ሐምሌ 26 ፣ 2013

ከዘር ፍጅት እስከ ፖለቲካዊ ተገማች አደጋዎች በኢትዮጵያ

City: Bahir Darፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

“በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያሉ እርስ በርስ የሚደጋገፉ ታላላቅ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?” የሚለው የአብዛኛው ኢትጵያዊ ጥያቄ ሲሆን ወቅታዊውን ሁኔታ ለመተንተን የሚያግዝን ሁኔታ ግምገማዎች እና ቃለ-መጠይቆችን በማካሄድ ጽሑፍ ተሰናድቷል።

Avatar: Ayele Addis
አየለ አዲስ

Ayele Addis is an award winner Journalist, Journalism, Trainer, Researcher, and Media & Communication Development Consultancy for Thomson Reuters' Foundation, Africa News Channel, Amhara Media, and Journalists Association. Ethiopian Mass Media Action (EMMA News), ARMA Media Production.Woldia University and Bahir Dar University and founder of Journal of Ethiopian Media and Communications.

ከዘር ፍጅት እስከ ፖለቲካዊ ተገማች አደጋዎች በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ በለውጥ ንፋስ አውንታዊ እና አሉታዊ ማዕበል እየተናጠች ነው፡፡ ሕብረተሰቡ በለውጥ ተስፋና ጉጉት፣ በግጭትና ጦርነት ስጋት ያልተገመተ የስሜት ጫና ውስጥ ይገኛል። ብዙ ያልጠሩ፣ የማይገመቱ ጉዳዮች ትንተናችን ላይ ተጽዕኖ ቢኖራቸውም ወቅቱን እና መፃዒውን የኢትዮጵያ ሁኔታ አመላካች ናቸው፡፡

“በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያሉ እርስ በርስ የሚደጋገፉ ታላላቅ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?” የሚለው ጥያቄ የነገ ሁኔታ የሚያሳስበው የአብዛኛው ኢትጵያዊ ጥያቄ ነው፡፡ ወቅታዊውን ሁኔታ ለመተንተን እና ነገን ለመተንበይ እንዲያግዝ የገዥውን ፓርቲ የግምገማ እና የሪፖርት ሰነዶች በማገላበጥ፣ ቃለ-መጠይቆችን በማካሄድ ይህንን ጽሑፍ አሰናድተናል።

የዚህ ጽሑፍ ትኩረት “ሥር-ሰደድ የኢኮኖሚ መዋቅር ቀውስ፣ የፖለቲካ አሰተዳደር ተልዕኮ አፈጻጸም መዳከም እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ እሴት እጦት ናቸው” የሚሉ ሦስት ዋና ዋና ሐገራዊ ተግዳሮቶች ላይ የሚመረኮዝ ነው።

የገንዘብ ሚንስትር ድኤታ የሆኑት ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ብልጽግና ፓርቲ ባዘጋጀው የምርጫ ቅስቀሳ ቪድዮ እንደሚሉት “ሥር ሰደድ የሆነው የኢኮኖሚ ቀውስ መገለጫዎች ከቁጥጥር ውጭ በመውጣት ላይ የሚገኘው ሥራ አጥነትና ኑሮ ውድነት ወይም የዋጋ ንረት ይገኝበታል።” ለዚህ ሀገራዊ ተግዳሮት የሚኖር አረዳድና ተግባራዊ ምላሽ ከአመራር አመራር፤ ከተቋም ተቋም እና ከድርጅት ድርጅት የተለያየ ነው ሲል በ2012 ዓ.ም የብልፅግና ፓርቲ ያወጣው ሰነድ ያመለክታል። ይህ መሰል ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮት ተጋርጦ ባለበት ሁኔታ በተወሰኑ የፌደራልና የክልል መንግሥታዊ ተቋማትና የድርጅቶች የስልጣን እርከን ውስጥ ያለው የሥራ ተልዕኮ አፈጻጸም መዳከም ብሎም መቆም ቀውሶችን በማባባስ በኩል ከፍተኛ ችግር በመፍጠር ላይ ይገኛል። ይህም ገዥው ፓርቲ እንደ ፖለቲካ መሪ ድርጅት ያለውን አሰሪ መዋቅር፣ ውጤታማ የለውጥ ሥትራቴጂ እና ለዘመኑና በቁጥር እጅግ እየጨመረ ለመጣው ትውልድ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ የአመራር ሥልትና ክህሎትን አለመጠቀሙን ይመለከታል።

በተመሳሳይ አቶ ሞገስ ባልቻ የብልጽና ፓርቲ የስልጠና ዘርፍ ኃላፊ የሀገሪቱ ታላቅ ተግዳሮት የሚሉትን ሲያስረዱ “በሐገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት ለውጡ ምንነትና ሂደት ላይ በሀገሪቱ ገዥ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎቻቸው መካከል እንደዚሁም በአጠቃላይ የሃገሪቱ ዜጎች መካከል የጋራ እሴት ካለመኖሩ በተጨማሪ የያዟቸው አመለካከቶች እና አቋሞች አልፎ አልፎም ተጻራሪ መልክ እየያዙ መቆየታቸው ነው።” በተለይ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የለውጥን ምንነት፣ ዓላማና ግቦች ላይ ብዥታ ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ጎራ ሲፈጠሩ ተስተውለዋል። ይህ የጋራ እሴት መዳከምና መሸርሸር በተለይ በየክልሎቹ ለብሔር ጽንፈኝነት መጦዝ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አበርክቷል።  

ሁሉም ለውጦች የራሳቸው ተቃውሞና የለውጥ ተገዳዳሪ ይኖራቸዋል። የኢትዮጵያን ሁኔታ ፈታኝ የሚያደርገው ግን የለውጡ ሂደት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረግ ሽግግር ብቻ ሳይሆን የሀገር ግንባታ ሂደቱም በጅምር ያለ መሆኑ ነው። በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ባለው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ በሽግግር ወቅት የሚፈጥረውን ሁለንተናዊ ክፍተት በመጠቀም ጸጥታ የሚያደፈርሱ የፖለቲካ አዝማሚያዎች ቢኖሩም ዋናው ተግዳሮት ግን ከዚህም ላቅ ያለ ነው።

ዋናው ተግዳሮት የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥታት በጠንካራ መሠረት ላይ ባልተገነባበት ሁኔታ ዴሞክራሲን የመትከል ሂደቱ የሚያስከትለው የሕልውና አደጋ ነው። የፌድራሊዝም መምህሩ ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ እንደሚሉት “በየክልሎቹ የብሔር ፖለቲካ ጥያቄዎች በፈሉባቸውና ፖለቲካን ከግል የሥልጣን ጥቅምና ሀብት የማጋበሻ ሱስ አሻግረው የማይመለከቱ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች በበዙበት ሀገር ሕልውናን አደጋ ውስጥ መግባቱ የሚጠበቅ ነው።” 

በጠባብ አጀንዳዎች የተያዘ ሕዝብና ፖለቲከኛ ዴሞክራሲን ቢፈልግ እንኳን ዴሞክራሲን የሚሸከም የሲቪክ ባህል ህብረተሰቡ ስላላዳበረ ሽግግሩን ፈታኝና በገመድ ላይ የመራመድ ያክል አደገኛ ያደርገዋል ሲልም የወቅቱ ገዥ ፓርቲ የወቅቱን ሁኔታ ይገመግማል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያሉት ታላላቅ ተግዳሮቶች የሚገለጡባቸው በርካታ ማሳያዎች ቢኖሩም አምስት ዋና ዋና ጉዳዮችን እንመለከታለን፡፡

1. የብሔር ፖለቲካ ፅንፈኝነት አዝማሚያ

በየክልሎቹ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ በኩል ለረዥም ጊዜ የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠባብ ሆኖ በመቆየቱ ምክንያት ደካማና በቂ አቅም የሌላቸው ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ከሀገራችንም ባሻገር አፍሪካን የሚያምሳት በዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ የተገኘውን የመቀራመት አባዜና የብሔር አጀንዳ ብቻ የተጠናወታቸው ሰዎች የሚበዙባቸው መሆናቸው ነው። በዚህም ምክንያት ፓርቲዎቹ ከዐቅመ ቢስነታቸው ባለፈ በውስጣቸው ጽንፈኛ የብሔር አቀንቃኞችን የሠገሠጉ በመሆናቸው በብሔር አጀንዳቸው ሀገሪቱን ለማመስ እንደአንድ አጋጣሚ ሁኖ ተስተውሏል።

የገዥው ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዓለሙ ስሜም ከላይ በተጠቀሰው ቪድዮ ላይ “ኢትዮጵያን እየፈተናት ያለው የብሔር ነጋዴነት የአንድ ብሔር ተቆርቋሪ በመምስልና የዚያን ብሔር ሰዎች ሊያሰባስቡ ይችላሉ የሚባሉ የብሶት ጥያቄዎችን በመሰብሰብ ለግል ጥቅም (ለሥልጣን፣ ለክብር፣ ለገንዘብ፣ ለዕውቅና፣ ወዘተ) ማዋል ነው። የብሔር ነጋዴው ብሔሩን የሚፈልገው የብሔሩን ችግር ለመፍታት አይደለም። ይልቁንም በልፋትና በጥረት ሳይሆን በአቋራጭ ሀብት ለማጋበስ እንደ መደበቂያ ዋሻ እና ከሕግ የማምለጫ መንገድ ያደርገዋል። ወድድርና ፉክክር በበዛበት ባለንበት ዘመን የብሔር ተወካይ ነኝ ባዩ በችሎታና በጥረት ላይ ያልተመሰረተው ጥቅምና ፍላጎቱ ጥያቄ ሲነሳበት “ብሔሬ ተነካ” ተብሎ ሕዝብ በሆታ እንዲነሳለት ይገለገልበታል። የብሔሩን ታሪካዊ ብሶቶች የሚፈልጋቸውም ለመፍትሔ ሳይሆን ለፖለቲካው ገበያ ይሆናል። ቁስሉን ዕያሳየ ከሰዎች ጠቀም ያለ እርዳታ የሚያገኝ ነዳይ ቁስሉን ለመታከምና ለመዳን እንደማይፈልገው ሁሉ የብሔር ብሶቶችን እያቀነቀነ የሚያተርፍ የብሔር ነጋዴም የብሔሩ ችግሮች እንዲፈቱ አይፈልግም።”ይላሉ፡፡            

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወዴት በሚል በብልጽግና ፓርቲ የተዘጋጀው ሰነድ ሁኔታውን እንዲህ አስቀምጦታል፡፡ የብሔር አጀንዳዎች በኢትዮጵያ መደበኛው የፓርቲ ፖለቲካ ለፋክክር ስለማያመቻቸው ተጠያቂነት የሌለበትን የአቀንቃኝነት (የአክቲቪዝም) ፖለቲካ ለትግላቸው ይጠቀሙበታል። በዚህም እነዚህ አካላት የትግላቸው አካለሄድ ሃያ አራት ሰዓት ግጭት ይፈለፍላሉ፤ ያመርታሉ። የብሔር አራማጆችም ዋነኛ የፖለቲካ ግብይት ስልታቸው ግጭትና ብጥብጥ ነው። የማኅበራዊ ሚዲያው ደግሞ የዘመኑ ዋነኛ የግጭት ማምረቻ ቦታቸው ሆኗል። ከፓርቲ ፖለቲካ ወደ አቀንቃኝነት (አክቲቪዝም) ፖለቲካ የተሸጋገሩት ግን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻ አይደሉም። ይልቁንም ገዥው ፓርቲ ራሱ በአቀንቃኝነት ፖለቲካ አቅሉን እየሳተ፣ አባላቱም አመዛዝነው የማይራመዱ እየሆኑ መጥተዋል።

የሐገራችንን የብሔር ፖለቲካ ፍጥጫ መሥመር በመከተል፣ የፖለቲካ አቀንቃኝነትንም በማራመድ፣ የማንነት ጥያቄዎችን በየቦታው በማቀጣጠልና የወረዳ፣ የዞንና የክልል አስተዳደርነት ጥያቄን በመለኮስ፣ በሂደቱ ጥቅም ለማግኘት የሚካሄድን ጥረት በተደጋጋሚ ሲበቅሉ ይስተዋላል። ይህም የወቅቱ የኢትዮጵያ ታላቁ ተግዳሮት አንዱ መገለጫ ነው። ይህ ዓይነት አዝማሚያ በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተች ዴሞክራሲያዊትና ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን የመገንባት ህልምን የሚፈታተን ነው።

2. የጎበዝ አለቅነት አዝማሚያ

የጎበዝ አለቅነት አዝማሚያ ማለት በመርሕና በዕውቀት፣ በድርጅት ፕሮግራምና በሕግ ከመመራት ይልቅ በሕዝብ ግፊትና በጭብጨባ እየታጀቡ፣ ራስን የአንድ አካባቢ አድራጊ-ፈጣሪ አድርጎ መሾም ነው። ለራስም ታጥቆ ሌላውንም አስታጥቆ ወደ አካባቢያው ገዥነት የመቀየር አጥፊ ሕልም ነው። ከዚያም ከፍ ሲል ሕዝብን አሰልፎ የጦርነት ነጋሪት ማስጎሰም ነው። ይህ አደጋ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አጥር እየወጣ በብሔር፣ በሃይማኖት እና ሌሎች አደረጃጀቶች ህዝቡ ውስጥ በመዛመት የክልል መንግሥታትንና ሕዝቡን ሥጋት ላይ እየጣለ መምጣቱ እየተስተዋለ ይገኛል።

ለሀገርና ለሕዝብ ሁለንተናዊ ዕድገትና ሰላም ከመሥራት ይልቅ በየክልሎችና በየዞኖች የጎበዝ አለቃ በመሆን “ውረድ እንውረድ” የሚል አደገኛ አዝማሚያ በሀገሪቱ ተስተውሏል። የጎበዝ አለቅነት የፖለቲካ ምስቅልቅል ምክንያት ሁለተኛው ምዕራፍ ነው። ለፖለቲካ ብልጫ ተብሎ የተጀመረው የብሔር ግጭትን የመቀስቀስ ዝንባሌ ቀስ በቀስ ጀማሪዎችን መልሶ እያታለለ ለሕዝብ ያሰቡ ሲመስላቸው ሕዝብን ከጀርባችው አሰልፈው የጦርነት ነጋሪት እንዲጎስሙ ያደርጋቸዋል። በብዙ አቅጣጫ የሚስተዋለው አካሄድ ከዚህ አዝማሚያ ጋር የተያያዘ ነው። በዕውቀት፣ በማስተዋል እና በመርሕ ከመራመድ ይልቅ ሁሉም በየጎራው የአክቲቪስት ሞገስ ፈላጊና የጭብጨባ ሱሰኛ የመሆን አዝማሚያ ይስተዋልበታል።

3. በሀገር አለመረጋጋት ውስጥ ከሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ የሚደረግ የዘራፊዎች ሙከራ

ቀደም ሲል ያለምንም ጠያቂና ቁጥጥር የሀገር ሀብትና ንብረትን በአንድ በኩል ከመንግሥት መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ላይ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን በመጠቀም የዘረፉትን፤ በሌላ በኩል በኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት ጤናማ የገበያ ውድድርን በሚያኮላሽና የሀገርንና የመንግሥትን ገቢ በሚያስቀር ተራ የውንብድና ሥራ ውስጥ በመግባት ያካበቱትን ሕገ-ውጥ ገንዘብ ለማሸሽ በማሰብ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ውስጥ ግጭት የመፍጠር ተግባር ውስጥ የገቡ ጸረ-ለውጥ ግለሰቦች ተበራክተዋል። በዚህ የጥፋት ተግባር ምክንያት የሚፈጠረው ትርምስና አደጋ ከሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ እድል እንደሚሰጣቸው በማመን እነዚህ ግለሰቦች በዝርፊያና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የሰበሰቡትን ገንዘብ ለዚሁ የጥፋት ተልዕኮ እያዋሉት ይገኛሉ።

4. የግጭት ፖለቲካን ሥልጣን ለመያዝ እንደሥልት የመጠቀም አዝማሚያ

በሕጋዊና በሕገ መንግሥታዊ መንገድ በሚደረግ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በመሳተፍ ክልላዊም ይሁን ፌደራላዊ ሥልጣንን በሕዝባዊ ይሁንታ ከማግኘት ይልቅ ከምርጫው አስቀድሞ የተለያዩ መሰረተ ቢስ ምክንያቶችን እየደረደሩና አማላይ ሰሞነኛ አጀንዳዎች እየፈጠሩ ሁከትና ረብሻ በመቀስቀስ የግጭት ፖለቲካ የማራመድ አባዜ የተጠናወታቸው ኃይሎች በመላው ሀገሪቱ ተበራክተዋል። እነዚህ ኃይሎች የሕዝቡንና የራሳቸውን ዘላቂ ፍላጎትና ጥቅም ከነባራዊ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች አንጻር መፈተሽ ያልቻሉ ናቸው ለማለት ይቻላል።

5ሃይማኖታዊ ግጭቶችን በመቀስቀስ ሐገራዊ ለውጥን የመቀልበስ ሙከራ

በኢትዮጵያ ሃይማኖትን መሰረት የሚያደርጉ ግጭቶች በአንዳንድ የሃገራችን ክፍሎች አልፎ አልፎ ይስተዋሉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ዕየታየ ያለው ሃይማኖት ነክ ቁርሾ ግን ከቀደመው ጊዜ የሚለይበት ባህርያት አሉት፡፡ ይህም ግጭቶቹ የእምነቱ ተከታዮች ሃይማኖታቸውን ከሌላው ጥቃት ለመከላከል ወይም ለመጠበቅ የሚያካሂዱት አለመሆኑ ነው፡፡

ባለፉት ቅርብ ዓመታት የተስተዋሉ ሃይማኖት ነክ ጥቃቶች በአንድ አከባቢ የሚኖሩ የተለያዩ እምነት ተከታዮች አንዱ ከሌላው ጋር በቀጥታ የሚጋጩባቸው አልነበሩም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከአከባቢው አንፃር አነስተኛ ተከታይ ያላቸው ቤተ-እምነቶችና አማኞች በሌሎች የሚጠቁበት መልክአ-ምድራዊ ቅርፅ የያዘ ነው፡፡ የሃይማኖት ተከታዮቹ ሙሉ በሙሉ በመልክአ-ምድር ተከፋፍለው የሚኖሩ ባይሆንም፣ በአንዳንድ የሃገሪቱ ክፍሎች ግን አንዱ ከሌላው መበላለጡ አልቀረም፡፡ ይህ ደግሞ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቤተ-እምነቶች በቀላሉ እንዲጠቁ አድርጓቸዋል፡፡

ሃይማኖት ነክ ጥቃቶቹ በሌላው ዓለም እንደተለመደው አክራሪ ሃይማኖተኞች የሚፈጥሯቸው አይደሉም፡፡ ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ያላቸው አማኞች ከሁሉም ሃይማኖቶች የሉም ባይባልም አሁን ላለው መጠቃቃት ግን ሃይማኖታዊ አክራሪነት መንስኤ ሲሆን አይስተዋልም፡፡ ከዚህ ይልቅ ፅንፈኛ ብሄርተኞች እና የግጭት ፖለቲካ ነጋዴዎች ከጥቃቶቹ ጀርባ ጎልተው ይታያሉ፡፡ እነዚህ አካላት በአንዱ የሃገሪቱ ክፍል አነስተኛ ተከታይ ያላቸውን ቤተ-እምነቶች ላይ ጥቃት በማስደረስ እሳት ይጭራሉ፤ በሌላኛው የሃገሪቱ ጫፍ ደግሞ የመልስ ምት እንዲሰጥ ይቆሰቁሳሉ፡፡

የግጭት ፖለቲካ አስተባባሪዎች በሁለቱም ጫፍ የሚለኩሱት እሳት በቶሎ ማጥፋት ካልተቻለ በሂደት ወደ ተደራጁ የሃይማኖት ግጭቶች እንዳያድጉ ያሰጋሉ፡፡ አሁን ካለው የሃገራችንና የቀጠናው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሃይማኖታዊ ግጭቶች አንዴ ከተጀመሩ የውጭ ጣልቃ ገብነት እያስከተሉ ልንወጣው ወደማንችለው አዘቅት ሐገሪቱን ሊከቷት ይችላሉ፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ” እንዲሉ በብሄር ፅንፈኝነት እየተማጠች ባለች ሃገር ሃይማኖታዊ ግጭት ሲታከልበት ወደ ከፋው የገደል ጫፍ ኢትጵያን የሚገፋን ይሆናል፡፡

አቶ አህመድ አባጊሳ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማኅበራት ኃላፊ “አሁን ያለው ሐገራዊ ለውጥ ከሕዝቡ ተፈጥሯዊ የለውጥ ፍላጎት እና በገዥው ፓርቲ ውስጥ በነበሩ የመታደስን ሃሳብ ያቀነቀኑ እና የለውጥ ድርጅታዊ ባሕሪያት የመነጩ ናቸው። በመሆኑም ለውጡ ሕዝባዊ መሠረት ይዞና በድርጅታችን የመታደስ ጠንካራ ድርጅታዊ ባሕልና አሰራር እየተመራ መሆኑ እውነት እንደሆነ ሁሉ የለውጥ ተገዳዳሪ አከላት ያላቸው ሐሳብም በተቀናጀ መንገድ እየተመራ መሆኑ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። ሕዝባዊና ድርጅታዊ መሠረት ባለው በለውጥ እንቅስቃሴውና እና በፀረ-ለውጥ አዝማሚያው መካከል ያለው ልዩነት የሕዝባዊ መሠረት ጉዳይ ነው።” ይላሉ፡፡

ከዚህ መሰረታዊ ሁኔታ በመነጨም በኢትዮጵያ ያለው ሐገራዊ ለውጥ በሚያስቀጥሉና ለውጡን በሚገዳደሩ ጉዳዮች መካከል ፉክክር እየተካሄደ ነው። የለውጥ ሃሳቦችም ሆኑ “የለውጥ ሃሳቦች ተገዳዳሪ አካላት” ተብለው የሚፈረጁ ቡድኖች የሚያመነጫቸውና የሚታገልላቸው ኃይል ያለ በመሆኑ ጉዳዩ ውሎ አድሮ የኃይሎች አሰላለፍ ጉዳይ ሁኗል። በመሆኑም በለውጡ ውስጥ የሚታዩ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችንና የኃይሎችን አሰላለፍ መፈተሽ ያስፈልጋል። ለውጡን ለመቀልበስና ለማጨናገፍ የሚጥሩ ኃይሎች አጋጣሚው ይዞላቸው የመጣውን ሽኩቻና ባላንጣነት እንደ መጨረሻ መልካም እድል በመመልከት የሞት ሽረት ትግል ያካሂዳሉ። ዓላማቸውም እነሱ በኢኮኖሚና በፖለቲካ የበላይነት መቀጠል ካልቻሉ አካባቢውን አተራምሰው የራሳቸውን ሰላማዊ ደሴት መፍጠር እንችላለን የሚል ጠባብ ፍላጎትና አለማስተዋል ይታይባቸዋል። ከኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፈላጭ ቆራጭነት ባልተጠበቀ ጊዜ የተነሳ ኃይል የሚያሳየው የእልኸኝነትና የማን አለብኝነት ስነ-ልቦናዊ ጠባይም ጉዳዩን የከፋ ያደርገዋል።

ሕብረተሰቡ በለውጥ ተስፋና ጉጉት፣ በግጭትና ጦርነት ስጋትና የኢ-ተገማችነት ስሜት ውስጥ ይገኛል። የለውጥ ተስፋና ጉጉት በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍሬ ማፍራት ጀምሮ ቀጣይነቱ ሳይረጋገጥ በቀላሉ ህዝቡ ወደ ጨለምተኝነትና ተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በሁሉም አቅጣጫ ይታያሉ። በሌላ በኩል የሐገሪቱ ለውጥ ተቃራኒ ኃይል ሆኖ ከቆመው አካል ጋር የሚዛመዱ ችግሮች የሆኑት ግጭት፣ መፈናቀል፣ ግድያ፣ የኑሮ ውድነት የመቀስቀስ፣ የማቆየት እና እየተበራከተ እንዲመጣ የማድረግ ስልት ህዝቡ በለውጥ ኃይሉ ላይ የነበረው እምነትና ቅቡልነት እየተሸረሸረ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡ ይህም በቀላሉ ለጥቃት የሚጋለጥ እየሆነ ይመጣና በስተመጨረሻም ለውጡን ሊያጨናግፈው ይችላል።

በአጠቃላይ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት  እየተፈተነባቸው ያሉ አራት ተቀባይነቱን ሊያጣባቸው የሚችሉ ዕድሎች አሉ። እነሱም በሽግግሩ ጊዜ እየተሰሩ ያሉ ስሕተቶች፣ ተቋማዊ ተግዳሮቶች፣ በለውጥ ጊዜ በሕዝቡ ዘንድ የሚፈጠሩ ብዥታዎችና ለውጡን ወደ ዕኩይ ዓላማ ለመምራት የሚችሉ የለውጡ ተቃራኒ አካላት አዝማሚያዎች ናቸው። ለውጡን ከአደጋ ለመጠበቅ ደግሞ እነዚህን ተያያዥ አራት ፈተናዎች መቋቋም ይጠበቅበታል።

ኢትዮጽያ ብዙ ውዝፍ የቤት ሥራዎች ያሉባት ሀገር ነች። የሀገረ መንግሥት ግንባታው አሁንም በሁሉም ዘንድ ተመሳሳይ መግባባት ያልተደረሰበትና ተጨማሪ ጥረት የሚጠይቅ በይደር ያለ ሥራ ነው። የኢትዮጵያዊነት ግንባታ በግድ የሚጫን ሳይሆን በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የሚመሰረት ለማድረግ ብዙ መሥዋዕትነት የተከፈለበት እና ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑ ባይካድም ዛሬም ድረስ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ሊጠናቀቅ አልቻለም። አቅጣጫውንም ለማወቅ አሁንም አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ሕዝቦችና ዜጎች ጥቃት በደረሰባችው ቁጥር “ኢትዮጵያ ምኔ ናት?”፣ “ኢትዮጵያዊነትስ ለምኔ?”፣ “የፌደራል ሥርዓቱ ምን ዋስትና ሰጠኝ?” እያሉ በመጠየቅ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ የለውጥ ኃይሉን የዕለት ተለት ስራና እንቅስቃሴ ፈታኝና ከባድ አድርገውታል።

ሌላው ተግዳሮት ሕዝቦችና ዜጎች በመንግሥት ተቋማት እና በመንግሥታቸው ብቃት ላይ ሙሉ ለሙሉ እምነት የሚጥሉበት ሁኔታ በተጨባጭ መፍጠር አለመቻሉ ነው። ሕዝቦችና ዜጎች በሀገረ-መንግሥቱ ቅርጽ ማለትም በፌደራል ሥርዓቱ አወቃቀር ላይ ገና መግባባት ላይ አልደረሱም። ይህ ማለት ደግሞ ከብሔረ መንግሥት ግንባታው በተጨማሪ የሀገረ መንግሥት ግንባታውም ገና ተፈላጊው ደረጃ ላይ አለመድረሱን ያመለክታል። ባጭሩ በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በፌደራል ሥርዓተ መንግሥቱ ጉዳይ ላይ ጭምር መሠራት ያለበት በርካታ ሥራ መኖሩን ያሳያል። ከብሔረ-መንግሥትና ሀገረ-መንግሥት ግንባታ እንጭጭነት ባሻገር የዴሞክራሲ ሥርዓት እና ባሕል አለመጎልበት በአንድ በኩል፣ የኢኮኖሚ መዋቅሩ ደካማነት ደግሞ በሌላ በኩል በአመራሩ ፊት የተደቀኑ ዓበይት ተግዳሮቶች ናቸው።

በዚህ ወቅትም ጥያቄው አንድም የለውጥ አዝማሚያው የለውጡ ሐሳብ የበላይነት እያገኘ ለውጡ በሚፈልገው አቅጣጫ ተጉዞ የሚጠበቀውን ውጤት ከሚያስገኝበት ደረጃ ላይ ይደርሳል፤ ወይም ተገዳዳሪ-የለውጥ ኃይሎች አዝማሚያ የበላይነትን ይዞ የለውጡን አቅጣጫ ከሀዲዱ ያስተዋል፤ ያጨናግፈዋል የሚል ነው።

አስተያየት