በአጭር ስልክ ጥሪ እና በተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበርያ የሚታገዝ የታክሲ አገልግሎት ሰጭ የሆነዉ “ዛይ ራይድ” በቅርቡ በሌሎች 5 የኢትዮጵያ ከተሞች አገልግሎቱን መስጠት እንደሚጀምር የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሀብታሙ ታደሰ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
ድርጅቱ በቅርቡ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ከተሞች ሀዋሳ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ አዳማ እና ቢሾፍቱ ሲሆኑ በአዲሱ አገልግሎት ከመኪና በተጨማሪ ሞተር ሳይክል፣ ሳይክል እና ባለ ሦሰት እግር ተሽከርካሪዎች እንደሚካተቱም ሰምተናል።
ከአዲስ አበባ በተጨማሪ የአገልግሎት አድማሱን ያሰፋው ተቋሙ በቀደመው አገልግሎቱ ያልተካተቱ የተሽከርካሪ ዓይነቶች ከማካተቱ ባለፈ ተጨማሪ አገልግሎቶች እንደሚኖሩትም አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል።
ሥራ አስኪያጁ ተጨማሪ አገልግሎት እና ተሽከርካሪዎች ያስፈለጉበትን ምክንያት ሲያብራሩ “የደምበኞቻችንን አቅም፣ ምቾት እና ፍላጎት ያገናዘበ አገልግሎት ለመስጠት ነው” ብለዋል አክለዉም ከአዲስ አበባ ውጭ አገልግሎቱ በሚጀመርባቸው ከተሞች ተገልጋዮች ሞተር ተሽከርካሪ፣ ሳይክል፣ ባለ ሦስት እግር ተሽርካሪ/ባጃጅ ወይም መኪና መጠቀም የሚችሉ ሲሆን እንደ ብዛታቸው፣ ፍላጎታቸው እና የመክፈል አቅማቸው ተሽከርካሪዎቹን የሚመርጡበት አሰራር ይኖራል፡፡ በአጭር የስልክ ቁጥር ወይም በሞባይል መተግበሪያ የዛይ ራይድ ተሸከርካሪዎችን የሚጠሩ ደንበኞች ራሳቸው መጓዝ ካልሆነም እንዲደርስላቸው የሚፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ለአሽከርካሪው መላክ ወይም እንዲያመጣላቸው ማዘዝ ይችላሉ ብለዋል ኃላፊው፡፡
የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ከድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ እንደሰማው “ዛይ ራይድ” ከሁለት ሳምንት በኋላ በሐዋሳ ከተማ አገልግሎቱን ሲጀመር አብረውት እንዲሰሩ ሁለት መቶ ተሽከርካሪዎችን እንደመዘገበም ታውቋል። የተመዝጋቢዎቹ ቁጥር ሥራ ለማስጀመር ያስቀመጠው አነስተኛ መጠን ላይ ሲደርስ ስልጠና ሰጥቶ ስራ እንደሚያስጀምር ይጠበቃል። በመጀመሪያው ዙር አምስት መቶ ተሽከርካሪዎችን ለመመዝገብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ለመነሻ የተያዘው የተሽከርካሪዎች ቁጥር የደንበኞች ብዛት እና ፍላጎት በየጊዜው ይጨመራል ተብሏል።
ዛይ ራይድ በአዲስ አበባው አገልግሎቱ ለስልክ ጥሪ የሚቀበልበትን “6003” ለክልል ከተሞችም እንደሚገለገልበት አሳውቋል። “ዛይ ራይድ” በስልክ ጥሪ እና በመተግበሪያ የታገዘ የታክሲ አገልግሎት በመስጠት በኢትዮጵያ የመጀመርያው ነው።
ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞች የታክሲ አገልግሎት በመስጠት ቀዳሚው “ታክሲዬ” የተሰኝዉ ድርጅት ሲሆን ታክሲዬ ከአዲስ አበባው በተጨማሪ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሀዋሳ፣ ጅግጅጋ፣ ድሬደዋ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር እና መቐለ ላይ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሁለት ዓመታት መቆጠራቸውን የድርጅቱ ማርኬቲንግ ኃላፊ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ውጭም በ18 የአፍሪካ ሐገራት ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣል። ከሀገራቱ መካከል ሞዛማቢክ፣ ማላዊ፣ ታንዛንያ ደቡብ ሱዳን፣ ዩጋንዳ እና ኬንያ ይጠቀሳሉ።
የማርኬቲንግ ኃላፊው ዲቦራ ማሞ እንዳብራሩት በ”6055” የስልክ ጥሪ ከደንበኞቹ ጋር የሚገናኘው “ታክሲዬ” ለአዳማ 6127፣ ለባህርዳር እና ጎንደር 6124 ለድሬዳዋ 6125 የሚጠቀምባቸው ቁጥሮች ናቸው። ከመኪና በተጨማሪም ሞተር ሳይክል እና ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ/ ባጃጅ ይጠቀማል።
ኃላፊው በማብራሪያቸው የባጃጅ አሽከርካሪዎች እንቀማለን በሚል ምክንያት ስማርት ስልኮችን ለመያዝ ፈደኛ አለመሆናቸው ሥራቸውን አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል። “ሥራው ከኢንተርኔት አገልግሎት እና ከስማርት ስልክ ጋር የተገናኘ በመሆኑ አስቸጋሪ አድርጎብናል” ብለዋል። ከክልል ከተሞች አገልጋዮች ኮሚሽን ማሰብ ያልጀመረው ድርጅቱ ገበያውን በማስለመድ ላይ ነኝ ብሏል። አጓጊ የሚባል ገበያ አለመሆኑንም አክሎ ገልጾአል።