ኅዳር 2 ፣ 2014

“ጋፋት” የመጀመርያው የኢንዱስትሪ መንደር

City: Gonderኢኮኖሚታሪክቱሪዝም

“ጋፋት”ን የያዘችው ደብረታቦር መገኛዋ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በደቡብ ጎንደር ዞን መስተዳድር ሲሆን በ1327 ዓ.ም. በአፄ ሠይፈ አርዕድ እንደተቆረቆረች ይነገርላታል።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

“ጋፋት” የመጀመርያው የኢንዱስትሪ መንደር

በቀድሞ አጠራር “ጁራ” በሚል ስያሜ የምትታወቀው ደብረታቦር በአሁኑ ወቅት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ነች። “ጋፋት”ን የያዘችው ደብረታቦር መገኛዋ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በደቡብ ጎንደር ዞን መስተዳድር ነው። በ1327 ዓ.ም. በአፄ ሠይፈ አርዕድ እንደተቆረቆረች ይነገርላታል። ከአዲስ አበባ 667 ኪ.ሜ. ከባህርዳር ከተማ 97 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ትገኛለች። በሰሜን ጠባሪ ማሪያም፣ በደቡብ ህረይ፣ በምስራቅ ጌራ፣ በምዕራብ ሰላምኮ የተባሉ አካባቢዎች ያዋስኗታል። ነገደ ጋፋት ወይም ነገደ እስራኤል የሚል መጠሪያ ያላቸው የጋፋት ነዋሪዎች በብረታ ብረት፣ በሸክላ፣ በሽመና፣ በቆዳ ሥራ ላይ የተሰማሩ ጠቢባን ነበሩ። ለአካባቢው ሕብረተሰብ የአንገት ጌጥ፣ የጀሮ ጌጥ እና ወረንጦ በመሸጥ ይተዳደሩ እንደነበር ይነገራል። በአካባቢው ይኖሩ የነበሩት ሰዎች የጋፋትኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው። ጋፋትኛ ቋንቋ እና ተናጋሪዎቹ በጊዜ ርዝመት በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ተተክተዋል።

በጎንደር እና አካባቢዋ የሚገኙ ቅርሶችን በማስጎብኘት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ማንደፍሮ ተሻለ “ጋፋት በኢትዮጵያ የመጀመርያው ኢንዱስትሪ መንደር ሊባል ይችላል” ይላሉ። እንደ አስጎብኚው አባባል ነገሩ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም በአፍሪካ የመጀመርያው ኢንዱስሪ መንደር ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚም አለ። ንጉሡ የውጭ ሀገር ኃይሎችን አስረው ኢትዮጵያ ወደፊት በሥልጣኔ ትራመድ ዘንድ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ስራዎችን ጋፋት ላይ አሰርተዋል። ከሴፓስቶፖል በተጨማሪ ሌሎች መድፎች እና መድፉ የተጓጓዘበት ጋሪ የተሰሩት በዚህች ታሪካዊ ሥፍራ ነው። ነገደ ጋፋት ለእቃ ማጓጓዣ የሚያገለግላቸው እንደ ካሬታ ያለ (በእጅ የሚገፋ ተሸከርካሪ የእቃ ማጓጓዣ) ሰርተው ይጠቀሙ ነበር። ጋፋት/ደብረታቦር አርቆ አሳቢው ንጉሥ አጼ ቴዎድሮስ ራዕዩን የተለመባት፣ የዘመናዊነት ፈር-ቀዳጅ፣ ቀድማ ዘምና ቀድማ የተረሳች፣ ሴባስቶፓል የተገነባባት፣… ለቁጥር የበዙ ታሪካዊ ሁነቶችን ያሳለፈች ናት።

በሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች በጋብቻ እና በማኅበራዊ ግንኙነት ስለሚገለሉ አካባቢያቸውን አጥረው ይኖሩ እንደነበር ይነገራል። አፄ ቴዎድሮስ ጋፋትን በመመልከትና በማጥናት የጦር መሳሪያ የማምረት ሐሳብ ወጠኑ። ከዚያም ቦታውን ከልለው እንዲጠብቁ አደረጉ።

ግዙፉ የጋፋት ታሪክ

ንጉሡ በወታደራዊ አቅሟ የደረጀች አገር ለመገንባት፣ በቴክኖሎጂ አገራቸውን ለማሳደግ በእጅጉ ጥረዋል። በአንድ ወቅትም ለእንግሊዝ መልእክተኛ ለራሳም በጻፉት ደብዳቤ “ከንግሥቲቱ ወዳጅ፣ ካንቱ ከወንድሜ የምፈልገው ፍቅራችሁን እንጅ ኃብት አልፈልግም። ኃብት አለመፈለጌ ኃብታም ሆኘ አደለም፣ በጥበብ ዓይኔን ትከፍቱልኝ ብየ እንጅ” ስለ ማለታቸው የታሪክ መዛግብት አስቀምጠዋል።

አጼ ቴዎድሮስ የውጭ አገር ሰው ሲያገኙ ዋናው ጥያቄያቸው "ምን ሥራ ታውቃለህ?” የሚል ነበር። ምንም አላውቅም የሚል ምላሽ ከሰጠ ዳግመኛ አያናግሩትም፤ ፈጥኖም ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ያዛሉ። ቴዎድሮስ ያሰባሰቧቸውን ሙያ ያላቸው ፈረንጆች በመጀመርያ ያሰፈሩት መቅደላ ነበር። ጥቂት ቆይቶ ግን ብርዱ እና ሌሎች ሁኔታዎች ስላልተመቹ ከመቅደላ ተራራ ወርደው ጋፋት እንዲኖሩ ተፈቀደ። በሰኔ ወር 1852 ዓ.ም. ፍላድ፣ ዎልድሚየር፣ ቤንደር፣ ሳልሙለር፣ ኮንዝላን፣ ሜየር ከነባለቤቶቻቸው ጋፋት (ደብረታቦር) አቀኑ። በዝናብ እና በጭቃ ምክንያት ከሰባት ቀን በኋላ ጋፋት ደረሱ። በዚያም በሕብረት ሆነው 12 ትናንሽ ቤቶች ሰሩ። በሕብረት ሥራውም አንዱን ቤት ሰርተው የሚጨርሱት በአምስት ቀን ነበር። በዚህ ዓይነት የሕብረት አሰራር እያንዳንዳቸው ሁለት ጎጆ አገኙ አንዱ ቤት የመኝታና እልፍኝ /ሳሎን/ ሲሆን አንደኛው ማድ ቤት ነበር። በዚህ ሁኔታ ጋፋት የአሮፓውያን ሠፈር ሆነ።

በዘመኑ ጋፋት የነበሩ ቤቶች፡- ካምፕ ወይም መኖሪያ ቤት፣ የዘበኛ ቤት (ዙሪያውን የቃፊር ቤት ነበር)፣ መሐል ላይ የፈረንጆች መኖሪያ ቤት፣የግብር ማስገቢያ ቤት፣ ከሰል ቤት፣ ፈረስ ቤት፣ የመድፍ መስሪያ ቤት፣ ሸክላ ቤት ናቸው።

ከዚህ በኋላ የጋፋት ነዋሪዎቹ ፈረንጆች መድፍ መስራት የጀመሩት። ቴዎድሮስ በወረቀት የተሳለውን የመድፉን ሞዴል ዓይተው ከተስማሙ በኋላ በአስቸኳይ እንዲሰራ አዘዙ። የጉልበቱን ሥራ የሚረዷቸውም በሽህ የሚቆጠሩ ሰዎች አቀረቡ። በብርቱ ጥረት እና በእልህ አስጨራሽ ትግል ሰማንያ ኩንታል የሚመዝነው መድፍ ተሰራ። በዚህ የተደሰቱት አጼ ቴዎድሮስ ‹‹ሴባስቶፖል›› ሲሉ ሰየሙት።

አፄ ቴዎድሮስ በመድፍ ስራው ላይ ለተካፈሉት ኢሮፓውያንም የክብር ቀሚስ በወርቅና በብር እቃ ያጌጠ ፈረስና በቅሎ ሸለሙዋቸው። ለእያንዳንዳቸውም አንድ አንድ ሽህ ብር ሰጧቸው። ቴዎድሮስ ፈረንጆችን በሽልማት ካስደሰቱ በኋላ ለመድፉም ሆነ ለሌላ እቃ ማጓጓዣ እንዲሰሩ ጠየቋቸው። እነሱም ተባብረው አስራ አራት ጋሪዎች ሰሩ።

የጋፋት የዛሬ ገጽታ

ጋፋት ውስጥ ከሚገኙ ቅርሶች መካከል የአጼ ዮሐንስ 4ኛ የክረምት ቤተ መንግሥት፣ ጥንታዊ ቤተ እምነቶች ይጠቀሳሉ፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ሁሉም በቂ ጥበቃ ባለማግኘት ምክንያት ፈራርሷል።

በአሁኑ ሰዓት ጋፋት ታሪካዊነቷን በሚመጥን ጥበቃ ስር አትገኝም። በወቅቱ ለመድፍ መስሪያ ያገለገሉ ቁርጥራጭ ብረቶች የጊዜን ፈተና አልፈው ከአፈር ጋር ተደባልቀው ይታያሉ። አስታዋሽ ያጡ ይመስላሉ። በዚያን ዘመን ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ቤቶች ጨርሰው ባይጠፉም ለመጪው ትውልድ ታሪክን በሚያስታውስ አያያዝ ስር አይገኝም። ቀድሞ የአጼ ቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት በነበረው ሥፍራ የገበሬዎች ቤት ሆኗል። ሰባት አባወራዎች ይኖሩበታል። እያረሱ እንስሳትን እያረቡ መደበኛ ኑሯቸውን ያካሂዱበታል። አሁን ያለው ሂደት የማይታረም ከሆነ ጋፋትን የሚያስታውስ የታሪክ አሻራ እንዳይጠፋ ያሰጋል።

አስተያየት