“ሁለት ልጆቼን በግል ትምህርት ቤቶች አስተምራለሁ። ቤት ኪራይ አለብኝ። ባለቤቴም ልክ እንደ እኔ በኮንስትራክሽን ስራ ውስጥ መሆኗ ችግራችንን የከፋ አድርጎታል” ይላሉ በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት ስራ የፈቱት የግንባታ ባለሙያው አቶ ተመስገን።
“በአዲሱ አሰራር ሲሚንቶ እንዲያሰራጩ የተመረጡት አከፋፋዮች ወትሮም በገበያው ላይ የሲሚንቶ እጥረት ሲፈጥሩ የነበሩ መሆናቸው ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል” ይላል በክልሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን ወስዶ እየሰራ ያለው የአማራ ክልል የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማኅበር።
በኢትዮጵያም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ስራ ፍለጋ ሲባዝኑ መዋላቸው ምስክር የማያስፈልገው መራር እውነት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የግንባታ ሥራዎች በየቦታው መበራከታቸው ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ይህም ለብዙ ሺህ ባለሙያዎች የኑሮ መሰረት ሆኗል።
ይሁን እንጂ ዋነኛው የግንባታ ግብዓት በሆነው የሲሚንቶ ምርት ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት ብሎም ከገበያ መጥፋት የግንባታ ባለሙያዎችን ለችግር እያጋለጠ ይገኛል። በየቦታው እየተከናወኑ የነበሩ የግንባታ ሥራዎች በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት መቋረጥ ብዙዎችን ከስራ ወጪ እያደረገ ነው።
በተለይም በባህር ዳር ከተማ የተፈጠረው የሲሚንቶ እጥረት በርካታ የግልና የመንግሰት ኮንስትራክሽን ሳይቶች ስራ እንዲያቆሙ ምክንያት ሆኗል። በከተማዋ በሲሚንቶ መወደድ እና ከገበያ መጥፋት ምክንያት ሥራ የፈቱ የግንባታ ባለሙያዎች ችግር ላይ መውደቃቸውን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
አቶ ተመስገን ሞላ እና ባለቤቱ ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን በግንባታ ስራ ያስተዳድራሉ። አቶ ተመስገን ረጅም ዓመት ልምድ ያላቸው ግንበኛ እንደሆኑ ይናገራሉ። ባለቤታቸውም ወ/ሮ ትግስት ይርጋ በግንባታ ስራ የልስን ባለሙያ ሲሆኑ በትዳራቸው ሁለት ልጆች አፍርተዋል።
እንደ አቶ ተመስገን ገለፃ በባህር ዳር ከተማ በግል እና የመግንስት የግንባታ ሳይቶች ኮንትራት እየወሰዱ ይሰሩ እንደነበር ይናገራሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሲሚንቶ ዋጋ መናር እና ከገበያ መጥፋት ጋር ተያይዞ ስራ በመፍታታቸው ለችግር እንደተዳረጉ ይገልጻሉ። “ሁለት ልጆቼን በግል ትምህርት ቤቶች አስተምራለሁ። ቤት ኪራይ አለብኝ። ባለቤቴም በኮንስትራክሽን ስራው ውስጥ ስላለች ችግሩን የከፋ አድርጎታል” ይላል አቶ ተመስገን።
አቶ ይበልጣል ታደሰ ደግሞ በባህር ዳር ከተማ የመኖሪያ ቤቶችን በግል ኮንትራት ወስዶ በልምድ የሚሰራ ባለሙያ ነው። ባህር ዳር ከተማ ባለው የሲሚንቶ እጥረት ምክንያት ስራ መፍታቱን እና በስሩ ለሚገኙ ሰራተኞች ጭምር ችግር ውስጥ መግባታቸውን ይናገራል። “ቀብድ የተቀበልንባቸውን ስራዎች ሳይቀር ለመመለስ ተገደናል” ይላል አቶ ይበልጣል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሲሚንቶ ዋጋ መናር እና ከገበያ መጥፋት ከትልልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ካላቸው የመንግስት ፕሮጀክቶች አንስቶ እስከ ትንንሽ የግለሰብ ግንባታዎች ላይ ድረስ ጎልህ ተጽዕኖ አሳርፏል።
መንግስት በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የሲሚንቶ ዋጋ መጨመርና እጥረትን ለመቆጣጠር ያስችላል ያለውን አሰራር መዘርጋቱ ይታወቃል። አሰራሩንም የራሱ የሆነ መመሪያ በማዘጋጀት በመመሪያ ቁጥር 908/2014 እንዲያወጣ አድርጎታል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባዘጋጀው መመሪያ በተደገፈው አሰራር መሰረት ሲሚንቶ በወኪል አከፋፋዮችና በችርቻሮ መሸጫ በኩል መሸጥ ቆሟል። በተጨማሪም በአዲሱ አሰራር መሰረት ሲሚንቶ እንደ ፕሮጀክቶች ክብደት እና ቅለት ታይቶ የሚያስፈልገው የሲሚንቶ መጠን የሚወሰን እና በመንግስት ፍቃድ ከተሰጣቸው አከፋፋዮች እንዲረከቡ ይደረጋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በተዋረድ ባለው አደረጃጀት በየከተሞች ያለውን የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ተመን እያወጣ ይገኛል። በዚህም በያዝነው ወር ለሁለተኛ ጊዜ የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ተመን በሁሉም አይነት የሲሚንቶ ምርቶች ላይ ማውጣቱ ይታወሳል።
ይሁንና መንግስት የዘረጋው አዲሱ አሰራር ውጤት እያመጣ አለመሆኑን የሚናገሩ አሉ። በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 14 በህብረት ስራ ማህበር ተደራጅቶ ቦታ ወስዶ ገንባታ የጀመረው አቶ ጀማል አህመድ የሲሚንቶ ችግርን ለመቅረፍ የተዘረጋው አስራር ችግሩን እንዳባባሰው ይገልጻል።
“በቀበሌ ተመዝግበን፣ ሳይታቸን ታይቶ የሚስፈልገን ሲሚንቶ ብዛት ተወስኖ፣ ለአቅራቢው ድርጅት ደብዳቤ ተፅፎልኝ ክፍያ ከፈጸምኩ ሁለት ወር አልፎኛል። እስካሁን ግን ሲሚንቶ ማግኘት አልቻልኩም” ይላል። በዚህም ስራ ለማቆም መገደዱን ገልጿል። እንደ አቶ ጀማል ገለፃ በከተማው የሲሚንቶ ችግርን ለመቅረፍ አዲስ አሰራር ከመዘርጋቱ በፊት ሲሚንቶ በኩንታል እስከ 1200 ብር ይሽጥ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በህገ ወጥ መንገድ እሰከ 2100 ብር እየተሸጠ ይገኛል።
በሌላ በኩል ቀበሌ አካባቢ ለትክክለኛው ሰው ፍቃድ መስጠት ላይ የሚስተዋል ችግር እንዳለ የሚናገሩም አሉ። ግንባታ ሳይጀምሩ የግንባታ ፍቃድ ያላቸው ሰዎች በቀበሌ ተመዝግበው ሲሚንቶ በመውሰድ ለነጋዴ እያስረከቡ እንደሚገኙ ገልጸው፤ በዚህ በኩል መንግስት በቂ ክትትልና ቁጥጥር ሊያደረግ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
300 አባላት ያሉት የአማራ ክልል የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማኅበር በክልሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን ወስዶ እየሰራ ይገኛል። እንደ የማኅበሩ ጸሐፊ አቶ ጋሻው አቧሀይ ማብራሪያ መሰረት አሁን ላይ ያለው የሲሚንቶ ዋጋ መናር እና ከገበያ መጥፋት የማህበሩ አባላት የያዟቸውን ሳይቶች አቋርጠው ስራ እንዲፈቱ አስገድዷል።
እንደ ማህበሩ ጸሐፊ ማብራርያ ሲሚንቶ እንዲያሰራጩ የተመረጡ ነጋዴዎች ወትሮም በገበያው ላይ የሲሚንቶ እጥረት ሲፈጥሩ የነበሩ በመሆናቸው ችግሩን አብሶታል። “በአዲሱ አሰራር ሲሚንቶ እንዲያሰራጩ የተመረጡ አከፋፋዮች አመላመል ሂደት ችግር አለበት። የእኛን ማህበርን መሰል ሌሎች ባለድርሻ አከላት ያሳተፈ አይደልም” ይላሉ የማህበሩ ፀሐፊ አቶ ጋሻው። ማህበራቸው ይህንኑ ቅሬታ ለክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አቅርበው መልስ እየተጠባበቁ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማኅበር ከዚህ በፊት የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ መናር ጋር በተያያዘ “የዋጋ መሻሻያ ካልተደረገ በክልሉ የወሰድኳቸውን ፕሮጅክቶች አቆማለሁ” ማለቱን አዲስ ዘይቤ መዘገቡ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከምትከተለው የነፃ ገበያ ፖሊሲ ጋር በተገናኘ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሲሚንቶ ችግርን ለመቅረፍ በዘረጋው አሰራር ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ። በርካቶች ውስብስብ ችግር ውስጥ ያለውን የሲሚንቶ አቅርቦት እና ስርጭት ችግርን ለመቅረፍ በተዘረጋው አሰራር ተስፋ አድርገዋል። “አሰራሩ ገና መጀመሩ እንደመሆኑ መጠን በሂደቱ የገጠሙ ችግሮች መቅረፍ ከታቸለ አዋጭ መንገድ ነው” ይላሉ አስተያየት ሰጪዎቹ።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የምትከተለው ነፃ ገበያ ፖሊሲ አንፃር አሰራሩ ትክክል እንዳልሆነ አጥብቀው የሚተቹም አልጠፉም። በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የልማታዊ ምጣኔ ሀብት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት አቶ ፋሲል ይትባረክ “በነፃ ገበያ ስርዓት መንግስት በምንም አይነት ሁኔታ ጣልቃ መግባት የለበትም” ይላሉ።
“በሀገሪቱ የተፈጠረውን የሲሚንቶ እጥረት እና ከገበያ መጥፋት በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በጥናት ተመርኩዞ መንግስት መፍታት አለበት” ይላሉ አቶ ፋሲል። በተጨማሪም በሲሚንቶ እጥረት ዙሪያ የተፈጠሩትን የግብዓት እጥረት፣ የስርጭት እና የመሳሰሉትን ችግሮች በመቅረፍ በቂ ምርት እንዲኖር ማድረግ እንደሚገባም ባለሙያው ይናገራሉ።
“በሌላ በኩል አንዳንድ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በተለያዩ ችግሮች በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ ባለመሆናቸው፤ ችግሩ እንዲቀረፍ መንግስት ለፋብሪካዎቹ ድጋፍ ሊደርግላቸው ይገባል። በተጨማሪም ከውጭ የማስገባት አማራጮችን ማየት አለበት” በማለት የምጣኔ ኃብት ባለሙያው አቶ ፋሲል ኃሳባቸውን ያጠቃልላሉ።
የአማራ ክልላዊ መንግስት በርዕሰ መስተዳደሩ ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) አማካኝነት በችግሩ ዙሪያ ከሲሚንቶ ፋብሪካ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።
የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማንኛውም የሲሚንቶ አምራች ፋብሪካ በሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት መመሪያ ቁጥር 908/2014 መሠረት ለተፈቀደላቸው አካላት ብቻ የሲሚንቶ ሽያጭ እንደሚፈጽም ገልጿል። ከተፈቀደላቸው አካላት ውጭ ማናቸዉም ሰው የሲሚንቶ ምርት ለግብይት ይዞ መገኘት እንደማይችልም በመመሪያው ተቀምጧል።
በመመሪያው መሰረት የገዙትን የሲሚንቶ ምርት ከታለመለት ዓላማ ውጪ ለሽያጭ ማቅረብ፣ ለመሸጥ መሞከር ወይም ከተፈቀደለት መስመር ውጪ በማንኛውም ማጓጓዣ ጭኖ መገኘት፣ ማጓጓዝ፣ በንግድ መደብር ወይም በማናቸውም ቦታ አከማችቶ መገኘት የተከለከለ ነው።.ማንኛውም አካል በመመሪያው የተገለጸውን ተላልፎ ከተገኘ በአዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 43 እና አግባብ ባላቸው ሌሎች ህጎች መሠረት በአስተዳደራዊ እና በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን ያትታል።