ከዓመታት በፊት የተነገረ ቁም ነገር አዘል ቀልድ እንዲህ ይላል፥ በአንድ የሀገራችን ከተማ ላይ ነው አሉ፤ የሚሾሙት የመንግስት ባለስልጣናት ሁሉ “የህዝቡን የዘመናት ጥያቂ የሚመልስ” ያሉትን የጤና ጣቢያ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ያስቀምጣሉ። ጤና ጣቢያው ግን አይገነባም። የመንግስት ተሿሚ በተቀያየረ ቁጥር በሚቀመጡት የመስረት ድንጋዮች የተማረረው ህዝብ “ከዛሬ ነገ ይሰራል” እያለ በተስፋ ቢጠብቅም ጠብ የሚል ነገር ጠፋ። በመጨረሻ ህዝቡ ለበላይ አካል “ወደ ሌላ ከተማ ሄደን እንድንታከም የመሰረት ድንጋዮቹን ሰብሰባችሁ መንገድ ስሩልን” ብሎ ደብዳቤ ጻፈ ይባላል።
ዛሬም ድረስ በሀገራችን ብዙ ቦታዎች የህዝቡን ችግር ይቀርፋሉ ተብለው የታሰቡ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ፕሮጀከቶችን ለመገንባት የተቀመጡት የመሠረተ ድንጋዮች ፍሬ ቢስ ሆነው ቀርተዋል። ለግንባታው ከህዝብ የተሰበሰበው፣ ከለጋሽ ሀገሮች በብድርና በእርዳታ የተገኘው አያሌ ገንዘብ የውሃ ሽታ ሲሆን ታዝበናል።
ይህን ጉዳይ በተመለከተ የጎንደሩ የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር በቅርብ ዓመታት ውስጥ በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦላቸው፣ በተስፋ ሲጠበቁ ስለቀሩት ፕሮጀክቶች የሚከተለውን አጠናቅሯል።
ጎንደር ከተማ ከ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከአስር በላይ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ቃል የተገባ ቢሆንም ብዙዎቹ ሳይፈጸሙ ቀርተዋል። በየዓመቱ እና በየሁለት ዓመቱ ከንቲባ ሲቀያየር፣ ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ፣ የተበጀተው ገንዘብ ባክኖ፣ ቃል የተገባውም ሳይፈፀም እና ለዚህም ተጠያቂ አካል ሳይኖር ከቀሩባቸው ከተሞች መካከል ጎንደር አንዷ ነች።
በጎንደር ከተማ በመንግስት በጀት፣ በህዝብ ገንዘብ እንዲሁም በጎንደር ዲያስፖራ ወገኖች ድጋፍ በርካታ መሰረተ ልማቶች እየተሰሩ ያሉ፣ የተቋረጡ እና ጭራሱንም የግንባታ ስራ ካልተጀመረባቸው ብዙ ፕሮጀክቶች ውስጥ ጥቂቶቹን ለመዳሰስ ተሞክሯል።
ዘመናዊ የእግር ኳስ ስታዲየም ግንባታ
“ፋሲል ከነማን ያክል ተፎካካሪ ክለብ ይዛ ዘመናዊ ስታዲየም ሊኖራት ይገባል” በሚል የክለቡ ደጋፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት ጎንደርን የዓለም አቀፍ ስታዲዮም ባለቤት ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀመረ። በህዳር ወር 2012 ዓ.ም እስከ 45 ሺህ ህዝብ ሊያስተናግድ የሚችል ስታዲየም ለማሰራት የዲዛይን ስራው እየተዘጋጀ መሆኑን የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን አስታውቆ ነበር።
በወቅቱ የክልሉ መንግስት ፕሮጀክቱን በፍጥነት ሰርቶ ለማጠናቀቅ ማቀዱ በከተማዋ ነዋሪዎችና በእግር ኳስ ደጋፊዎች ዘንድ ትልቅ ደስታን ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ቃል የተገባው ሳይተገበር የውሃ ሽታ ሆኖ መቅረቱ ብዙዎችን አሳዝኗል።
በጎንደር ከተማ አዘዞ ክ/ከተማ አይራ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ እስታዲየሙ እንደሚገነባ ይፋ ሆነ። ይህን የሰሙ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ፕሮጀክቱ ለወጣቶች ያለውን አስተዋፆ በማሰብ የአቅማቸውን ለማገዝ ፈቃደኛነታቸውን ገልፀው ነበር።
የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ጨዋታዎቹን የሚያከናውነው ወደ ሌላ ከተማ በማቅናት መሆኑ ይታወቃል። ይህን በማስቀረት ቡድኑ በከተማው እና በደጋፊው ፊት እንዲጫወት፤ ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ የጎንደር ከተማ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ በትኩረት እየሰራ መሆኑን በጊዜው አሳውቆ የነበረ ቢሆንም እስከ ዛሬ ማለትም እስከ ህዳር 2015 ዓ.ም ምንም አይነት ጅማሮ አልተካሄደም።
በተጨማሪም ፋሲል ከነማ ልምምድ የሚያደርግበት ነባሩ ስታዲየም ደረጃውን ለማሳደግና እድሳት እንደሚደረግለትም ቃል ተገብቶ የነበረ ቢሆንም ምንም አይነት እንቅስቃሴ የሌለ መሆኑን አዲስ ዘይቤ ተዟዙራ ተመልክታለች።
ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የወጣትና ስፖርት ሃላፊ አቶ አበበ ላቀው “ስለ ዘመናዊ ስታዲየም የስራ ሁኔታ እውቀቱ የለኝም” የሚል ምላሽ ተሰጥተዋል። የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ በበኩላቸው ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ እስካሁን ቦታውን ለስታዲየም ተሰይሞ ከመያዝ ውጭ ምንም አይነት የስራ እንቅስቃሴ እንደሌለ ገልፀዋል።
ሰሜን በጌምድር የባህልና የምርምር ማዕከል ግንባታ
ጎንደር ለቱሪዝም መስፋፋት ምቹ የሆኑ የኪነጥበብና የኪነ ህንፃ፣ የታሪክና የባህል እሴቶች መገኛ ብትሆንም ራሱን የቻለ የባህል ማዕከል ባለመኖሩ ባህልና ኪነጥበባዊ እሴቶቿን በተደራጀ መልኩ ማስተዋወቅ አለመቻሉ በተደጋጋሚ ይነገራል።
ይህንንም ለመቅረፍ በማሰብ ሰሜን በጌምድር የባህልና የምርምር ማዕከልን ለመገንባት ህዳር 27 ቀን 2012 ዓ.ም የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።
የመሰረተ ድንጋይ በማስቀመጥ ስነስርአቱ ላይ በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ መላኩ አለበል እንዲሁም በጊዜው የጎንደር ከተማ የባህል ማዕከል ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አስፋው ገብረማሪያም እንዲሁም የከተማዋ ከንቲባ እንደተገኙ የጊዜው ሪፖርቶች ይናገራሉ።
የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነስርዓት ላይ ማዕከሉ የአማራን ህዝብን በተለይ የጎንደርን ታሪክ ባህልና ትውፊትን በማሰባሰብና በማስተዋወቅ ህዝባዊ አንድነትን ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንዳለው ገልፀው እንደነበር ይታወሳል።
ይህ ፕሮጀክት በጎንደር ነባር የእግር ኳስ ሜዳ ከፍ ብሎ ባለው የቅርጫት ኳስ መጫወቻ አጠገብ መሰረተ ድንጋዩ የተጣለ ሲሆን በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ማለትም በ 2015 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የጎንደር ባህል ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ አስፋው ገብረማሪያም ተናግረው ነበር።
ይሁንና አዲስ ዘይቤ ቦታው ደረስ ሄዳ እስከተመለከተችበት ጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ድረስ ምንም ነገር ያልተጀመረ መሆኑን ታዝባለች ።
የወጣቶች የመዝናኛ ማዕከል
የጎንደር ወጣቶች በእረፍት ጊዜያቸው የመዝናኛ ቦታ የማጣት ችግርን የተረዳ የመሰለው ከተማ አስተዳደሩ ከዓለም ባንክ ጋር በመቀናጀት የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ለማስገነባት በ2011 ዓ.ም ገደማ የመሰረተ ድንጋይ አሰቀምጦ ነበር።
ይህ የወጣት ማዕከል 'ፒያሳ' ተብሎ በሚጠራ ስፍራ አፄ በካፋ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ይገኛል። መዝናኛ ማዕከሉ በጎንደር ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ባለቤትነት እና በሃና ተፈራ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ አማካኝነት ግንባታው የተጀመረ ቢሆንም ዛሬ ላይ የማዕከሉ ስራ ቆሞ ይታያል።
ማዕከሉ ለአምስት ዓይነት አገልግሎቶች ማለትም የመረብ ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ዘመናዊ ሱቆች፣ አረንጓዴ ልማትና መናፈሻ እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ መፀዳጃ ቤት እንዲኖረው ታስቦ ግንባታው የተጀመረ ቢሆንም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ በጅምር ቀርቷል።
የማዕከሉ አጥር ግንባታ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በዓለም ባንክ ወጭ የተጠናቀቀ ሲሆን ሃና ተፈራ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ 5ቱን የመዝናኛ አገልግሎቶች ግንባታ በ13 ሚሊዮን 373 ሺህ 65.15 ብር በጀት በ 2014 አ.ም አጠናቆ እንዲያስረክብ ውል የወሰደ ቢሆንም ከ2014 ዓ.ም ጥር ወር ጀምሮ ግንባታው ተቋርጧል።
የዚህን ፕሮጀክት ስራ ማቆም በተመለከተ አዲስ ዘይቤ ወደ ጎንደር ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አቅንታ የፕሮጀክቱን ስራ አስኪያጅ አቶ ተረፈ አስመላሽ እንዲሁም ምክትል ስራ እስኪያጅ አቶ ታዘባቸው ነጋን አነጋግራለች።
“ለግንባታው መዘግየት ከፕሮጀክት ቦታ ላይ ያለ የቴሌ ታወር ቶሎ አለመነሳት፣ የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረት መኖር፣ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ተሽከርካሪዎች ለግዳጅ ይፈለጉ ስለነበር አሸዋ እና ድንጋይ ጭኖ የሚያመጣላቸው መኪና ማግኘት አለመቻሉ ዋና ምክንያቶች ናቸው” ይላሉ አቶ ተረፈ አስመላሽ።
የመዝናኛ ማዕከሉን ለማጠናቀቅ ሁለት ወር ጊዜ እንደሚወስድባቸው የገለፁት አቶ ተረፈ፤ የሜዳ ንጣፍ፣ የጣራ ስራ እና የኮንክሪት እንዲሁም የማስዋብ ስራ እንደቀራቸው ተናግረው “በተያዘለት በጀት እስከ ታህሳስ 30 እናጠናቅቃለን” ብለውናል።
አቶ ታዘባቸው ነጋ በበኩላቸው የበጀት ምንጩ ከዓለም ባንክ፣ ከክልል እና ከከተማ አስተዳደር የተገኘ መሆኑን ገልፀው የእቃዎች የዋጋ ንረት ለስራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል።
የገነት ተራራዎችን የማልማት ስራ
በጊዜው የነበሩት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ ሲናገሩ በከተማዋ የገነት ተራራ የማልማት ፕሮጀክትን ጨምሮ የከተማ አስተዳደርን የቢሮ ህንፃ፣ የስድስቱን ክፍለከተሞች ህንፃ፣ የ 25 ቀበሌ ቢሮዎችን እንዲሁም የመስቀል አደባባይን የማስፋፋትና የፖሊስ ካምፕ መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶችን ዲዛይን ለማስራት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቶ ነበር።
በዚህም መሰረት የጎንደር ከተማ አስተዳደር በ 2013 ዓ.ም አራት ትልልቅ ዲዛይኖችን ለማሰራት ከኢትዮጵያ ዲዛይን ስራዎች ሱፐርቪሽን ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
ስለሆነም ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የገነት ተራራን የማልማት ፕሮጀክት ሲሆን ለዲዛይን ስራው 21 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ወደ ስራ ተገብቶ ነበር።
ይህ የገነት ተራራን የማልማት ፕሮጀክት በ 2014 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ቃል የተገባ ቢሆንም እስከ 2015 ዓ.ም ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደሌለ ታዝበናል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የሆኑት አቶ ባዮህ አቡሃይ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ የገነት ተራራን የማልማት ፕሮጀክት በዲዛይን ስራ ላይ መሆኑን ገልፀው “በ2016 ዓ.ም ሙሉ ስራውን እናጠናቅቃለን” ብለዋል።
በዓለም ባንክ እና በተለያዩ አጋር አካላት ተገንብተው ለአግልግሎት ክፍት የሆኑ ፕሮጀክቶችስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
በጎንደር ከተማ ከለጋሽ ሀገራት በተገኘ ብድር እና እርዳታ በመገንባት ላይ ያሉ እና ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ። በሌላ በኩል በከፍተኛ ወጪ ተገንብተው ያለአገልግሎት ቆመው የቀሩ ፕሮጀክቶችም አሉ።
ከእነዚህ መካከል በዓለም ባንክ ድጋፍ ግንባታው ተጠናቆ ባለታወቀ ምክንያት አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየው የጎንደር አዘዞ ገበያ ማዕከል አንዱ ነው። የገበያ ማዕከሉ በ2011 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ገብቶ የነበረ ቢሆንም ባልታወቀ ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጦ ከ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሚያሳዝን መልኩ የቆሻሻ መጣያና የመፀዳጃ ቦታ መሆኑን አዲስ ዘይቤ መዘገቧ ይታወሳል።
ይህ የገበያ ማዕከል ባለሶስት ወለል (G+2) ሲሆን ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን ያስተናግዳል ተብሎ የታሰበ ነበር። በገበያ ማዕከሉ ውስጥ ለመስራት ቦታ የደረሳቸው ባለእድለኞችም የመስሪያ ስፍራ ሳያገኙ ከገበያ ማዕከሉ ውጭ አስፓልት ዳር እየተገበያዩ ይገኛሉ።
የጎንደር ከተማ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ሚያዚያ 03 ቀን 2011 ዓ.ም የገበያ አዳራሹ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ከሚችለበት ደረጃ ላይ መሆኑን ተመልክተው ነበር። ከዚያ በኋላ አንድም የመንግስት አካል ብቅ ብሎ አይቶት እንደማያውቅ አዲስ ዘይቤ በስፍራው ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል።
የገበያ ማዕከሉ ከመገንባቱ በፊት በቦታው ላይ በጉሊት ንግድ የሚተዳደሩ በርካታ ሰዎች ነበሩ። ማዕከሉን ለመገንባት በ2006 ዓ.ም ነጋዴዎቹን ከቦታቸው በማንሳት ግንባታው ሲያልቅ ቦታ እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸው ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ ተደረገ።
ታድያ ማዕከሉ ተገንብቶ በተጠናቀቀበት ጊዜ ለነጋዴዎች መከፋፈል ሲጀመር ጉዳዩ እንደታሰበው አልነሆነም። ሁሉም ከቦታው የተነሱት ማህበረሰቦች የድርሻቸውን ማግኘት ባለመቻላቸው እስከ አሁን ድረስ ከተማ አስተዳደሩን በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የገበያ ማዕከሉ ለመፀዳጃነት እየዋለ መሆኑን አዲስ ዘይቤ መዘገቧን ተከትሎ በ15 ሺህ ብር ወጪ ማዕከሉ ሊፀዳ መቻሉ ተገልጿል። ምንም እንኳ የገበያ አዳራሹ ለጊዜው የተፀዳ ቢሆንም ለነጋዴዎች ተከፋፍሎ ሰራ አልጀመረም። ነጋዴዎች ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ ቢያነሱም እስካሁን መፍትሄ እንዳላገኙ ይናገራል።
እነዚህ ከላይ የጠቃቀስናቸው ለጎንደር ከተማም ሆነ ለሀገር ጠቃሚ ሆነው ሳለ ችላ የተባሉ ፕሮጅክቶች ናቸው። እነኚህ ጥቂት ማሳያ ምሳሌዎች ናቸው እንጂ ሁሉ ለማዘርዘር የሚቻል አይደለም።
ዛሬም “የህዝቡን የዘመናት ጥያቄ የሚመልስ የልማት ስራ” እየተባለ በየቦታው ተጥለው ዳዋ የዋጣቸው የመሰረት ድንጋዮች በዙሪያችን አሉ። ይገነባሉ የተባሉት ፕሮጀክቶችም ከምን እንደደረሱ የሚታይ ሃቅ ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ ለዚህ ሁሉ ፕሮጀክቶች በከንቱ መቅረት፣ መጓተትና ኪሳራ ተጠያቂ አካል አለመኖሩ ነው።