መጋቢት 26 ፣ 2014

ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሴቶች የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ሊሰጥ ነው

City: Bahir Darዜና

ክትባቱ 14 ዓመት ለሞላቸው ሴቶች በስድስት ወር ልዩነት ሁለት ጊዜ ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል ከ15 ዓመት በላይ ለሆኑት ደግሞ በስድስት ወር ልዩነት ሦስት ጊዜ ይሰጣል ተብሏል።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሴቶች የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ሊሰጥ ነው
Camera Icon

ፎቶ: ማህበራዊ ሚዲያ

በአማራ ክልል ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በላይ ለሆነ ሴቶች የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ ተነገረ። ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሁሉም የጤና ተቋማት ሊሰጥ በታቀደው ክትባት 570ሺህ 473 ታዳጊዎች እና ሴቶችን ለመከተብ እቅድ ተይዟል።

በዓለም በገዳይነቱ የሚታወቀው የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር (ሰርቪካል ካንሰር) በኢትዮጵያ በገዳይነቱ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የጤና ሚንስቴር መረጃዎች ዕንደሚያሳዩት በዓለም በዓመት 528 ሺህ በላይ ሴቶች በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ይጠቃሉ። ከእነዚህም ወስጥ 270 ሺህ ያህሉ ለህልፈተ-ህይወት ይዳረጋሉ። በአብዛኛው ከ15 እስከ 25 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ሴቶች በበሽታው የሚጠቁ ሲሆን ከ40 ዓመት በላይ በሚገኙ ሴቶች ላይ የሞት መጠኑ ከፍ ይላል።

በአማራ ከልል ጤና ቢሮ የጤና ማበልጸግ፣ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መልሰው ጫንያለው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለስኬታማነቱ እንዲረባረቡ ጥያቄ አቅርበዋል። “በዘመቻ መልክ ለሚሰጠው ክትባት የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ይወጡ” ብለዋል።

የክትባቱ አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ “ከስድስት ወራት በፊት የመጀመሪያውን ዙር ክትባት የወሰዱ ሴቶች ሁለተኛውንና የመጨረሻውን ዙር ክትባት በአሁኑ ዙር ይወስዳሉ” ብለዋል። በኢትዮጵያ በዓመት 4ሺህ 6መቶ ሴቶች በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ይያዛሉ። ከእነዚህም መካከል 70 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ይሞታሉ። 

እንደ አስተባባሪው ማብራሪያ ክትባቱ 14 ዓመት ለሞላቸው ሴቶች በስድስት ወር ልዩነት ሁለት ጊዜ ይሰጣል። በሌላ በኩል ከ15 ዓመት በላይ ለሆኑት ደግሞ በስድስት ወር ልዩነት ሦስት ጊዜ ይሰጣል ብለዋል።