መጋቢት 25 ፣ 2014

የሴቶች ምርጫ እየሆነ የመጣው ሰው ሰራሽ ጥፍር

City: Addis Ababaየአኗኗር ዘይቤ

የጥፍር ፋሽን በአለም አቀፍ ደረጃ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ገበያ ሲሆን ከሁሉም አስተያየት እና ጥናቶች መገንዘብ እንደሚቻለው ይህ የጥፍር ውበት አጠባበቅ እድገቱ ፈጣን መሆኑን ማስተዋል ይቻላል።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

የሴቶች ምርጫ እየሆነ የመጣው ሰው ሰራሽ ጥፍር
Camera Icon

Credit: https://www.beautynailhairsalons.com (Hanita Nail Bar)

የውበት እና የፋሽን ኢንዱስትሪው የተለያዩ አማራጮችን በማቅረብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመነ እና እያደገ መጥቷል። የእጅ ውበት አጠባበቅን በተመለከተ ሰው ሰራሽ ጥፍሮችን ማስተከል በምዕራቡ አለም የሚዘወተር አንድ የመዋቢያ መንገድ ነው። ይህም የውበት ኢንዱስትሪውን መቆጣጠር ከቻሉ ተዘውታሪ የፋሽን ዘይቤዎች አንዱ አድርጎታል። 

ሰራሽ ጥፍሮች በተለያዩ ቀለሞች እና ዲዛይን የተሰሩ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ለየት ላሉ ዝግጅቶች በስተቀር በኢትዮጵያ ሴቶች ዘንድ እምብዛም ያልተለመደና ያልነበረ ቢሆንም አሁን አሁን ግን ብዙ ሴቶች የዕለት ተዕለት የመዋቢያ ምርጫቸው አድርገውት እየታየ ነው።

በመላው ዓለም የሰው ሰራሽ ጥፍሮች ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መጥቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በ Transparency Market Research የቀረበው ጥናት ይህ የፋሽን እና የውበት ዘርፍ ከጊዜ ወደጊዜ በዝመና እያደገ እንደሚሄድ እና የተፈላጊነት መጠኑም እየጨመረ እንደሚሄድ ያሳያል። ለዚህም አንድን ወይም ሁለትን ነገር እንደምክንያትነት ማስቀመጥ ከባድ እንደሚሆን በመጥቀስ፣ ነገር ግን እንደ ኢንስታግራም ያሉት የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ሴቶች ስለ መልካቸው፣ ስለአለባበሳቸው እና ስለአቀራረባቸው ልዩ ትኩረት እየሰጡ እንዲሄዱ ማድረጉ በሰው ሰራሽ ጥፍር ላይ ፍላጎት እንዲጨምር በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያትታል።

በዋነኝነት ሁለት ዓይነት ሰው ሰራሽ የጥፍር ስታይሎች ያሉ ሲሆን እነሱም አክሪሊክክ እና ጄል ናቸው። የጄል ሙሌት በመባል የሚታወቀው የጥፍር ውበት ሙሌት የሚከናወነው በሶስት የሂደት ደረጃ ሲሆን ይህም በመጀመርያ የሚተከለውን ሰው ሰራሽ ጥፍር ለመያዝ እንዲያመቸው ተፈጥሯዊውን የሴቷን ጥፍር ሙሉ ለሙሉ የመሞረድ፣ የመቦረሽ፣ እና በጥቂቱ ቆዳዋን የማንሳት ስራ ይሰራል። በመቀጠል ሰው ሰራሽ ጥፍሩን በተፈጥሯዊ ጥፍሯ ላይ ለማጣበቅ የሚያስችለውን ጄል በመጠቀም ሙሌቱ ይከናወናል፣ የተለጠፈው ጥፍር በ UV መብራት ውስጥ ከ 30 ሰከንድ እስከ ሁለት ደቂቃዎች እንዲደርቅ ይደረጋል። በመጨረሻም እንደተጠቃሚዋ ፍላጎት ጥፍር ቀለም በመቀባት ስራው ይጠናቀቃል።

አክሪሊክ የጥፍር አይነት ደግሞ ሰው ሰራሽ ጥፍሩን ለመለጠፍ በተዘጋጁ ፈሳሽ እና ዱቄት ኬሚካሎች በመታገዝ በጥፍር ላይ የሚለጠፍ ሲሆን የአሰራር ሁኔታው ጥንቃቄ የተሞላበት፣ ረዘም ያለ ደቂቃዎችን የሚወስድ እና ከጄል አንጻር ከሰው ጥፍር ጋር ተመሳሳይነቱ የጎላ ነው።

እነዚህን አገልግሎቶች ለመጠቀም የሚጠየቀው ዋጋ ተጠቃሚዋ እንደምትመርጠው ቦታ የሚለያይ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በአብዛኛው ከሁለት መቶ ብር እስከ ዘጠኝ መቶ ብር ባለው የዋጋ ልዩነት መሃል አገልግሎቱን ማግኘት ይቻላል።

ሰው ሰራሽ የጥፍር ማስዋብ ስራ በወጣት የፋሽን ተከታዮች ዘንድ ተወዳጅ እየሆነ መምጣቱ ለብዙ የውበት ባለሙያዎች ራሱን የቻለ የስራ እድል ለመፍጠር ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። ለዚህም ማሳያ የሚሆኑት አሁን አሁን በከተማችን ላይ በብዛት የሚስተዋሉት የጥፍር ውበት ሳሎኖች ናቸው።

በመስቀል ፍላወር አካባቢ ከሚገኙ የጥፍር ውበት ሳሎኖች መካከል አንዱ በሆነው አሃዱ የጥፍር ስቱዲዮ ውስጥ አገልግሎት ከሚሰጡት ባለሙያዎች መካከል አንዷ የሆነችው ሳሮን ተስፋዬ፣ “የጥፍር ውበትን ለመጠበቅ ሰው ሰራሽ ጥፍሮችን ማስተከል አዲስ ነገር ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይ ወጣት ሴቶች ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ ሆኗል፣ ለምሳሌ እኔ በግሌ በቀን ከአራት እስከ አምስት ደንበኞችን ልሰራ እችላለሁ” ስትል ከውበት አኳያም ከተፈጥሮው ጥፍር ይልቅ ቀለማቸውን ሳይለቁ በመቆየት እና ከጥንካሬ አኳያ ተመራጭ ያደርጋቸዋል በማለት አስተያየቷን ትሰጣለች።

ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ የሚገኘው “ዲቫ የጥፍር ሳሎን” መስራች እና የውበት አጠባበቅ ባለሙያ የሆነችው ሄለን ይስማውም ከሳሮን ሀሳብ ጋር በመስማማት ይህ የሰው ሰራሽ ጥፍር ለሴቶች ተጨማሪ በራስ የመተማመን መሳርያ መሆኑንም ትናገራለች።

በዲቫ ሳሎን አገልግሎቱን ስትጠቀም ያገኘናት መታሰቢያ ታደሰ የተባለች ወጣት፣ “እኔ ትንሽ ጊዜ ያለሰው ሰራሽ ጥፍር ስቀመጥ ባዶ የሆንኩ ያህል ይሰማኛል፣ ጭር ይልብኛል” በማለት፣ ለሰው ሰራሽ ጥፍር ያላትን አድናቆት ትገልጻለች። አያይዛም መጥፎ ጎኑን ስትናገር፣ "አንዴ ከተሰራሽ በኋላ ተፈጥሯዊው ጥፍርሽ እንደበፊቱ አይሆንም ይሰባበራል ከዛ አኳያ መጠቀሙን መቀጠል የውዴታ ግዴታሽ ይሆናል" ትላለች።

ይህ የሰው ሰራሽ ጥፍር ከጤና አኳያስ እንዴት ይታያል ብለን ጥያቄ ያቀረብንላቸው የራንክ የቆዳ ህክምና መስራች ዶክተር ሩት ሊካሳ በበኩሏ፣ “እኔ የምመክረው አርቴፍሻል ጥፍርን አለመጠቀም ነው” በማለት በአብዛኛው ጥፍር ማሳደግ የሚያስቸግራቸው ሴቶች አርቴፊሻል ጥፍርን መጠቀማቸው ወይም ጥፍራቸው ጥሩ የሆኑ ሴቶችም ለውበት ሲሉ መጠቀማቸው እንደማይመከር እና ጥፍርን ለመለጠፍ የሚጠቀሙት ኬሚካል እንዲሁም የማድረቂያው ጨረር በተደጋገመ ቁጥር ከጥፍርም በተጨማሪ ጥፍርን የሚደግፈውን ቆዳም የማስረጀት ባህሪ እንዳለውና ለተለያዩ የፈንገስና የባክቴሪያ በሽታዎች እንደሚዳርጉ ትገልፃለች። ዶ/ር ሩት በተጨማሪ እንደምትናገረው፣ "በሌላ በኩል ተፈጥሯዊ ጥፍራችን ጤናው የሚረጋገጠው በየጊዜው በሚያሳየው እድገት እና መተካካት ነው፣ ነገር ግን የሰው ሰራሽ ጥፍር ይሄን እድገት በመጫን ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ልክ አይሆንም"።

ታሪክ እንደሚያሳየው የጥፍር ውበት እና ፋሽን አመጣጥን ከአንድ ባህል እና ሀገር ጋር ብቻ ማዛመድ ይከብዳል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥናት ያካሄዱ ተመራማሪዎች በ5000 ዓ.ዓ ገደማ ግብፃውያን የሞቱ ከብቶችን ግብዓት በመጠቀም ሰው ሰራሽ ጥፍር በመስራት እና ሂና በመቀባት ለመዋቢያነት ይጠቀሙት እንደነበር ይናገራሉ። በዛው ዓመት ገደማ እንደዚሁ የህንድ ሴቶችም ላስቲክ ልባችን በመጠቀም ጥፍራቸውን ያስጌጡ እንደነበር ተፅፏል። 

አመቱ በውል ባይታወቅም የመጀመርያውን ዘመናዊ የሰው ሰራሽ ጥፍር ሰርታ ያቀረበችው ሀገር ቻይና እንደሆነች የሚነገር ሲሆን ይህም የእንቁላል አስኳል፣ ሰም፣ አበባ፣ ቀለማማ ድንጋዮችን እና ዝልግልግ ቅባቶችን በመጠቀም ይሰሩት እንደነበር ተፅፏል። 

አሁን አሁን የጥፍር ፋሽን በአለም አቀፍ ደረጃ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ገበያ ሲሆን ከሁሉም አስተያየት እና ጥናቶች መገንዘብ እንደሚቻለው ይህ የጥፍር ውበት አጠባበቅ እድገቱ ፈጣን መሆኑን ማስተዋል ይቻላል።

አስተያየት