ጥቅምት 30 ፣ 2014

መጽሐፍ በቡና

City: Addis Ababaመዝናኛየአኗኗር ዘይቤማህበራዊ ጉዳዮች

“ማንበብ ክልክል ነው!” የሚል ማስታወቂያ በመለጠፍ የሚያነቡን ሰዎች ቤቱን ለቀው እንዲወጡ እስከመጠየቅ በሚደርስ ድፍረት ሲያሸማቀቁ የነበሩ ካፌዎች የሚነበቡ ነገሮችን በማቅረብ ደንበኞችን መሳባቸው አዲስ ጅማሬ ይመስላል።

Avatar: Henok Terecha
ሄኖክ ተሬቻ

Henok is a reporter at Addis Zeybe. He is passionate about storytelling and content creation.

መጽሐፍ በቡና
Camera Icon

Photo: Henok Terecha

ቀደም ባለው ጊዜ “ማንበብ ክልክል ነው!” የሚል ማስታወቂያ በመለጠፍ ካፌ ውስጥ ለማንበብ የሚሞክሩ ሰዎች ቤቱን ለቀው እንዲወጡ እስከመጠየቅ በሚደርስ ድፍረት ሲያሸማቀቁ የነበሩ ካፌዎች የሚነበቡ ነገሮችን በማቅረብ ደንበኞችን መሳባቸው አዲስ ጅማሬ ይመስላል። ንባብን በማበረታታት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በበርካታ ተገልጋዮች የታመነበት በካፌዎች ውስጥ የሚነበቡ ነገሮችን የማቅረብ አገልግሎት አዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ካፌዎች እየተለመደ ይመስላል። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በከተማዋ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ መስቀል ፍላወር፣ ቦሌ፣ ገርጂ፣ ፒያሳ፣ ላፍቶ አካባቢዎች በሚገኙ መደብሮች መደበኛውን የካፌ አገልግሎት ጨምሮ መጽሐፍ ሲያስነብቡ ተመልክቷል። ከእነዚህም መካከል ፊሊ ካፌ፣ ማንኪራ ካፌ፣ ጫካ ቡና፣ ዓለም አርት ጋለሪ ይገኙበታል። 

ተገልጋዮች ምን ይላሉ?

ቴዎድሮስ በጋሻው ገርጂ አካባቢ በሚገኝ “ዓለም አርት ጋለሪ” ውስጥ የሚገኝ ካፌ የዘወትር ደንበኛ መሆኑን ይናገራል። “ቤቱን ለመጀመርያ ጊዜ የተዋወቅኩት ከሠዓሊያን ጓደኞቼ ጋር ነበር። አሁን የዘወትር ደምበኛ ነኝ። ደንበኝነቴን ያጠናከረው መጽሐፍ መኖሩ ነው” የሚለው ቴዎድሮስ በሥራ ቦታው አቅራቢያ የሚገኘውን መጽሐፍ አቅራቢ ካፌ ዘወትር ይጎበኛል። ምሳውን በልቶ ሲያጠናቅቅ የከሰዓት በኋላ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት በሚተርፈው የሻይ ቡና ሰዓት ብቻ በመጠቀም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሁለት መካከለኛ መጠን ያላቸው መጽሐፍትን አንብቦ ስለመጨረሱ ነግሮናል። “አገልግሎቱ ሊበረታታ የሚገባው መልካም ጅምር ነው። ከታሰበበት እንደዋዛ የሚጠፋን ሰዓት በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል” ብሏል።

“ጫካ ቡና” ውስጥ ከሻይ ቡናው ጋር መጽሐፍ አዞ ሲያነብ ያገኘነው አድማሱ በላቸው “የካፌው ቋሚ ደንበኛ ነኝ” ይላል። “ደንበኝነቴን የጀመርኩት በሻይ ቡና ቢሆንም የንባብ አገልግሎቱ ቤቱን እንዳዘወትር አስገድዶኛል። ጅማሬው ንባብን ከማበረታታት አንጻር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ዝም ብሎ “አንብቡ!” ከማለት የሚነበበውን ማቅረብ ለውጥ ያመጣል ባይ ነኝ” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ተናግሯል። ፊሊ ካፌ፣ ማንኪራ ካፌ ያገኘናቸው የንባብ አገልግሎቱ ተጠቃሚ ደንበኞችም ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥተውናል።

ከንባብ አገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት አስተያየት ሰጪዎቻችን በተለመደው የካፌ አገልግሎት ያልተለመደውን የንባብ አገልግሎት ማግኘታቸው ያስገኘላቸውን ጠቀሜታ አስመልክተው እንዲህ ብለዋል። ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም፣ በቅርብ ከማይገኙ መጻሕፍት ጋር ለመተዋወቅ ከማገዙም በተጨማሪ ሰዎች በካፌ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቦታዎችም እንዲያነቡ ይገፋፋል።

መጻሕፍቱ ከየት ተሰባሰቡ?

በየጊዜው ለንባብ የሚበቁትን ጋዜጦች እና መጽሔቶችን ጨምሮ ቆየት ያሉ እና አዳዲስ መጻሕፍትን ከሚያቀርቡት ካፌዎች መካከል አንዱ የሆነው “ጫካ ቡና” የመስቀል ፍላወር አካባቢ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ባርቱጋ በርጋና ለካፌያቸው ደንበኞች መጽሐፍ ማቅረብ የጀመሩት ንባብን ለማበረታታት መሆኑን ነግረውናል። 

“ቀዳሚ ዓላማችን የንባብ ባህልን ማሳደግ ነው። የደንበኞቻችንን እርካታም ይጨምርልናል” የሚሉት ኃላፊው “ደንበኞቻችን ለንባብ በተዘጋጀው ቦታ ላይ ሻይ ቡና እያሉ ከተዘጋጁት የሕትመት ውጤቶች መካከል ያሰኛቸውን ማንበብ ይችላሉ” ብለውናል።

የካፌው ተጠቃሚ ደንበኞች በካፌው አገልግሎቶች ላይ ያላቸውን አስተያየት በተመለከተ ደግሞ አቶ ባርቱጋ ሲናገሩ “አስተያየቶቹ አበረታች ናቸው። ይሄንን ጨምሩ፣ ይሄ ይጎድላል የሚሉ ሐሳቦችን ተቀብለናል። የብዙዎቹ ደንበኞች ሐሳብና አስተያየት ግን የሚያበረታታ ነው” 

የ“ዓለም አርት ጋለሪ እና ካፌ” ባለቤት ወ/ሪት ዓለም ጌታቸው ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራት ቆይታ “አገልግሎቱን ስንጀምር የተጠቀምነው የራሳችንን መጽሐፍት ነበር። ያቀረብነው ለግል ፍላጎታቸውን የሰበሰብናቸውን መጻሕፍት ነበር። እስካሁን ተጨማሪ መጸሕፍት አልገዛንም። ነገር ግን እኛ ካቀረብናቸው መጻሕፍት በተጨማሪ ሐሳቡን የወደዱት ደንበኞቻችን በርካታ መጻሕፍት አበርክተውልናል። አሁን ያለው ክምችት የኖረው በደንበኞቻችን እገዛ ነው” ብላናለች። የጫካ ቡና ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው “ለንባብ የምናቀርባቸውን በየጊዜው የሚወጡ አዳዲስ መጻሕፍት እና መጽሔቶች የምናቀርበው በግዢ ነው። ወጪ ቢኖረውም ደንበኞቻችን ቤታችንን እንዲያዘወትሩት ስለሚያደርግ እንደተጨማሪ ወጪ አንቆጥረውም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አንባቢዎች

ረዥም ጊዜ ወስደው የሚያነቡ እና የሻይ ሰዓታቸውን ወይም የምሳ ሰዓታቸውን ብቻ በማንበብ የሚያሳልፉ ደንበኞች እንዳሏቸው የካፌዎቹ ሥራ አስኪያጆች ነግረውናል። መጽሐፍት የሚያቀርቡ ካፌዎችን የምትመርጠው ሳላማዊት ግርማ “ለሥራ ወይም ለሌላ ማኅበራዊ ጉዳይ ቀጠሮ ሲኖረኝ ሳይሰለቸኝ ለመጠበቅ ጥሩ አማራጭ ሆኖኛል። ስልክ እየነካኩ ወይም ብዙም ጠቀሜታ የሌላቸውን ገጾች እያገላበጡ ከመቆየት ከመጻሕፍትጋር መቆየት በጣም ጠቃሚ ነው” ብላለች።

አስነባቢ ካፌዎቹ ለደንበኞቻቸው የሰዓት ገደብ አላስቀመጡም። ተጠቃሚው በቃኝ የሚለውን ጊዜ ያህል የመጠቀም ዕድል አለው። የተጋነነ በሚባል የሰዓት ርዝመት ሲጠቀም ደንበኛ እንዳላጋጠማቸው ከካፌዎቹ ባለቤት እና ሥራ አስኪያጆች ሰምተናል።

በተጨማሪም ደንበኞች መጽሐፍቱን ማንበብ የሚችሉት የካፌውን አገልግሎት እስከተጠቀሙ ድረስ ብቻ እንጂ ይዘው እንዲሄዱ አይፈቀድላቸውም።

 የንባብ አማራጮች

ገበያ ላይ በቀላሉ የሚገኙ በቅርብ ጊዜ የወጡ መጻሕፍት፣ ሳምንታዊ መጽሔቶች እና ጋዜጦች በካፌዎቹ ውስጥ ለንባብ ከሚቀርቡት መካከል የበዛውን ቁጥር እንደሚይዙ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ተመልክቷል። በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፉ እና ለታዳጊ ህጻናት የሚሆኑ የተረት መጻሕፍትም የስብስቡ አካል ናቸው። በይዘት ደረጃም ልብ ወለድ፣ ፍልስፍና፣ ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ስነ-ልቡና መጻሕፍትን ማግኘት ይቻላል።

እለታዊ እና ሳምንታዊ የሆኑት ጋዜጣ እና መጽሔቶች በየጊዜው ይቀያየራሉ። ጊዜ ሲያልፍባቸው የመነበብ እድላቸው ስለሚቀንስ እናነሳቸዋለን። መጻሕፍቱ ግን አይቀያየሩም በግዢ ወይም በስጦታ ሲገኙ እየጨመሩ የሚሄዱ ናቸው።

እነማን ያነባሉ?

አስነባቢ ካፌዎቹ በተለያየ የእድሜ ክልል እና የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ደንበኞች እንዳሏቸው ነግረውናል። በጫካ ቡና በኩል የሚበዙት የቤቱ የንባብ ደንበኞች እድሜአቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆነ ጎልማሶች ቢሆኑም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወጣት ደንበኞችንም ማፍራት መጀመራቸውን ይናገራሉ። ዓለም አርት ጋለሪ ደግሞ ተጨማሪ ቅርንጫፎችን እንዲከፍቱ የሚጠይቁ ደንበኞች ጭምር ስለማፍራታቸው አዲስ ዘይቤ ሰምታች።  

“ከስብስቦቻችን መካከል የሕጻናት መጻሕፍትም ይገኛሉ” የሚሉት የዓለም አርት ጋለሪ ስራ አስኪያጅ ከታዳጊ ህጻናት እስከ አዛውንቶች በማንኛውም አጋጣሚ ጋለሪያቸውን ወይም ካፌአቸውን የጎበኘ ሰው የንባቡም ተሳታፊ እንደሚሆን ተመልክቻለሁ ብለዋል።    

የአዲሱ ባህል አዲስ አበርክቶ

የንባብ ባህል አላደገም የሚለውን ድምዳሜ በርካቶች ይስማሙበታል። የሕዝብ ቁጥሯ ከ100 ሚልዮን በላይ ለሆነ ሐገር የሚታተሙ መጻሕፍት የኮፒ ብዛት ለዚህ አባባል በዋነኛ ማመሳከሪያነት ይቀርባል። በጥቂት ሺዎች የሚቆጠር ቅጂ የሚታተሙ መጻሕፍት ተሸጠው ለመጠናቀቅ የሚፈጅባቸው ጊዜያት ርዝማኔ የተደራሽነታቸውን መጠን ያሳያል። ከሥራ እና ከትምህርት ጉዳዮች ውጭ ለጊዜ ማሳለፊያ ወይም ለመዝናኛ ማንበብ እየቀረ ለመምጣቱ ደግሞ የኢንተርኔት መስፋፋት፣ የመጽሐፍት ዋጋ ውድ መሆን፣ የጊዜ እጥረት፣ የመጻሕፍት በቅርበት አለመገኘት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።    

ተደጋግሞ የተነሳውን የአንባቢዎች ቁጥር መቀነስ እና የንባብ ባህል መጥፋት ለማነሳሳት እንዲህ ዓይነት ተግባራት የማይተካ ሚና ይጫወታሉ። እንደ ፓሪስ ባሉ ከተሞች የተለመደው በካፌዎች ውስጥ የማንበብ እና የማስነበብ ልምድ መዳበሩ እየተነሳ ላለው የንባብ ባህል መውረድ ችግር የመፍትሔ መንገድ እንደሚሆን ብዙዎች ይስማማሉ። በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች መስፋፋቱም ምክንያታዊ እና አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ያየለ ጠቀሜታ እንዳለው የዘርፉ ምሁራን ያብራራሉ።

አስተያየት