ሚያዝያ 7 ፣ 2014

የሰባት ጎጎት ዶቢ ክስታኔ ማኅበረሰብ ተወላጆች በወረዳ የመደራጀት የ20 ዓመት ጥያቄአችን ይመለስ የሚል ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ

City: Hawassaዜና

የጉራጌ ዞን የሰባት ጎጎት ዶቢ ክስታኔ ማኅበረሰብ በመሰቃን ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በስሩ 16 ቀበሌያትን አቅፎ ይዟል። ከእነዚህ ውስጥ ጀሌ 1፣ 2 እና 3፣ ወገራም አንድ እና ሁለት፣ ድራማ፣ ይመርቾ አንድ እና ሁለት ተጠቃሽ ናቸው።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የሰባት ጎጎት ዶቢ ክስታኔ ማኅበረሰብ ተወላጆች በወረዳ የመደራጀት የ20 ዓመት ጥያቄአችን ይመለስ የሚል ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ

የሰባት ጎጎት ዶቢ ክስታኔ ማኅበረሰብ ተወላጆች የ20 ዓመት የመዋቅር ጥያቄአችን ይመለስልን የሚል ጥያቄያቸውን ለማሰማት በትላንትናው እለት ሐዋሳ በሚገኘው የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ቢሮ ፊትለፊት ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል። የሰባት ጎጎት ዶቢ ክስታቴ ማኅበረሰብ ተወላጅ የሆኑት ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ያለው በመስቃን ወረዳ ስር የመተዳደር አሰራር ተሽሮ በወረዳ መደራጀት እንዲፈቀድ ጥያቄ ሲቀርብ ስለመቆየቱ ተናግሯል። 

የማኅበረሰቡ ተወካዮች ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ በመስቃን ወረዳ ስር በቆዩባቸው ዓመታት ምንም አይነት የመንግስት አገልግሎት አለማግኘታቸውን፣ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎቻቸው ምላሽ አለማግኘታቸውን አንስተዋል።   

የጉራጌ ዞን የሰባት ጎጎት ዶቢ ክስታኔ ማኅበረሰብ በመሰቃን ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በስሩ 16 ቀበሌያትን አቅፎ ይዟል። ከእነዚህ ውስጥ ጀሌ 1፣ 2 እና 3፣ ወገራም አንድ እና ሁለት፣ ድራማ፣ ይመርቾ አንድ እና ሁለት ተጠቃሽ ናቸው።

ከማኅበረሰቡ ተወክለው አቤቱታቸውን ለማቅረብ ከመጡ ነዋሪዎች መካከል አቶ አሸናፊ ወልደ አረጋ አንዱ ናቸው። "ከወረዳ እስከ ፌደራል ድረስ ጥያቄያችንን በደብዳቤ አስገብተናል። ነገር ግን ምንም ጠብ ያለ ነገር የለም። ተበድለናል። በተለይ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች አልተመለሱም። በተጨማሪ ከወረዳው ምንም አይነት ድጋፍ እያገኘን አይደለም" በማለት አስረድተዋል።

ሰልፈኞቹ ከያዙት መፈክር መካከል "ህዝባዊ መድረኩ የሰባት ጎጎት ዶቢ ክስታኔ ተወላጆችን ያካተተ አይደለም”፣ “ጥያቄያችን ከ1994 እስከ 2014 ዓ.ም. የተጓተተው በእኛ ችግር ሳይሆን በወያኔ ስርዓትና ቅሪቶቹ ነው”፣ “የሰባት ጎጎት ዶቢ ክስታኔ ህዝብ በወረዳ መዋቅር የመደራጀት ጥያቄ በአስቸኳይ ይመለስልን” የሚሉ ይገኙበታል።

የሰልፈኞቹን አቤቱታ ያዳመጡት ከርእሰ መስተዳድር ቢሮ የተወከሉ አመራሮች ከሰልፈኞች የመጣላቸውን ጥያቄ መቀበላቸው እና "በቅርብ መፍትሔ ላይ እንደርሳለን ጊዜ ስጡን" የሚል ምላሽ መስጠታቸውንም ሰምተናል።

"የራሳችን ቋንቋ እና ባህል ያለን ህዝቦች በመሆናችን ራሳችንን በራሳችን ማስተዳደር አለብን።  ይህ ደግሞ ሕገ-መንግስታዊ መብታቻችን ነው" የሚሉት ከማኅበረሰቡ ተወክለው የመጡት ነዋሪዎቹ "ልንታሰር እና ልንጨቆን አይገባም" የሚል መልእክት ለማስተላለፍና 20 ዓመት የሞላውን በወረዳ የመደራጀት ጥያቄ ለማቅረብ ወደ ክልሉ መስተዳደር መምጣታቸውን ተናግረዋል።