ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጎንደር እና አካባቢዋ በሎተሪ የማጭበርበር ድርጊቶች እየተበራከቱ ስለመምጣታቸው ከፖሊስ ያገኘነው ሪፖርት ያስረዳል። በነዋሪዎች የማይጠረጠሩ ተቀያያሪ ስልቶች ያሏቸው አታላዮቹ ድርጊቱን የሚፈጽሙት በቡድን ወይም በተናጠል ነው። በሎተሪ ስም ተጭበርብረው ገንዘባቸውን፣ ጌጣጌጦቻቸውን፣ የእጅ ስልካቸውን፣ ላፕቶፕ እና ሌሎች ንብረቶቻቸውን የተቀሙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ካነጋገራቸው ነዋሪዎች ተረድቷል።
በሎተሪ የማጭበርበር ተግባር ላይ የተሰማሩት ግለሰቦች የሚመርጡት የሕብረተሰብ ክፍል እንደሌለ ከአስተያየት ሰጪዎቻችን ሰምተናል። የማታለያ ዘዴአቸውን እየቀያየሩ ነዋሪውን ብቻ ሳይሆን ለጉብኝት የመጡ እንግዶችንም በማታለል ንብረታቸውን ይወስዳሉ። ድርጊቱ ሀይ ባይ የማያገኝ ከሆነ የከተማዋን ቱሪዝም ሊጎዳው እንደሚችል የብዙዎች ስጋት ነው።
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የደብረታቦር ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ እስከዳር አራጋው “በሎተሪ ማጭበርበር እስከ 50 ሺህ ብር ድረስ የተጭበረበሩ ሰዎች መኖራቸውን አውቃለሁ” ይላሉ። አቶ እስከዳር የማጭበርበር ሂደቱ ምን እንደሚመስል ሲያብራሩ “በሎተሪ የማጭበርበር ተግባር ላይ የተሰማሩት ግለሰቦች ያገለገሉ የሎተሪ ትኬቶችን ይሰበስባሉ። ፈጣን ሎተሪን ጨምሮ ጊዜ ያለፈባቸውን ሁሉንም ዓይነት የሎተሪ ትኬቶች የሚገለገሉባቸው ‘ፎርጅድ’ ሎተሪ ለማዘጋጀት ነው” ብለውናል።
የሰበሰቡትን ካርድ እና ትኬት ዕውነተኛውን በገንዘብ የሚመነዘር እጣ ያለው ሎተሪ አስመስለው ያዘጋጁታል። የህትመት መሳሪያዎችን፣ ማጣበቂያዎችን እና ሌሎች መገልገያዎችን ያለፈበትን ሎተሪ ያላለፈበት ለማስመሰል ይጠቀማሉ። በቅርብ ከወጣው ገንዘብ የሚያስገኝ እጣ ጋር አመሳስለው ያዘጋጁና እንደሚያታልሉት ሰው ማንነት ራሳቸውን በመቀየር ይጠቀሙበታል። መታወቂያ የለኝም፣ ሐገሩን አላውቀውም፣ ሎተሪውን በአነስተኛ ገንዘብ ግዛኝ፣ በጌጣጌጥ ለውጠኝ በሚሉ እና በሌሎች ዘዴዎች ተጠቅመው ገንዘብ ወይም ጌጣጌጥ ይዘው እንደሚሰወሩ ሰምተናል።
“የቀረበኝ ማንበብ እና መጻፍ የማይችል በመምሰል ነው” የሚለው ወጣት ስሙን እንድንጠቀም አልፈቀደልንም “ይህችን ካርድ ዕይልኝ ብሎ ቀረበኝ። ፈጣን ሎተሪ ነበር። 75 ሺህ ብር ደርሶታል። የሆነ ሰው 10 ሺህ ደርሶሀል 6 ሺህ ልግዛህ ብሎኝ ነበር ሲለኝ አልተጠራጠርኩትም። እንዳለው 75 ሺህ ደርሶታል። ቦታውን እንደማያውቀው፣ እዚያ አካባቢ አጭበርባሪ እንዳለ ብዙ ነገር አወራኝ። ስላሳዘነኝ ቼኩን ከብሔራዊ ሎተሪ ተቀብዬ እንዳመጣለት ተስማማን። መንገድ ስጀምር በምን አምንሃለሁ አለ። መተማመኛ እንዲሆነው ላፕቶፔን ሰጠሁት። ውስጥ ስገባ ሎተሪው የተጭበረበረ ነው። በፊት የተውኩት ቦታ ስሄድ የለም። ላፕቶፔ ቀለጠ” ሲል ገጠመኙን አካፍሎናል።
የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆነችው መሰለች አባቡ ተመሳሳይ ገጠመኝ አላት። የሐይማኖት አባት መስለው ቤተክርስቲያን በር ላይ ያገኟት አጭበርባሪ ከሎተሪ ሻጭ ጋር ቆመው እንደነበር ታስታውሳለች። “ይሄ ልጅ የሚለኝ እውነት ነው እስኪ እይልኝ ልጄ ብለው ቀረቡኝ። 25ሺህ ብር ደርሷቸዋል። ሎተሪ ሻጩ እንዳላመኑት ነገረኝ። ልክ መሆኑን ስነግራቸው ግን በዚህ ደካማ ጉልበቴ እንዴት ብዬ ልሂድ እባክሽ ብሩን ተቀበይልኝ አሉኝ። ትልቅ አባት ስለሆኑ እምቢ ማለት አልቻልኩም። በባጃጅ ኮንትራት ልውሰዶት ብላቸውም ፈቃደኛ አልሆኑም። እዚያው እንደሚጠብቁኝ ተስማማን። ለመተማመኛ የታክሲ ብር ብቻ አስቀርቼ ቦርሳዬን ሰጠኋቸው። አጭበርባሪ መሆናቸውን ያወቅኩት ካርዱ ፎርጅድ ነው ሲሉኝ ነው። ስመለስ የሉም። ቦርሳዬ ውስጥ ስልክ፣ ገንዘብ እና ወርቅ ነበረበት”
አጭበርባሪዎቹ እንታወቃለን ብለው የማያስቡበት ቦታ ሁሉ ቢገኙም የእምነት ቦታዎች አካባቢ የእምነት አባት በመምሰል፣ ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች ማንበብ እና መጻፍ የማይችሉ በመምሰል የሚያጭበረብሩት እንደሚበዙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ወ/ሮ እናንዬ ፈንቴ የደብረታቦር ከተማ የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ቢሮ የሽያጭ ሰራተኛ ነች “ህጻናትን በመጠቀም ያጭበረብራሉ” ብላናለች። ይህ ዘዴ ከ8 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት የተዘጋጀላቸውን ገንዘብ የሚያስገኝ ‘ፎርጅድ’ ካርድ በመያዝ የሚያታልሉበት ነው። የማጭበርበሩ አካል የሆኑ ሌሎች ሰዎችም መንገደኛ መስለው የሚያጨናብሩበት ጊዜ አለ። ትልልቅ ሰዎችን በመቅረብ እጣው ሲደርሳቸው ግራ እንደተጋቡ የሚያስመስሉት ህጻናቱ በተባባሪዎቻቸው ታግዘው ሊረዳቸው የሚሞክረውን ሰው ገንዘብ ወይም ጌጣጌጥ እንደሚወስዱ እናንዬ ፈንቴ ነግራናለች።
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የደብረታቦር ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ እስከዳር አራጋው ሕብረተሰቡ ለአጭበርባሪዎች እንዳይጋለጥ እየተወሰደ ስለሚገኘው እርምጃ ነግረውናል። “የመጀመርያው እርምጃችን ደምበኞቻችን ግንዛቤ እንዲያገኙ ማስቻል ነው። በየከተማው በባነር እና በራሪ ወረቀቶች ማስታወቂያ እንሰራለን። ሁለተኛው እርምጃ ተመሳሳይ የጥፋት ተግባራት ላይ የተሰማሩ ሰዎች እንዳሉ ማሳወቅ ነው። ደምበኞቻችን በሌሎች ሰዎች የደረሰውን መጭበርበር ሲመለከቱ ራሳቸውን እንደሚጠብቁ እናስባለን። ሦስተኛው እርምጃ በዚህ ወንጀል የተሰማሩ ሰዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ነው። የአጥፊዎቹ መቀጣት መቀጣጫ ሲሆን የወንጀለኞች ቁጥር እንደሚቀንስ እንጠብቃለን” የሚል ምላሽ አግኝተናል።