ኅዳር 17 ፣ 2014

ከ70 ሺህ በላይ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞችን ስጋት ውስጥ የከተተው "አጎአ"

City: Hawassaኢኮኖሚ

ኢንዱስትሪ ፓርኩ ተመርቆ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ከ60 ሺህ በላይ ሰራተኞችን በቋሚነት እንደሚቀጥር መረጃዎች ያመለክታሉ።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ከ70 ሺህ በላይ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞችን ስጋት ውስጥ የከተተው "አጎአ"
Camera Icon

Photo: The Reporter

በሶስት ሚልየን ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አሁን ላይ ከ31 ሺህ በላይ ቋሚ ሰራተኞች አሉት። ኢንዱስትሪ ፓርኩ ሐምሌ 6/2008 ዓ.ም. ተመርቆ ስራ ጀምሯል። በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ከ60 ሺህ በላይ ሰራተኞችን በቋሚነት እንደሚቀጥር መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የ‹ኢፒክ› ካምፓኒ የሰው ሀብት አመራር አቶ ዳግም ሐይማኖት ኢትዮጵያ ከ‘አጎአ’ መቀነስ ከፍ ያለ ተጽእኖ እንሚኖረው ይናገራል። 95 በመቶ የሚሆነውን አጠቃላይ ምርት ለአሜሪካ ገበያ የሚያቀርቡት ፋብሪካዎቹ በወር ከ230 ሺህ በላይ አልባሳትን ይልካሉ። ‘አጎአ’ን ማጣት ከ2ሺህ በላይ ሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ላይ ጉዳት ማድረሱ እንደማይቀር ያምናሉ።

በAfrica Growth & Opportunity Act (AGOA) ከአርባ ያላነሱ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ እንደሆኑ በዲሴምበር 21/2018 Trade law Center የተባለ ተቋም በድረገፁ ላይ ይዞት የወጣው መረጃ ያሳያል። ይህ ተቋም የ‹አጎአ› ተጠቃሚ ሀገራት ብሎ ካስቀመጣቸው መካከል ኢትዮጵያ፣ ማሊ፣ ጊኒ፣ ቦትስዋና፣ ካሜሮን እና ደቡብ አፍሪካን በቀዳሚነት ማስፈሩን ተመልክተናል። በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ክሊንተን ዘመን የተጀመረው ከቀረጥ ነፃ ግብይት ከሃያ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። ኢትዮጵያ ከቀረጥና ከኮታ ነጻ በሆነው የንግድ ችሮታ ተጠቃሚ መሆኗ ለበርካታ ሥራ አጦች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ ብዙዎች ይስማማሉ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ‘አጎአ’ን ታሳቢ ያደረጉ ወደ ሃያ ሁለት የሚጠጉ የኢንደስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል። አብዛኛዎቹ ፓርኮች ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ ገበያ ሲያስገቡ የገቢ ቀረጥ አይከፍሉም።

በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሃምሳ ሁለት ‘ሼዶች’ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ሃያ የሚሆኑት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ምርቶቻቸውን ከቀርጥ ነጻ ይልካሉ። ከመካከላቸው ኢፒክ፣ ኤቨረስት፣ ኢንዶቼን፣ ጄፒ ጋርመንት፣ ጄፒ ቴክስታይል፣ ሰልቨር ስፓርክ፣ ሱምቤሪታ፣ ኢሳቤላ፣ ኬጄጄ እና አቬንዳ ካምፓኒዎች ወደ ዮኤስ ኤ ምርቶቻቸውን የሚልኩ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ አውሮፓ፣ ካናዳ፣ ኤሺያ፣ ዮናይትድ ኪንግደም እና ቻይና ይልካሉ።

መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ አድርገው፣ በርካሽ የሰው ጉልበት የሚያመርቷቸውን ዓለምአቀፍ ‘ብራንዶች’ ለአሜሪካን ገበያ የሚያቀርቡት ፋብሪካዎች የቀረጥ ቅናሹን ማጣታቸው የምርት ሂደት ወጪአቸውን ያሳድገዋል። አነስተኛ ወጪን ታሳቢ በማድረግ የተቀላቀሉት ገበያ አዋጭነቱ አጠያያቂ መሆኑ ፋብሪካቸውን እንዲዘጉ ማስገደዱ ሰራተኞችን እና ቤተሰቦቻቸውን አሳስቦ ብቻ አያበቃም። በሐገር ደረጃ መፍትሔ የሚያሻው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል።

በኤቨረስት ካምፓኒ የሺፒንግ ክፍል ኃላፊ የሆነው አቶ አዲሱ ደሳለኝ ከ70 በመቶ በላይ ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ እንደሚልኩ ነግረውናል። በቅርቡ በተሰማው ዜና በስራቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚኖረውም አልሸሸጉም። ከ50 ሺህ በላይ ልብሶችን ወደ ተለያዩ ሀገራት እንደሚልኩም ጨምረው ነግረውናል።

በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ቤስት ኢንተርናሽናል ጋርመንት ውስጥ ተቀጥራ መስራት ከጀመረች ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረችው እልፍነሽ ሞሎሮ ስጋቷን አጋርታናለች “ከክፍለ ሀገር ነው የመጣሁት ቤተሰቤንም የምረዳው ከዚሁ ከማገኘው ገንዘብ ነው። አሁን እንደተባለው ኢትዮጵያ ከአጎአ የምትቀነስ ከሆነ እኔ ብቻ ሳልሆን የእኔን እጅ የሚጠብቁ ቤተሰቦቼ ለከፋ ችግር ሊጋለጡ ይችላሉ። እንደምታውቀው አሁን ላይ ስራ ለመያዝ ያለው ፍዳ ከፍተኛ ስለሆነ ወደ ሀረብ ሀገር ለመሄድ ወስኜ አሁን ሀገሪቷ ያለችበት ሁኔታ  ግዴታ እንድቆይ አስገደደነ” ብላለች።

"ከአጎአ የመቀነሳችን ዜና ከተሰማ በኋላ ከደሞዛችን ውጪ በትርፍ ሰዓት ስራ የምናገኘውን ገቢ ቀንሶብናል። አሁን ‹ኦቨርታይም› የለም። ድርጅቱ እስከሚዘጋ ድረስ አልያም ሌሎች ሰራተኞች እንደሚሆኑት እሆናለሁ" ሲል ስጋቱን የገለፀልን ደግሞ የፓርኩ ሰራተኛ መሐመድ አወል ነው።

ከቀርጥ ነፃ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው ኤቨረስት ካምፓኒ ኢትዮጵያ ከ‘አጎአ’ እድል ብትሰረዝም ሥራዬን አላቋርጥም ብሏል። “ከ2ሺህ 3መቶ በላይ ሰራተኞች አሉን። እስካሁን ሰራተኞች ለመቀነስም ሆነ ፋብሪካችንን ለመዝጋት አላሰብንም። በቅደሚያ ፊታችንን ወደ ሌሎች ሐገራት ገበያ እናዞራለን” ብለዋል። ምርታቸው ኢትዮጵያ ተመርቶ የዓለም ገበያን የሚቀላቀልባቸውን ልዩ ልዩ ስልቶች በማቀድ ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ አዲሱ ሙከራው የማይሳካ ከሆነ ቀስ በቀስ የሰራተኛ ቅነሳ ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል።  

በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የኢንቨስትመንት ኮሚሾን ዋና ኃላፊ አቶ በላይ ኃይለሚካኤል ከ‘አጎአ’ መቀነሳችን ከሰባ ሺህ በላይ ዜጎችን ቤት የሚያንኳኳ እና እጅግ አደገኛ ነው ብለዋል። የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋናው ስራ ኢንቨስተሮችን ወደ ሀገር ውሰጥ ማምጣት እንደሆነ ጠቁመው ‘አጎአ’ን ስናጣ የእሱን ገበያ የሚተካ ገቢ ማፈላለግ የመንግሥም ሆነ የንግዱ ማኅበረሰብ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

አስተያየት