ኅዳር 7 ፣ 2015

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገነባው መንገድ የፓርኩን ብዝኃ ህይወት ለአደጋ ማጋለጡ ተገለፀ

City: Bahir Darወቅታዊ ጉዳዮች

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን እ.ኤ.አ በ1978 በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገነባው መንገድ የፓርኩን ብዝኃ ህይወት ለአደጋ ማጋለጡ ተገለፀ
Camera Icon

ፎቶ፡ homesecurity.press

በ1958 ዓ.ም ከለላ ተበጅቶለት የተቋቋመው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በየጊዜው በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ለአደጋ ተጋልጧል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የፓርኩ ብዝኃ ህይወት እየተመናመነ መምጣቱን ተከትሎ ዩኔስኮ በ1988 ዓ.ም ፓርኩን በዓለማችን አደጋ ውስጥ ካሉ ቅርሶች መካከል መድቦት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በፓርኩ ውስጥ እየተገነባ ያለው የመንገድ ስራ በፓርኩ የብዝኃ ህይወት ላይ ተጨማሪ አደጋ ደቅኗል። 

“ችግሩ እንዲፈታ ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በተደጋጋሚ በደብዳቤ ቢጠየቅም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም” ይላሉ የኢትዮጵያ ዱር አንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ናቃቸው ብርሌ። 

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለሁለት ከፍሎ የሚያልፈው መንገድ ቀደም ብሎ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። መንገዱ ፓርኩን አቋርጦ ወደ ጃናሞራ፣ ፀለምት እና የዳአ ከተሞች የሚወስድ ነው። 

ይህ መንገድ በፓርኩ ብዝኃ ሕይወት ላይ አደጋ እያስከተለ በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ባቀረበው ምክረ-ሀሳብ መሰረት በተለዋጭ መንገድ እንዲተካ ታስቦ ከአስር ዓመት በፊት ስራው ተጀምሯል። አዲስ የተጀመረው መንገድ 70 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን ወጭው በፌዴራል መንግስት እንደሚሸፈን ተገልጿል።

የፓርኩ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው እንደሚናገሩት “የመንገድ ፕሮጀክቱ ለበርካታ ዓመታት ተጓቷል። በዚህም በፓርኩ የብዝኃ ሕይወት ላይ አደጋ ተጋርጧል”። እንደ ጽ/ቤቱ ኃላፊ ገለፃ የግንባታ ማሽነሪዎች እጥረት፣ የፀጥታ ችግር እና ለመንገድ ግንባታ የሚያስፈልገውን ቦታ ከሶስተኛ ወገን ነፃ የማድረግ (የወሰን ማስከበር) ችግር ለመንገዱ ግንባታ መጓተት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በሰሜን ጎንደር የሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ያዋስኑታል። ከ20 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችም ኑሯቸው በፓርኩ ዙሪያ በመሆኑ ህይወታቸው ዛሬም ድረስ ከፓርኩ ጋር የተሳሰረ ነው።

ለዓመታት በተጓተተው የመንገድ ግንባታ ምክንያት በፓርኩ አንዳንድ ቦታዎች ማለትም ሳንቃበር፣ ጨነቅና ቧሂትን በመሳሰሉት የፓርኩ ክፍሎች የዱር እንስሳት የሚራቡበትና የሚንቀሳቀሱበት አካባቢዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። 

ቦታዎቹ በተለዋጭ መንገድ ግንባታ ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜ በዶዘር እየታረሱ ነው። ይህም በፓርኩ ብዝኃ ሕይወት ላይ ጥፋት ሊያስከተል እንደሚችል ያለውን ስጋት የፓርኩ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ከ1200 በላይ የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎች በፓርኩ ውስጥ ሲገኙ ከእነዚህ ዝርያዎች መካከል አብዛኞቹ ሀገር በቀል መሆናቸው ይነገራል።

በሀገሪቱ የሚገኙ ፓርኮችን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤት መሆኑ ይታወቃል። የባለስልጣኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ናቃቸው ብርሌ፣ የተለዋጭ መንገድ ግንባታው በፓርኩ የብዝኃ ሕይወት ደህንነት ላይ አደጋ ማስከተሉን ይስማማሉ። ችግሩን ለመፍታትም ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጋር ተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን ይገልጻሉ።  

መንገዱ የሚሰራው በፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን ባለቤትነት ሲሆን የስራ ተቋራጮቹ ደግሞ የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣንን ጨምሮ፣ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት እና አኪር /አወጣኸኝ ኪሮስ/ የተባለ የግል ተቋራጭ በጋራ ናቸው። 

የመንገድ ስራው ከተጀመረ ከዓመታት በኋላ አኪር የተባለው የግል ተቋራጭ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ስራውን ሳያስረክብ አቋርጦ መውጣቱ ተገልጿል። 

በዚህም አኪር የተባለው ድርጅት አቋርጦት የወጣው የመንገድ ግንባታ ክፍል ለመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት መሰጠቱን ከሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል። 

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን ምላሽ ለማካተት አዲስ ዘይቤ ያደረገችው ጥረት አልተሳካም። 

በሌላ በኩል ፓርኩ ያለበትን አሁናዊ ሁኔታ ለማወቅ በየጊዜው የዱር እንስሳት ቆጠራ ይካሄዳል። የዱር እንስሳት ቆጠራ በፓርኩ የሚገኙ የዱር አንስሳትን በፆታ፣ በእድሜ እና በዓይነት ለይቶ ለማወቅ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከወን ተግባር ነው።

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊው አቶ አበባው እንደሚያስረዱት የዱር እንስሳት ቆጠራ በዓመት ሁለት ጊዜ ይደረጋል። “ዋሊያ፣ ቀይ ቀበሮ እና ጭላዳ ቆጠራ ከሚደረግባቸው የዱር እንሰሳት ዋነኞቹ ናቸው” ይላሉ። እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ላለፉት ሁለት ዓመታት በበጀት እና የፀጥታ ችግር ምክንያት ዓመታዊ የዱር እንስሳት ቆጠራ በፓርኩ አልተደረገም።

ነገር ግን ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው የቆጠራ ውጤት አበረታች እንደነበር የፓርኩ ኃላፊ ይናገራሉ። በዚህም መሰረት ከ20,000 በላይ ጭላዳ ዝንጀሮ መኖሩ ሲረጋገጥ፤ የቀይ ቀበሮ ቁጥር ከ 25 ወደ 75 እድገት ያሳየ ሲሆን ዋልያ አይቤክስ ከ900 በላይ ደርሶ ነበር።

የዘንድሮው የዱር እንስሳት ቆጠራ ሲጠናቀቅ የሚገለፅ መሆኑን የፓርኩ ኃላፊ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በሳንቃ በር እና መስገጎ በሚባሉ ቦታዎች 330 ሄክታር በላይ ቦታ በሰደድ እሳት ተቃጥሎ እንደነበር ይታወሳል። 

እንደ አቶ አባባው ገለፃ ፓርኩ ደርሶበት የነበረው መጠነ ሰፊ ቃጠሎ የተለያዩ አካላት ባደረጉት ርብርብ የተቃጠለው ከፍል ሙሉ በሙሉ ማገገም ችሏል።

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከአዲስ አበባ ከተማ 800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንዲሁም ከታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ በስተሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ 120 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል። ይህ ድንቅ እና ማራኪ የመስህብ ስፍራ 412 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በኢትዮጵያ ረዥሙን የራስ ዳሽን ተራራን ጨምሮ በማራኪ መልክዐ ምድር የታደለ ነው።

ይህን ስፍራ ለመጎብኘት በርካታ ጎብኚዎች ከመላው ዓለም ይመጣሉ። በሰሜኑ ጦርነት እና በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት የጎብኝዎች ቁጥር ከመቀነሱ በፊት በ2011 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከ32,000 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች ፓርኩን ጎብኝተውት እንደነበር ከፓርኩ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አቶ ታደለ ሞላ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፖርክ አስጎብኚዎች ማህበር ሰብሳቢ ነወ። በኮቪድ-19 እና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ባለፉት ዓመታት የቱሪስት ፍሰቱ ሙሉ በሙሉ ቆሟል በሚባል ደረጃ ደርሶ እንደነበር ያስታውሳል።

በዚህም ከ120 በላይ የሆኑት የማህበሩ አባላት ለከፋ ችግር ተዳርገው የነበረ ሲሆን፣ ሆኖም በፓርኩ ከ2014 ዓ.ም ነሃሴ ወር ጀምሮ የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር መሻሻል እያሳየ መሆኑን አቶ ታደለ ይገልጻል። ይህም ቢሆን ቀድሞ ከነበረው የጎብኚዎች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር፤ ቁጥሩ እጅግ አነስተኛ መሆኑን የአስጎብኚዎች ማህበር ሰብሳቢው አቶ ታደለ ይናገራል።

በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት ማለትም ባለፉት ሶስት ወራት 240 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎች ፓርኩን የጎበኙ ሲሆን ከዚህም ከ241,542 ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል። በ2014 ዓ.ም ደግሞ 738 ጎብኚዎችን ፓርኩን ጎብኝተዋል። በ2013 ዓ.ም ፓርኩ እጅግ ዝቅተኛ የጎብኚዎች ቁጥር ያስመዘገበ ሲሆን ይህም 2,238 ጎብኚዎች ብቻ ነበር።

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፖርክ በኢትዮጵያ ብቻ ከሚገኙት ብርቅዬ እንስሳት መካከል ዋልያ አይቤክስ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ የምኒልክ ድኩላ እና ቀይ ቀበሮ የመሳሰሉትን ብርቅዬ እንስሳትን በውስጡ ይዟል። በተመሳሳይም ፓርኩን መጠለያ ያደረጉ ከ200 የሚበልጡ የአዕዋፍ ዝርያዎች ይገኙበታል። ከእነዚህም ወስጥ አምስቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው። 

አስተያየት