ሚያዝያ 7 ፣ 2014

የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የቦርድ አባላት ሹመት የሕግ ጥሰት ጥያቄና ቀጣዩ የሚድያ ነፃነት

ወቅታዊ ጉዳዮች

አዲሱ ሹመት ግልጽ በሆነ ሁኔታ የህግ ጥሰት እንደፈፀመና ለቀጣዩ የሚድያ ነፃነት ዋነኛ ማነቆ ሊሆን እንደሚችል ከዘርፉ አካላት አስተያየቶች ተሰንዝረዋል

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የቦርድ አባላት ሹመት የሕግ ጥሰት ጥያቄና ቀጣዩ የሚድያ ነፃነት

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 29/2014 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዘጠኝ የቦርድ አባላትን በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁ የሚታወስ ሲሆን ምክር ቤቱ ሹመቱን ካጸደቀላቸው ግለሰቦች መካከል፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባሏ ዶ/ር አጋረደች ጀማነህ ይገኙበታል።

ይህን ተከትሎም በርካታ የሚድያ ባለድርሻ አካላት ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 በመጣስ ከሕግ ውጪ ሹመት ሰጥቷል በማለት የተለያዩ ቅሬታዎችን አቅርበዋል።  የሕግ መጣስ ተስተውሎባቸዋል ተብለው ከቀረቡት ነጥቦች መካከልም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑ ግለሰቦች በቦርድ አባልነት መካተታቸው እና የቦርድ አባላት ተዋፅዖ ዋናዎቹ ናቸው።

የፖለቲካ ፓርቲ አባላት

በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሠረት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት ከሚመረጡባቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ፤ የፖለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆን አልያም በፖለቲካ ፓርቲ ያልተቀጠረ መሆን እንደሚኖርባቸው ተደንግጓል። ነገር ግን ምክር ቤቱ ካጸደቃቸው የቦርድ አባላት መካከል ሶስት የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባላት ተካተዋል።

የእጩዎች ምልመላ ግልፅነት

የቦርድ አባላት እጩዎች ምልመላ እና የማጽደቅ ሂደት ግልጽ አልነበረም የሚለው ሌላኛው ቅሬታ ያስነሳ ነጥብ ሲሆን፣ በአዋጁ መሰረት የባለስልጣኑ የቦርድ አባላት እጩዎች የመመልመል እና የማጸደቁ ሂደት ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መልኩ መካሄድ አለበት ይላል።

አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 9.2 ሕዝቡ የቦርድ አባላት እጩዎችን እንዲጠቁም እና በእጩ አባላት ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ይደነግጋል። አያይዞም የእጩዎች አመራረጥ ሂደት እና የእጩዎች ዝርዝር ቀድሞ በመገናኛ ብዙኃን ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበትም በግልፅ አስቀምጧል። ይሁን እንጂ በዚህ የእጩ ቦርድ አባላት ምልመላ እና የማጽደቅ ሂደት ህዝብ እንዲሳተፍ የተመቻቸ ዕድል አለመኖሩ ጥያቄ ያስነሳ ነበር። 

የቦርዱ አባላት ተዋፅዖና ሙያዊ ስብጥር

በሶስተኛነት የተነሳው ቅሬታ የቦርድ አባላቱ ተዋፅዖን ይመለከታል። በአዋጁ አንቀጽ 9.5 እንደተደነገገው ከቦርዱ አባላት መካከል፤ ሁለቱ ከሲቪል ማሕብረሰብ፣ ሁለቱ ከመገናኛ ብዙኃን፣ ሁለቱ ለመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ጠቀሜታ እና አግባብነት ካላቸው የተለያዩ ተቋማና የሕብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ሦስቱ አግባብነት ካላቸው የመንግሥት አካላት የተወጣጡ መሆን እንዳለባቸው ቢያትትም በቦርድ ሹመቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቁ 9 አባላት ውስጥ ከመገናኛ ብዙኃን የተወከለ አለመኖሩ ተጨማሪ ቅሬታ አስነስቷል።

የቦርዱ አባላት ስለሚኖርባቸው ኃላፊነት በሚመለከት ደግሞ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራቸውን በተገቢው መንገድ መፈጸም የሚችሉ ከዘርፉ ጋር የተገናኘ የትምህርት ዝግጅት እና ብቃት ያላቸውን እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 የተቀመጡ መስፈርቶችን የሚያሟሉ 9 የቦርድ አባላት አቅርበው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያስሾሙ እና የሹመኞቹ የመጀመሪያው ኃላፊነት የአዋጅ ቁጥር 1238/2013 አፈጻጸም እና የባለስልጣኑን ሥራዎች በበላይነት መቆጣጠር እንደሚሆን ተገልጿል።

243 የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተገኙበት የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ በጸደቀው ሹመት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴንን የቦርዱ ሰብሳቢ፤ የቱሪዝም ሚኒስትሯን ናሲሴ ጫሊን ደግሞ ምክትል ሰብሳቢ አድርጎ ሾሟል። ይህም ከ11 የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ሲገጥመው፤ 17 አባላት ደግሞ ድምጽ አለመስጠታቸው ታውቋል።

በሰብሳቢነት እና በምክትል ሰብሳቢነት ከተሾሙት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተጨማሪ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሀሰን አብዱልቃድር እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት የብልፅግና ፓርቲ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አጋረደች ጀማነህ የቦርዱ አባል ሆነው ተመርጠዋል። በተጨማሪም በሀይማኖታዊ አገልግሎታቸው ከፍተኛ ተቀባይነት ያተረፉ፤ ኡስታዝ ያሲን ኑሩ፣ ቀሲስ ታጋይ ታደለ እና ዶ/ር ወዳጄነህ መሃረነም የቦርድ አባል መሆን ችለዋል። በሌላ በኩል ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ አና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶ/ር መሳይ ገብረማርያም የቦርዱ አባላት ሆነዋል።

በዋና ሰብሳቢነት የተሾሙት ሬድዋን ሁሴን ከ2005-2007 ዓ.ም ድረስ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል። ምክትል ሰብሳቢዋ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በውጪ ቋንቋ እና ስነ-ጽሁፍ እንደሰሩ ተነግሯል። 

የቦርድ አባላት ሹመቱ ሕግን ይጣረሳል? ማስተካከያስ ሊደረግበት ይችላል?

የመንግስትን የውሳኔ ሃሳብ በንባብ ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት በፓርላማ የመንግስት ዋና ተጠሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ ሹመቱን ለተቃወሙ የምክር ቤቱ አባላት ሹመቱ ሕግን ተከትሎ የተደረገ መሆኑን ሲያስረዱ፣ “በተሿሚ የመንግስት አካላት የቀረቡ አመራሮችን በተመለከተ አዋጁ ላይ የተቀመጠውን ሃሳብ መነሻ በማድረግ ነው እንጂ የሚጣረስ አይደለም” በማለት ተናግረው ነበር። አክለውም አመራሮቹ ሲመረጡ እውቀታቸው፣ ልምዳቸው፣ ዝንባሌያቸው እና ከዚህ በፊት የነበራቸው የስራ ውጤት ታሳቢ መደረጉን እና የመንግስት አካላት የተካተቱት አዋጁን መሰረት በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ቅሬታ ካቀረቡ አካላት መካከል ቀዳሚው የሆነው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ሹመቱን፣ “ግልፅ የሆነና የማያሻማ የሕግ ጥሰት ያለበት፣ ሕግን ሳይሸራረፍ መተግበር ያለመቻልን ችግር አጉልቶ የሚያሳይ እና የአገራችንን የሚድያ እድገት በእጅጉ የሚጎዳ በመሆኑ ሕዝብም በሕግ አውጭው ተቋም ላይ እምነት እንዳይኖረው ያደርጋል” ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቃቸውን አዋጆችንና ድንጋጌዎችን ተፈፃሚነታቸውን በትኩረት መከታተል ስለመቻሉ ጥያቄ የሚያጭር ሆኖ ማግኘቱን የሚገልፅ መግለጫ አውጥቷል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ማህበሩ ያወጣው መግለጫ ከመንግስት አካል ምላሽ ስለማግኘቱ እና የማህበሩ ክትትል እስከየት ድረስ እንደሆነ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ጥበቡ በለጠ፣ “እስካሁን ምላሽ አላገኘንም፣ ነገር ግን ጥቂት ጊዜ ብንሰጣቸው ይመልሱልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይህን የሚከታተል እና ጥያቄዎችን የሚያቀርብ ቡድን በማህበሩ ተዋቅሮ ስራውን እየሰራ ነው” ሲሉ መልሰዋል።

እንደፕሬዝዳንቱ ገለጻ የማህበሩ ትኩረት የተቀመጠው ሕገ ደንብ እና አዋጅ መጣሱ ላይ ነው። “ተቃውሟችን በተመረጡት ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ አይደለም፣ ግለሰቦቹ በስራም በልምድም ከፍ ያለ ቦታ እንዳላቸው እሙን ነው። ነገር ግን ሁሉም ተስማምቶ ያስቀመጠውን ሕግ ማክበር ካልተቻለ ለሚድያው መቀጨጭ ምክንያት ነው የሚሆነው” ይላሉ።

አያይዘውም በሀገሪቱ ላይ ለሚስተዋለው የግል ሚድያዎች አለማደግ እና መንገዳገድ የህጉ መላላት ትልቅ መንስዔ መሆኑን በመጥቀስ፣ ህጉን የማስጠበቅ እና ሚድያው ጠንካራ ማገር ላይ እንዲቆም የሚድያ ባለሙያው መንግስት ላይ ጫና ማሳደር እንዳለበት ይገልጻሉ። “የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን በሹመቱ ከማካተቱ ባሻገር በጋዜጠኝነት እያገለገሉ የሚገኙ ባለሙያዎችን ቦርዱ አለማካተቱ ሌላው ትልቅ ችግር ነው፣ ሚድያው ህጉን አክብሮ ቢሰራ እና እድገቱ የተስተካከለ ቢሆን ቀዳሚው ተጠቃሚ የሚሆነው መንግስት ነው” ሲሉም አክለው ተናግረዋል።

የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እና ድንጋጌዎችን በማርቀቁ ሂደት ውስጥ ተዋናይ የነበሩ እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የሕግ ባለሙያ በበኩላቸው፣ “በሹመቱ ላይ የአዋጁ ህጎች መጣሳቸውን ማስተባበል የማይቻል ግልጽ ጉዳይ ነው፣ አዋጁ የመንግስት ውክልና ያላቸው አካላት የቦርዱ አባል እንዲሆኑ የሚደነግገው ሕግ ሲተረጎም ከገዢው ፓርቲ አባላት ውጭ የሆኑ ነገር ግን በመንግስት ኃላፊነት ስር የተቀመጡ ሰዎችን ነው የሚመለከተው። ነገር ግን ከተሾሙት አራት የመንግስት አካላት ውስጥ አምባሳደር ናሲሴ ብቻ ናቸው የፓርቲ አባል እንዳልሆኑ የተነገረው” ሲሉ ተቃውሟቸውን ሰንዝረዋል።

የሕግ ባለሙያው እንዳብራሩት የቦርዱ አባል የሚሆኑ ተሿሚዎች የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደሌለባቸው በይፋ የተደነገገ ሲሆን “ምክር ቤቱ ሹመቱ ሕግ መጣሱን ተቀብሎ ማስተካከያ ማድረግ ወይም በቂ ማብራሪያ መስጠት ይኖርበታል፣ ይህ የማይሆን ከሆነ በህጉ መሰረት ሹመቱን እስከመሻር እና እስከመሰረዝ የሚያደርስ ማስተካከያ ስራ መሰራት ይኖርበታል” ሲሉ አስረድተዋል። አክለውም የሚድያ ሕጉን የሚያሻሽለው አዋጅ ያስፈለገበት ምክንያት በኢትዮጵያ የሚድያ ነፃነትን ለማስከበር እስከሆነ ድረስ ያለምንም ማወላወል ህጉ ሊከበር እንደሚገባ አፅዕኖት ሰጥተዋል። 

ድርጊቱ በምን አላማ ላይ ተመስርቶ እንደተፈጸመ መገመት ከባድ ነው የሚሉት ባለሙያው፣ ሆኖም መንግስት ምናልባት አዋጁን የማስተካከያ እርምት የመውሰድ እቅድ ካለውም ግልፅ ሊያደርገው እንደሚገባ ይገልጻሉ።

በሌላ በኩል በዚሁ ጉዳይ በሀገሪቱ ውስጥ በጋዜጠኝነት ላይ በቀጥተኛነት እየሰሩ የሚገኙ ባለሙያዎች እይታስ ምን ይመስላል የሚለውን ለመመልከት ያነጋገርነው የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው አቶ ታምሩ ጽጌ፣ “በግልጽ የተቀመጠን አዋጅ መጣሱ ጋዜጠኞችን ብቻ ሳይሆን ስለሚድያ ያገባኛል የሚለውን ሁሉ የሚነካ ጉዳይ ነው፣ የሀገሪቱ ሚድያ ሌሎች ብዙ ያልተፈቱ ችግሮች እያሉበት ሌላ በመንግስት እንዳንተማመን የሚያደርግ ችግር መፈጠር የለበትም” በማለት ያስረዳል።

የሚድያ ዘርፉ ዋና ባለስልጣን መስርያ ቤት ከፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ በሆኑ ሰዎች መመራቱ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን ከመከላከል አንስቶ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው እንደሚታወቅ የሚናገረው ታምሩ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን ቅሬታ በመቀበል ስህተት መሰራቱን አምነው ምክር ቤቱ ማስተካከያ እንዲያደርግ እንደሚጠይቁ አምናለሁ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።  

የቀረቡትን ተቃውሞዎች በሚመለከት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ምላሽ ምን እንደሚመስል የጠየቅናቸው የባለስልጣን መስርያ-ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ ቢሯቸው ለዚህ ጉዳይ ምላሽ የመስጠት ስልጣን እንደሌለው እና በአዋጁ አንቀፅ 4(2) መሰረት የባለስልጣን መስርያ-ቤቱ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስከሆነ ድረስ፣ ኃላፊነቱ መመርያዎችን ተቀብሎ ስራ መስራት መሆኑን በመጥቀስ ለቀረበው ቅሬታ ማብራሪያም ሆነ ምላሽ መስጠት የሚችለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን ተናግረዋል።

በጥቅሉ ለቀረቡት ተቃውሞዎች በምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ማብራሪያ አጥጋቢ አይደለም የሚሉ የሚድያ ዘርፉ በርካታ አካላት በተለያዩ መንገዶች ፓርላማው ውሳኔውን እንዲቀይር እየጠየቁ ይገኛሉ። 

አዲሱ ቦርድ በቀጣይ የሚድያ ምህዳር ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል?

ይህ በአዲሱ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ቦርድ እየተነሳበት ካለው የህግ ጥሰትና በቀጣይነት የሀገሪቱ የሚድያ ነፃነት ላይ ሊኖረው የሚችለው ተፅዕኖ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በዘርፉ ሰፊ ተቀባይነትና ልምድ ያላቸው ጋዜጠኞችና የሚድያ ባለሙያዎች አስተያየት ከመስጠት በ “አልሸሹም ዞር  አሉ” ተቆጥበዋል። 

የተሻለ የሚድያ ነፃነትና መብት አየተከበረበት ነው በተባለው በ ጠ/ሚ አብይ አህመድ አስተዳደር በኢህአዴግ ዘመን በድፍረት ኃሳባቸውን ይገልፁ የነበሩት ጋዜጠኞች ዛሬ በእንዲህ አይነት ከሚድያው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባለው ጉዳይ ላይ ዝምታን መምረጣቸው በራሱ የሚጠቁመው አንድ እውነት አለ። 

በአዋጁ አንቀፅ 14 መሰረት የቦርድ አባላቱ የስራ ዘመን አራት አመት ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ቅሬታውን ተቀብሎ ማስተካከያ ካላደረገ ለቀጣይ አራት አመታት ይህ ተቃውሞ የነገሰበት ሹመት በምን አይነት መልኩ ከመገናኛ ብዙኃኑ አካላት ጋር ተስማምቶ ሊቀጥል እንደሚችል ማሰብ ያዳግታል ሲሉ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

የብዙሃን መገናኛ ምሁር የሆነው ታዋቂው ፀሃፊ ቲሞቲ ኩክ የአንድ ሀገር ሚድያ በመንግስት የአይነቁራኛ ቁጥጥርና ዕይታ ውስጥ ሲወድቅ ሊፈጠር ስለሚችለው ሁኔታ ሲያስረዳ፣ "የገዢው መደብ ልሂቃን የሚድያውን ሽፋን ይቆጣጠራሉ፣ የምርመራ ጋዜጠኝነት እምብዛም ይሆናል። አብዛኛው መረጃ በልሂቃኑ በሚመረጡ አቅጣጫዎችና መነፅር ተቃኝቶ ይቀርባል። ጋዜጠኞች ወይ ምርጫ በማጣት አልያም ግዴታ ሆኖባቸው ስራቸው የመንግስት የመረጃ ምንጮች ላይ የተመሰረተ ይሆናል። በዚህም ሁኔታ የሚድያ ሽፋን በስልጣን ቁጥጥር ስር ይወድቃል። ይህም ማለት ጋዜጠኞች የሚያቀርቡት መረጃ ከከፍተኛ የመንግስት አስተዳደር ተነስቶና በልሂቃኑ አልፎ በሚቀመርበት ሂደት (Cascading Activation) ውስጥ ይወድቃል" ይላል።

የሚድያ ነፃነትን ማክበርና ከመንግስት ቁጥጥር ነፃ የማድረግን መሰረታዊ መርህ ኢትዮጵያ በተለያዩ አለም አቀፍ ስምምነቶች ተስማምታ የፈረመችበት ቢሆንም፣ ይህንን መርህ እንዲሁም በሀገሪቱ የፀደቀውን ህግ የሚጣረስ አሰራር በአዲሱ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የቦርድ አባላት ምርጫ ላይ መተግበሩ በቀጣይነት መንግስት ሚድያውን ለመቆጣጠር ያለውን ኃሳብ ያሳብቃል በማለት ጥርጣሬያቸውን የሚገልፁ ባለሙያዎችም አሉ። 

በዚህ ጉዳይ ላይ በተለያየ ኣቅጣጫ የሚነሱት ቅሬታዎችና ጥያቄዎችም በቀጣይነት የመገናኛ ብዙኃን ስነ-ምህዳሩ ስለሚኖረው ጤነኛ ጉዞ በርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል ይጠቁማሉ።