ሐምሌ 24 ፣ 2013

ጎርጎራ፡ ተሸሽጋ የኖረችው የታሪክ አድባሯ ትንሳኤ!

City: Gonderኢንዱስትሪባህል ልማትቱሪዝም

ቀደም ባለው ዘመን የመንግሥት ስልጣን ላይ የሚገኙ አመራሮች በድብቅ ይዝናኑባት እንደነበረ የሚነገርላት ‹‹ጎርጎራ›› በገበታ ለሐገር ፕሮጀክት ተፈጥሯዊ ይዘቷን በጠበቀ መልኩ እንደምትለማ ሲነገር ትኩረት ስባ ነበር።

Avatar: Ghion Fentahun
ግዮን ፈንታሁን

ጎርጎራ፡ ተሸሽጋ የኖረችው የታሪክ አድባሯ ትንሳኤ!

ጎርጎራ ከጎንደር በስተምዕራብ 63.4 ኪሎ ሜትር፣ ከባህር ዳር በጣና ሀይቅ 78 ኪሎ ሜትር፣ ከባህር ዳር በአዘዞ መስመር 220 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በጣና ዳርቻ የምትገኝ ጥንታዊና ታሪካዊ አነስተኛ የባህር ዳርቻ ከተማ ናት፡፡ በጣና ሐይቅ ላይ ለሚደረገው ጉዞም እንደ መዳረሻ ወደብ በመሆን ታገለግላለች፡፡ በ1312 ዓ.ም. የተቋቋመችውና የ701 ዓመት እድሜ ባለፀጋዋ “የደብረሲና ማርያም” አንድነት ገዳም ለጎርጎራ ከተማ መመስረት መሰረቱን ጥላለች። “የደብረሲና ማርያም” አንድነት ገዳም የተቋቋመችው በአፄ አምደ ጽዮን የንግሥና ዘመን እንደሆነ የገዳሙ አባቶች ይናገራሉ፡፡ በዚያን ዘመን በአካባቢው ለያዥ ለገናዥ ያስቸገሩ ሽፍታዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሽፍታዎች የአካባቢውን ነዋሪ ረፍት በመንሳታቸው ህዝቡ ለንጉሡ አቤቱታ ያቀርባል፡፡ የህዝቡን አቤቱታ ተከትሎ ንጉሡ የጦር አዛዡን ኤስድሮስ ወደ ሽፍቶቹ አቅንቶ አደብ እንዲያስገዛቸው ትዕዛዝ ያስተላልፋል፡፡

በዘመኑ ለዘመቻ ሲኬድ ታቦት ይዞ መንቀሳቀስ ልምድ ነበር፡፡ ኤስድሮስ ወደ ጦርነት ሲያመራ የድንግል ማርያምን ታቦት በመያዝ ለውጊያ ይዘምታል፡፡ ኤስድሮስ ሽፍቶቹን አሸንፎ ድል ስለቀናው ለማስታወሻነት የደብረሲና ማርያም ቤተክርስቲያንን እንዳሳነፀ የገዳሙ ታሪክ ያወሳል፡፡ የአፄ አምደ ጽዮን የጦር ባለሟል ኤስድሮስ የትውልድ ስፍራ ደብረሲና በመሆኑ “የደብረሲና ማርያም” ስያሜ ከጦር አዛዡ የትውልድ መንደር ጋር እንደሚተሳሰርም የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ “ጎርጎራ” የሚለው ስያሜም አካባቢው ላይ ሸፍተው ከነበሩት አራት ሽፍቶች አንዱ የሆነው “ባሻ ጐርጐጎር” የተወሰደ እንደሆነ በአፈ-ታሪክ ይነገራል፡፡

በሌላ በኩል በአፄ ሱስንዮስ ዘመን መንግሥት በ1604 ዓ.ም. ንጉሡ ዋና መቀመጫቸውን ከጉዛራ ወደ ጎርጎራ አዘዋውረው የመናገሻ ከተማ እንዳደረጓት የጎርጎራ ታሪክ ይነግረናል፡፡ የአፄ ሱስንዮስ ልጅ የሆኑት አፄ ፋሲለደስ በንግሥና ዘመናቸው መጀመሪያ ላይ በዋና ከተማነት የተጠቀሙባት ይህችን ጥንታዊት ከተማ እንደሆነ ከታሪክ መዛግብት ማጣቀስ ይቻላል፡፡ በወቅቱ በጎርጎራ የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ የንጉሡን መናገሻ ከተማ ከጎርጎራ ወደ ጎንደር እንዲዛወር ገፊ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡ የጎርጎራ ከተማ ኋላ መቅረትም ከዚህ ክስተት ማግሥት ይጀምራል፡፡ የነገሥታቱ የቤተ-መንግሥት ፍርስራሾች ዛሬም በቦታቸው ለታሪክ ምስክርነት ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ ጎርጎራ ለዘመናት ተረስታ ቆይታ በአፄ ኃይለሥላሤ ዘመን መነቃቃት እንድትችል ንጉሡ ጥረት አድርገዋል፡፡ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ለእረፍትና ለመዝናናት የሚመርጧት ከተማ እንደነበረችም የከተማዋ ነባር ነዋሪዎች በትዝታ ወደ ኋላ ተጉዘው ያስታውሳሉ፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ ከልማት ተነጥላ ኖራለች፡፡

አቶ ወርቁ እንግዳ የጎርጎራ ነዋሪ የሀገር ሽማግሌ ናቸው፡፡ ስለጎርጎራ ህዝብ ተናግረው አይጠግቡም፡፡ አቶ ወርቁ “የጎርጎራ ህዝብ በደስታ ብቻ ሳይሆን በሀዘንና በችግር ወቅትም ተናጠላዊ ኑሮ አያውቅም፤ ስራንም በጋራ የመስራት እሴቱ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ልማት ለመስራት ምቹ ነው” ይላሉ፡፡ በመቀጠልም አቶ ወርቁ “ጎርጎራ ከዚህ በፊት ተዘንግታ የኖረች ከተማ ናት፡፡ የጎርጎራ መልማት ከጥቅል ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ባሻገር ለልጆቻችን ሰፊ የስራ ዕድልን ይፈጥራል” በማለት የጎርጎራን መልማት በተስፋ ይጠብቃሉ፡፡

ጐርጐራ የደብረሲና ማርያም መቋቋምን ተከትሎ የተቆረቆረች በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ውብ ከተማ ነች፡፡ ይህች የመልማት ፀጋን በጉያዋ ታቅፋ የያዘች ጥንታዊት ከተማ ለዓመታት አስታዋሽ በማጣት ታሪክና የተፈጥሮ ፀጋዋ ላይ ተኝታ ኖራለች፡፡ ጎርጎራ በተፈጥሮ ሀብት እጅግ የበለፀገች አካባቢ ናት፡፡ ጎርጎራ በቱሪዝም ኢንደስትሪ፣ በሆቴልና መዝናኛ፣ በስፖርት፣ በግብርና ዘርፍ በእርሻና እንስሳት ማድለብ፤ በመስኖ ልማት፣ አትክትና ፍራፍሬ እንዲሁም በአበባ ልማት ዘርፍ ምቹ የሆነ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆን የሚችልም የልማት ቀጣና ናት፡፡ በሌላም በኩል ጎንደርና ጎጃምን በልማት ለማስተሳሰር የምታስችል ‘ኮሪደር’ ናት፡፡

በልማት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላት ጎርጎራ ዛሬ ላይ ከገባችበት ድባቴ ለመንቃት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ የ“ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት የከተማዋን ቀጣይ ዕድል ለመወሰን ከደጃፏ ደርሷል፡፡ ጎርጎራ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ ይህን ሀብት በአግባቡ ማልማት ከተቻለ ዓለም አቀፍ ዘመናዊ የባሕር ዳርቻ መዝናኛ ከተማ በማድረግ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ሆና ከራሷ አልፋ ለሀገር ኢኮኖሚ ታላቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላለች ተብሎ ይታመናል፡፡ ጎርጎራ ከተፈጥሮና ታሪካዊ ሀብቷ ባሻገር እንደሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ሁሉ ማኅበረሰቡ በጋራ የሚኖርባት ከተማ ናት፡፡ ጎርጎራ ከውቡ ጣና ሀይቅ ጋር የምትዋሰን መሆኗ የምድር ገነት አድርጓታል፡፡ 

ጎርጎራን በገበታ ለሀገር የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ አድርጎ ለማልማት ሀገር አቀፍ ፕሮጀክት ከተቀረፀ ጀምሮ በርካታ ባለሀብቶች ጎርጎራ ላይ ሀብታቸውን ለማፍሰስ ጥያቄ ማቅረባቸውን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር አስታውቋል፡፡ “ገበታ ለሀገር” ጎርጎራን ለማልማት የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ትኩረት በእጅጉ በመሳብ ላይ የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ ለጎርጎራ ፕሮጀክት አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ የሚያስገነባውን ግዙፍ ሪዞርት ጨምሮ ከ100 በላይ የልማት ፕሮጀክቶች ቀርበው በምርመራ ላይ እንደሚገኙ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር ያገኘናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አብዛኛዎቹ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚሠማሩ መሆኑንም ማወቅ ተችሏል፡፡ በተለይ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ የሚያስገነባው ሪዞርት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ፕሮጀክት እንደሆነ ታምኖበታል፡፡

የዞኑ አስተዳደር አካባቢው በተገቢው መንገድ እንዲለማ ከቢሮክራሲ የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ባለሀብቶች የሚጠበቅባቸውን ማሟላት እስከቻሉ ድረስ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚደረግም ዞኑ አመላክቷል፡፡ ባለሀብቶች ጎርጎራን በማልማት ለአካባቢው ብሎም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል፡፡

አቶ ደሳለኝ አስራደ የገበታ ለሀገር ጎርጎራ ፕሮጀክት አስተባባሪ ናቸው፡፡ አቶ ደሳለኝ እንደሚሉት ጎርጎራ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ሀብት የታደለ አካባቢ በመሆኑ መሰረተ ልማት በመሟላትና ተፈጥሮውን በመጠበቅ ብቻ አካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ “ተራራዎቹ፣ ሜዳዎቹ፣ ሸንተረሮቹና ሸለቆዎቹ ተፈጥሯዊ ገፅታቸው ባለበት እንዲለሙ ይደረጋሉ” ይላሉ አቶ ደሳለኝ፡፡

ጎርጎራ እግር ጥሎት የተገኘ እንግዳ በተፈጥሮና በታሪካዊ ሀብቶቿ የበለፀገችውን ከተማ ተመልክቶ በአድናቆት እጁን በአፉ ሳይጭን የተመለሰ የለም ይላሉ ነዋሪዎቿ፡፡ ጐርጐራ እንደ ጥንታዊነቷና እንደ ታሪካዊነቷ በእድገት ብዙ መራመድ የነበረባት የወደብ ከተማ ነች፡፡ ጎርጎራ ላይ በመሆን የተንጣለለውን የጣና ሐይቅ ከነግርማ ሞገሱ በማየት ለመደነቅና ከከተማ ጫጫታ ርቆ መንፈስን በሚያድሰው ድንቅ ተፈጥሮዋ የማይረሳ ጊዜን ለማሳለፍ ትክክለኛ አማራጭ ናት። 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት ይፋ የተደረገው “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክትና ከፕሮጀክቱ ማግስት ጀምሮ ጎርጎራ የጠራቻቸው ኢንቨስትመንቶች በጋራ ተሳስረው የጥንታዊቷ ጎርጎራ ከተማ ትንሳኤ እንደሚሆኑ አቶ ይርጋ አይቸው የተባሉ የከተማው ነዋሪ ይናገራሉ፡፡ ጎርጎራ የወደፊቷ የአፍሪካ ምርጧ የቱሪዝም የወደብ ከተማ በማድረግ የሚገባት ከፍታ ላይ ለመድረስ በመንደርደር ላይ ትገኛለች፡፡

አስተያየት