ኅዳር 23 ፣ 2014

ምክንያት አልባ የተኩስ ድምጽ ያማረራቸው የደቡብ ጎንደር ነዋሪዎች ቅሬታ

City: Gonderወቅታዊ ጉዳዮች

ከጀምበር ማዘቅዘቅ በኋላ የተኩስ ድምጽ መስማት እየተለመደ ስለመምጣቱ የደቡብ ጎንደር ዞን የደብረታቦር ከተማ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ምክንያት አልባ የተኩስ ድምጽ ያማረራቸው የደቡብ ጎንደር ነዋሪዎች ቅሬታ

ከጀምበር ማዘቅዘቅ በኋላ የተኩስ ድምጽ መስማት እየተለመደ ስለመምጣቱ የደቡብ ጎንደር ዞን የደብረታቦር ከተማ ነዋሪዎች ይናገራሉ። “ክስተቱ በቅርብ ጊዜ የተጀመረ አይደለም” የሚሉት ነዋረዎቹ “ቀደም ሲል ጋብ ብሎ ነበር፤ አሁን እንደገና ብሶበታል” ይላሉ። ነዋሪዎቹ ከምሽት ጀመሮ ሌሊቱን የሚደመጠው ተኩስ ከሦስት ዓመት በፊትም እንዳጋጠመና አሁን ተባብሶ እንደሚደመጥ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

ወ/ሮ የእልፍኝ ማተቤ በደብረታቦር ከተማ በቀበሌ 05 ወይም በተለምዶ አጠራሩ ወይብላ ማሪያም ሰፈር ነዋሪ ናቸው። “ከገጠር መጥቼ እዚህ ሰፈር ተከራይቼ እየኖርኩ ነው” የሚሉት ወይዘሮዋ እሳቸው በነበርኩበት አጎና አካባቢ ጥይት ካልባረቀበት ወይም ሰው ካልሞተ ጥይት እንደማይተኮስ ያስታውሳሉ። “ይህንን ያየሁት ከተማ ገብቼ ስኖር ነው። አብዛኛውን ጊዜ በምሽት የጥይት ድምጽ ይሰማል። ምክንያቱ ምን እንደሆነም አይታወቅም። ልጆቼ ከእንቅልፋቸው እየባነኑ የሰላም እንቅልፍ የላቸውም። ትልልቁም ሰላም የለውም” ብለዋል።  

የወረታ ነዋሪ የሆነው ሌላው አስተያየት ሰጪአችን አለልኝ አንዳርጌ ይባላል። ከምሽት አንስቶ ሌሊቱን የሚደመጠው የተኩስ ድምጽ ከደብረታቦር በባሰ ሁኔታ ወሮታም እንዳለ ይናገራል። “አንዳንዶች የሰሜኑ ጦርነት ያሉበት ቦታ የደረሰ ይመስላቸዋል። ሌሎች ደግሞ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች የሚተኩሱት ነው ይላሉ። እውነተኛ ምክንያቱን የሚያውቅ የለም” ሲል ገጠመኙን አጋርቶናል።  

 “ሳይተኮስ የማያድርበት ቀን የለም” የሚለው አቶ ዋለልኝ ከሰሜኑ ጦርነት መባባስ በኋላ እየጨመረ ቢመጣም ቀድሞም የነበረ ስለመሆኑ ይናገራል። እንደ ነዋሪዎቹ ግምት ጥይቱ የሚተኮሰው ለተለያዩ ማኅበራዊ ዝግጅቶች ደስታን እና ሐዘንን ለመግለጽ፣ ሌባን ለማባረር፣ የጦር መሳሪያን ደህንነት ለመሞከር፣ ባላጋራን ለማስፈራራት፣ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረግ ጥረት እና ይህንን በመሳሰሉት ሰበቦች ነው።

አቶ ታዘብ እንግዳው የደብረታቦር ከተማ የቀበሌ 04 ነዋሪ ነው። “በአካባቢው በደስታ ወይም በሀዘን ጊዜ ጥይት የመተኮስ ልማድ አለ። ትልቅ ሰው ሲሞት ወይም ሰርግን ለመሰሉ ዝግጅቶች ጥይት ይተኮሳል። ይሔኛው ግን ከዚያ ይለያል። አንድ ጊዜ ተተኩሶ የሚያቆም ሳይሆን ተከታታይነት ያለው ነው። ከዚህ በፊት አንድ ጥይት ሲተኮስ ሰዎች ሌባም ከሆነ አደጋም ከሆነ ብለው ከቤት በመውጣት አካባቢያቸውን ይቃኙ ነበር። አሁን ያ ሁሉ ቀርቷል” ብሎናል።

የደቡብ ጎንደር ዞን የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር የሰላምና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሽባባው ሞላ ይህን መሰል ድርጊት ይበልጥ የተስፋፋው ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል። እየወሰዱት የሚገኘውን እርምጃ በተመለከተ “የቀበሌ መዋቅሩ፣ የከተማ አስተዳደሩ፣ የፖሊስ አባላት፣ የአድማ ብተና፣ የሚሊሻ ኃይሎቻችን በመቀናጀት እየሰራን ነው። አላግባብ የሚተኩሱትን እያስቀጣን ነው። በተጨማሪም ከፖሊስ አካላት ውጪ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እያገድን ነው” በማለት አስረድተዋል። ችግሩ በተጠቀሰው ዓመት የተስፋፋበት ምክንያት በግልጽ እንደማይታወቅም ከንግግራቸው ተረድተናል።

“አግባብነት የሌለው ተኩስ በርካታ ጉዳቶች አሉት” የሚሉት ኃላፊው ህጻናት እና ሴቶች፣ ነፍሰጡሮች እና አዛውንቶች ተረጋግተው የእረፍት ጊዜያቸውን እንዳያሳልፉ እንቅፋት ከመሆኑም በተጨማሪ ለጸረ-ሰላም ኃይሎች ሽፋን የመስጠት አደገኛ ውጤት እንዳለው ነግረውናል። “የቀብር ስነ-ስርአት ላይ የተተኮሰ ጥይት የንጹሐን ለቀስተኞችን ህይወት ያጠፋበት አጋጣሚ አለ” ሲሉ የቅርብ ጊዜ ገጠመኛቸውን አጋርተውናል። “በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ አመራሩ እና የጸጥታ አካሉ ወደ ጦር ግምባር በመዝመቱ ክፍተት ተፈጥሯል። በዚህ ምክንያት የምሽት ተኩስ ጨምሯል። አሁን ግን ሕግ አውጥተን አጥፊዎችን እየቀጣን እንገኛለን” ያሉ ሲሆን የቅጣት ዝርዝሩን እንደሚከተለው ዘርዝረዋል።

“በሰርግ፣ በለቅሶ፣ በክርስትና ወይም በሌላ ባህላዊ የሰዎች መሰብሰቢያ ቦታ ጥይት የተኮሰ የገንዘብ ቅጣት ይቀጣል። ቅጣቱ ለአንድ ጥይት 1ሺህ 5መቶ ብር ሲሆን በተደጋጋሚ የሚያጠፋ ግለሰብ በእጁ የሚገኘውን የጦር መሳሪያ ይነጠቃል” ብለዋል። አላግባብ ተኳሾች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማሰብ ከነዋሪው ጋር በተደረገ ውይይት እየተፈጸመ የሚገኘው የቅጣት ሕግ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ መተግበር መጀመሩም ተገልጾአል። በዚህ ሕገ-ወጥ ድርጊት ተሰማርተው የሚገኙ ግለሰቦችን ማኅበረሰቡ በጥቆማ ቅጣታቸውን እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባውም ተጠቁሟል።