እየሸፈኑ እንደሚገኙ የጠቀሱ አንድ ግለሰብ የቅርብ ቤተሰባቸውን ዲያሊስስ ሲያደርጉ የሚያሳይ ፎቶ በባነር የለጠፈ ሚኒባስ "እኔ ነኝ ደራሽ ለወገኔ" በሚል ሙዚቃ ታጅቦ በመሀል መገናኛ ምፅዋት ሲጠይቅ ተመልክተዉ የሀዘንና የንዴት ሰሜት እንደፈጠረባቸዉ አጫዉተዉኛል ሲል አንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ በቅርቡ በፌስቡክ ገጹ ላይ አጋራ።
ጸሀፊዉ ጥቆማውን ያደረሱት ግለሰብ በራሱ ወጪ እየታከመ ያለን ሰው ያለ እርሱ እውቅና ፎቶውን በድብቅ በማንሳት ለግላቸው ገቢ ማግኛ ሲለምኑበት በማየታቸዉ መሀል መንገድ ላይ መኪናቸውን አቁመው ወደ ምፅዋት ጠያቂው ሚኒባስ በመሄድ አሽከርካሪውን በሚያናግሩበት ወቅት መኪና ውስጥ ከሌሎች ተባባሪዎች ጋር ጫት እየቃሙ እንደነበር እና ለፀብም እንደተጋበዙባቸው በመጨረሻም በአቅራቢያው ፖሊሶች ስለነበሩ በቁጥጥር ስር ሊውሉ መቻላቸውን እንዳጫወቱትም ይገልፁና “ይህም በትክክል እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ምንዱባኖች ላይ የለጋሾችን እጅ የሚያሳጥር እና ጥርጣሬን የሚያጭር ቢሆንም ነገር ግን ህብረተሰቡ ከእነዚህ እንክርዳዶች እንዲጠነቀቅ ይሁን” ሲል መልእክቱን አስፍሯል።
ከቅርብ አመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ታካሚዎችም ያላቸውን ሃብት እና ጥሪት አሟጠዉ ሲጨርሱ በህይወት ለመኖር ከሃገር ወጥቶ መታከም ግድ ሲሆንባቸው እና በሽታው ጊዜ የማይሰጥ ሲሆን የህክምና ወጭ ለመሸፈን የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት የተለያዩ መንገዶችን ይፈልጋሉ። ታማሚዎች ህክምናችዉን በሀገር ዉስጥ ሆስፒታሎች ወይንም ወደ ተለያዩ ሃገራት ሄዶ ለመታከም በከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ በየጎዳናዉ የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰብ ግድ ሆኖባቸዉ ይስተዋል። በዚህ ተለምዷዊ የህክምና ገንዘብ አሰባሰባ ሂደት ያለፉ በርካቶች ህክምናቸዉን ተከታትለዉ ድነው ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል።
ይሁን እንጂ ይህ የጎዳና ላይ የህክምና እርዳታ አሰባሰብ ወጥ የሆነ አሰራር ስላልተዘረጋለት እና ድርጊቱን የሚቆጣጠር የመንግስት አሰራር አለመኖሩ ከላይ እንደተገለፀው ላለ የህገወጥ ድርጊት በር እየከፈተ እንደሚገኝ በተለያየ መንገድ ሲጠቀስ ቆይቷል።
ይህ ወገንን የመርዳት ተግባር የሚበረታታ ሆኖ ሳለ ይህንን ለተቸገሩ (የህክምና ገንዘብ ላጡ) እንደ አፋጣኝ የገንዘብ ማሰባሰብያ እርዳታ የሚያገለግለውን ወገንን የማዳን ተግባር ላልተገባ እና ለራሳቸው ጥቅም የሚያውሉት እና ህብረተሰቡ ይህን አማራጭ እንደ ገንዘብ ምንጭ እና እንደ ዋና ስራቸው የያዙት ሰዎች መኖራቸው መሰማት ከጀመረ ሠነባብቱዋል ብለዋል። በዚህም ምክንያት በተለይ ከተማችን አዲስ አበባ ሰዎች በሚሰባሰቡባቸዉ እና የንግድ ተግባሮች በሚከናወኑበት ቦታዎች ላይ ይህንን የመኪና ላይ ገንዘብ የመሰብሰብ ተግባር በብዛት እና በተደጋጋሚ ማየት የተለመደ ነው።
አዲስ ዘይቤ ጉዳዩን በተመለከተ ባደረገችዉ ዳሰሳ እንዲሁም ብዙ ሰዎች ካጋጠማቸውና በአይናቸውም ካዩት በመነሳት ያገኘናቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት በመዲናችን በብዛት ይህ የማጭበርበር ስራ ተስፋፍቶ እንዳለ እና ብዙ ሰዎች እንደተጭበረበሩ ተረድታለች።
የተሳሳተ የህክምና ማስረጃ በመያዝ ፣ መኪና ተከራይተው ፣ ያልታመመን ሰው መኪናው ውስጥ በማስተኛት የሃሰት የበሽታ ታሪክ ፈጥሮ ድምጻቸው ከፍተኛ በሆኑ የድምጽ ማጉያዎች ሃሰተኛ የህክምና ታሪኮችን በመተረክ ፣ ልብ የሚነኩ በመሳሪያ የተቀነባበሩ ዘፈኖችን በከፍተኛ የሚረብሽ ድምጽ እና የመኪና መንገድ ዘግቶ እና አጨናንቆ በመቆም ለዚህ ሃሰተኛ ተግባር የተደራጁትን አባሎቻቸውን በእግረኛ መንገድ ላይ ታማሚ ነው ያሉትን ሰው ፎቶ በቲሸርት ላይ አሰርተው እና የብር መሰብሰቢያ ካርቶኖቻቸውን ይዘው ብር ሲቀበሉ ይስተዋላል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም አንዳንድ የታክሲ ባለቤቶች መኪናቸውን በማቅረብ ከተሰበሰበው ብር ላይ በፐርሰንት ድርሻ በመደራደር ስራውን በስፋት እየሰሩት እንዳለም አዲስ ዘይቤ ተረድታለች። ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው ብዙ እውነተኛ ታማሚዎች በዚህ ገንዘብ የማሰባሰቢያ ሂደት ታክመው ወደ ሃገራቸው የተመለሱ መሆኑን የሚታወቅ ቢሆንም አሁን ላይ እንደ አንድ የስራ ዘርፍ እየታየ እና ህብረተሰቡ በከፍተኛ ሁኔታ ትክክለኛውን ታማሚ እና እውነተኛ የተቸገረውን ለመለየት ስላቃተው ሁሉንም በአንድ የመፈረጅ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ይህ ተግባር ህብረተሰቡን ከማጭበርበር ባለፈም በመንገድ መጨናነቅ እና ከፍተኛ የድምጽ ብክለት በማስከተል ደረጃም ከባድ ችግር ሆኖ ስሞታዎች ሲቀረብበት ይስተዋላል።
በዚህ የመንገድ ላይ የህክምና እርዳታ አሰባሰብ ዙርያ ያናገርናቸው የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ከሆኑት ከአቶ ብርሃኑ ኩማ መንገድ ላይ ለሚስተዋሉ መጨናነቆች እና ከፍተኛ ድምጾች ለመቆጣጠር ሲባል ከዚህ በፊት ላይ ፍቃድ እንዳላቸው እንደሚጠይቁ እና ህጉም ፍቃድ ሳይኖራቸው መንገዱን ማጨናነቅ እና የድምጽ ብክለት መፍጠር ገልጸዉ አሁን ላይ ይህ ፍቃድ የመጠየቅ ተግባር ግን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ እንደቆመ የትኛውንም የመንገድ ላይ የድምጾች ብክለት በመፈጥር መልኩም ሆነ የመኪና መንገዶችን አጨናንቀው ለሚደረጉ የህክምና እርዳታ ማሰባሰቢያዎች ምንም አይነት ፈቃድ እንደማይጠይቁ ያስረዳሉ።
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማነጅመንት ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ቢኒያም ለእርዳታ ማሰባሰብያ ፍቃድ ይሰጥ እንደነበር በመግለጽ። ፍቃድ አሰጣጡም ህመምተኞቹ ከሚኖሩበት ወረዳ የድጋፍ ማሰባሰብያ ወረቀት ፣ ከሚታከሙበት ሃኪም ቤት የበሽታውን ሁኔታ የሚገልጽ ማህተም ያለው ወረቀት እና ለመጨረሻ ጊዜ ዳያሊሲስ ያረጉበትን ወረቀት ይዘው በመምጣት የፍቃድ ወረቀት እንደሚፃፍላቸውና ሲፃፍላቸው ከሁለት ማስጠንቀቂያዎች ጋርም እንደሆነ ገልጸውልናል።
አንደኛው ማስጠንቀቂያ የጊዜ ገደብ ሲሆን እርዳታ እሰባሳቢዎቹ የሚጻፍላቸው የፈቃድ ወረቀት ላይ ሁለት የጊዜ ቀነ ገደብ እንደሚሰጣቸው ማለትም በመጀመርያው የርዳታ ማሰባሰቢያው ላይ በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ውስጥ የሚፈልጉትን ያህል ብር እና እርዳታ ካላገኙ ተጨማሪ ሁለተኛ ጊዜ ቀን እንደሚጨመርላቸው።
ሁለተኛው ማስተንቀቂያም የህክምና እርዳታ ገንዘብ ማሰባሰብያውን ማድረግ የሚችሉት መኪና ውስጥ ብቻ እንደሆነ እና ከመኪና ወርዶ ህብረተሰቡን መጠየቅም ሆነ ረጅም ሰአት አንድ ቦታ ቆሞ በመኪና መንገዶቹን መዝጋት ፍቃዳቸውን እንደሚያስቀማቸው እና እንደሚያስቀጣቸው ጭምር ነግረውናል።
ሆኖም ቢሮው ከአንድ ወር በፊት ፍቃድ መስጠቱን እንዳቆሙ እና ያቆሙበት ምክንያትም ፍቃድ የሚጠይቀው የሰው ቁጥር መብዛቱ እና ይህንን የህክምና እርዳታ ገንዘብ ማሰባብሰቢያ ሃሰተኛ የህክምና ማስረጃዎችን እያመጡ አላማውን ለሳተ የግል ጥቅም እያዋሉት መሆኑን በጥቆማ ፣ በክትትል ስለደረሱበት እና ማስረጃዎቻቸው ላይ የሚያጠራጥሩ ጉዳዮችን ለማጣራት በሚሞክሩ ሰአት ሰዎቹ በዛዉ ደብዛቸው እንደሚጠፋ ገልጸው ለጊዜው ዘላቂ እና ህጋዊ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች መለያ እስኪፈጠር ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ ማቆማቸውን ሀላፊው ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል።
በዚህም ተያይዞ አብዛኛውን ጊዜ ወደውጪ እንዲላኩ ከሚያዙት ሶስት ሆስፒታሎች መካከል ለማግኘት የቻልነው ዘውዲቱ ሪፈራል ሆስፒታል ሲሆን እነሱም በሰጡን መረጃ መሰረት ምንም አይነት ለህክምና እርዳታ የሚሆን ፍቃድ እንደማይሰጡ ገልጸውልናል።
በአዲስ አበባ እየተስተዋለ ያለዉን የጎዳና ላይ የህክምና እርዳታ አሰባሰብ በተመላከተና ሂደቱ ለህገወጦች በር እየከፈተ ያለበትን ሁኔታ በማዉሳት ፖሊስ በህገወጥ ድርጊቶች የሚሳተፉ ግለሰቦችን ለመቆጣጠርም ሆነ ጥፋተኞች ሆነው ሲገኙ የሚወሰደውን የቅጣት እርመጃ በተመለከተ አዲስ ዘይቤ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለማወቅ ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።