ሚያዝያ 9 ፣ 2014

ለአዲስ አበባ የአየር ብክለት የትራንስፖርት ዘርፉ 60 በመቶ ድርሻ በመያዝ ከፍተኛው ሆኗል

ጤናየአኗኗር ዘይቤ

ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት ካስቀመጠው የጎጂ ብናኝ ነገሮች መጠን አንጻር የአዲስ አበባ ከተማ የብናኝ ልቀት ዓለም አቀፍ ልኬቱን በሶስት እጥፍ በልጧል

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ለአዲስ አበባ የአየር ብክለት የትራንስፖርት ዘርፉ 60 በመቶ ድርሻ በመያዝ ከፍተኛው ሆኗል
Camera Icon

Credit: Irish TImes

የአዲስ አበባ ከተማ ከ2012 እስከ 2013 ዓ.ም. የትራንስፖርት ዘርፍ የአካባቢ ብክለት ጥናት ተካሄዷል። በጥናቱም መሰረት ለአየር ብክለት ዋነኛ ድርሻ ከሚወስዱ እንደ ኢንዱስትሪ፣ ደረቅ ቆሻሻ እና የትራንስፖርት ዘርፍ መካከል የትራንስፖርት ዘርፉ ለከተማዋ የአየር ብክለት 60 በመቶውን ድርሻ በመያዝ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገልጿል።

ጥናቱን ያካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የከባቢ አየር ብክለት ክትትልና ቁጥጥር ክፍል ነው። ጥናቱ የተደረገው በተሽከርካሪዎች ዓይነት እና የመሰረተ ልማቶች ላይ ሲሆን በመለኪያ መሳሪያዎች መሰረት የጭስ ልቀታቸው ተመዝኗል። በብናኝ መለኪያዎቹ መሰረት አውቶብስ 69 ማይክሮግራም በሜትር ኩብ፣ የጭነት ተሽከርካሪዎች (ፒክ አፕ) 66 ማይክሮግራም በሜትር ኩብ፣ የቤት መኪናዎች (አውቶሞቢል) 59 ማይክሮግራም በሜትር ኩብ በየጉዞው ሆኖ ተገኝቷል።

በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የከባቢ አየር ብክለት ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ የሆኑት አቶ አክሊሉ አደፍርስ፣ “አሃዙ የአውቶብስ በካይነት ቀዳሚ መሆኑን ቢያሳይም የሚመዘኑት በጭነት አቅማቸው ነው። አውቶብስ 80 ሰዎች በአንዴ ያጓጉዛል፤ የቤት መኪናዎችና የጭነት ተሽከርካሪዎች ይሄን እናድርግ ቢሉ ምናልባትም ከ20 ጊዜ በላይ መመላለስ ይኖርባቸዋል። ይህም ብክለቱን ይጨምረዋል” ይላሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከተማ እና የአካባቢ ምህንድስና መምህር አቶ መሳይ ሸምሱ ጥናቱ የአየር ብክለት በከተማዋ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን የሚያመላክት መሆኑን ይገልፃል። ለብክለቱ ዋነኛ መንስኤዎች የሚሆኑት የተሽከርካሪ እድሜ እና የነዳጅ ጥራት መሆናቸውን የሚጠቅሰው ባለሙያው፣ “ይህ የሚያሳየው የመንግስት ውሳኔዎች የሚያስፈልጉት መሆኑን ነው። ትኩረት የሚሹ እና ነዋሪዎች በራሳቸው ማስተካከል የማይችሏቸውን ጉዳዮች በፖሊሲና መመሪያ መደገፍ ያስፈልጋል” በማለት ይናገራል።

በጥናቱ መሰረት ተሽከርካሪዎች ከአገልግሎት ዘመን በላይ ማገልገላቸው፣ የትራፊክ መጨናነቅ፣ ሞተር አልባ ትራንስፖርት ዘዴዎችን የመጠቀም ልምድ ማነስ፣ ጥቅም ላይ የሚውሉ የነዳጅ ምርቶች ጥራት አለመጠበቅ፣ ጊዜውን እና ጥራቱን የጠበቀ የተሽከርካሪዎች ጥገና አለመደረግ እንዲሁም መሰረት ልማቶች አረንጓዴ ልማትን ታሳቢ አለማድረጋቸው የአየር ብክለት መንሳኤዎች መሆናቸው ተረጋግጧል።

በቢሮው የከባቢ አየር ብክለት ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ዋሚ ቁምቤ ጥናቱ የራሱ መሰረታዊ መነሻ ያለው እንደሆነ ያስረዳሉ። ጥናቱ ከ469 የተለያዩ ተሽከርካሪዎች የጭስ ልቀት ናሙና ተወስዶ የተሰራ ሲሆን በአማካይ የሁሉንም ተሽከርካሪዎች ልቀት እና የብክለት መጠንን መለየት አንደተቻለ አቶ ዋሚ ይናገራሉ።

ጥናቱ እንደሚጠቁመው የናፍጣ ነዳጅ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛውን ብክለት የሚያደርሱ ናቸው። በእነዚህ መንስኤዎች የሚከሰቱ በካይ ጋዞች፣ የብናኝ ነገሮች ክምችት (Particulate Matters)፣ ካርቦን ዳይኦክሳይድ፣ ካርቦን ሞኖኦክሳይድ፣ ናይትሮጂን ዳይኦክሳይድ፣ ሰልፈር ዳይኦክሳይድ እና ሃይድሮ ካርቦን ሲሆኑ በሰዎች ጤና እና በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ጫና ከፍተኛ ነው።

የእንግሊዙ በርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ እኤአ ከ2017 እስከ 2020 በምስራቅ አፍሪካ ከተማዎች ያለውን የአየር ብክለት በተመለከተ ባቀረበው ጥናት ብናኝ ነገሮች (particulate matters) ከፍተኛ ጉዳት ከሚያደርሱት ውስጥ ሆነው ተገኝተዋል። በዩኒቨርሲቲው ጥናት ውስጥ በአዲስ አበባ የአውቶብስ ተሽከርካሪዎች ላይ ተወስኖ በተደረገው ጥናት በከተማው የዓለም ጤና ድርጅት አማካይ ልኬቶችን ያለፈ እና ከፍተኛ የጤና እክል የሚያስከትል ብክለት መኖሩን ተመላክቷል።

ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት በአየር ውስጥ መገኘት ያለበት የጎጂ ብናኝ ነገሮች ፓርቲኩሌት ማተር (PM) መጠን ደረጃን ከ10 እስከ 15 ማይክሮግራም በሜትር ኩብ ያስቀመጠ ቢሆንም የአዲስ አበባ ከተማ የብናኝ ልቀት ዓለም አቀፍ ልኬቱን በሶስት እጥፍ በልጦ 38 PM ማይክሮግራም በሜትር ኩብ ሆኗል።

በበርኒንግሃም ዩኒቨርሲቲው ጥናት ቀጥተኛ ብክለት የሚያደርሱ ተብለው የተለዩት ብናኝ ነገሮች፣ ካርቦን ዳይኦክሳይድ፣ ካርቦን ሞኖኦክሳይድ፣ ናይትሮጂን ሞኖኦክሳይድ ዋነኞቹ ናቸው። ውህደት በመፍጠር አየርን የሚበክሉ ሆነው የተገኙት ደግሞ የሚተኑ ጋዞች፣ ብናኝ ነገሮች፣ ሀይድሮ ካርቦን፣ ናይትሮጂን ኦክሳይድ፣ ሰልፈሪክ አሲድ፣ ናይትሪክ አሲድ፣ አሞኒየም እና ሰልፈር ኦክሳይድ ናቸው። 

በመሰረተ ልማት ችግር ተሽከርካሪዎች በተዘጋጋ መንገድ ላይ ቆመው መቆየታቸው ሌላኛው የብክለት መንሳኤ ነው። የደረቅ ቆሻሻዎች ወደ ውሃ መውረጃዎች መግባትና በዝናብ ጊዜ መውጣታቸውም ለአየር ብክለቱ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው።

እነዚህ በካይ ጋዞች የሚያደርሱት ተፅዕኖ የአካባቢያዊ እና የጤና ተብሎ በጥናቱ ተከፍሏል። በርካታ የጤና እክሎች ከአየር ብክለት ጋር የተያያዙ ናቸው ማለት እንደሚያስችል የጥናቱ ግኝት ያትታል። በእነዚህ በካይ ጋዞች ምክንያት የከተማ ነዋሪዎች ሊጋለጡባቸው ከሚችሉ የጤና እክሎች መካከል ጭንቀት፣ ኦቲዝም፣ ካንሰር፣ የልብ ስርዓት መዛባት፣ አስም፣ ሳል፣ ራስምታት፣ የደም ግፊት፣ የአተነፋፈስ ስርዓት ችግር እና የደም ዝውውር ችግር ዋነኞቹ ናቸው።    

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በአየር ብክለት ሳቢያ በየዓመቱ እስከ 7 ሚሊዮን ሰዎች በመላው ዓለም ህይወታቸውን ያጣሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሞት የሚከሰተው በከባቢ አየር ወይም ከቤት ውጪ በሚፈጠር ብክለት ሲሆን አብዛኞቹ ተጠቂዎች ደግሞ የእድሜ መግፋት የማይታይባቸው መሆኑን ያመለክታል።

ይህ የአየር ብክለት በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ተክሎችን ከመግደል ይጀምራል የሚሉት የከባቢ አየር ብክለት ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያው አቶ ዋሚ “ክፍተኛ ብክለት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ እፅዋት መትከልና ማሳደግ ይከብዳል። ይህ የከተማዋ ብክለት አስከፊ ደረጃ ለመድረሱ አንድ ማሳያ ሲሆን በተጨማሪም ትኩረት ያልተሰጠው የአየር ብክለት ጉዳይ ህንፃዎች ላይ የመሰነጣጠቅ ችግር እስከመፍጠር ይደርሳል” ይላሉ። 

ባለሙያዎቹ እንደሚገልፁትና የከተማ እና አካባቢ ምህንድስና ባለሙያው አቶ መሳይ ሸምሱም እንደሚስማማበት፣ የአየር ብክለት በአካባቢም ሆነ በጤና ላይ የሚያደርሰው ጫና በጊዜ ሂደት የሚፈጠር በመሆኑ ትኩረት ማግኘት አልቻለም።

በአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የተሰራውን ጥናት መሰረት በማድረግ የመፍትሔ ሃሳቦች ተብለው የቀረቡት በሶስት ተከፍለዋል። ከመንግስት በኩል የሚጠበቁ እርምጃዎች ተብለው የተቀመጡት ያረጁ እና የአገልግሎት ዘመን ያለፈባቸው ተሽከርካሪዎችን ለባለንብረቶቹ ተመጣጣኝ ካሳ እየሰጡ ማስወገድ፣ የተለያዩ ሀገራት ለዓመታት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ማገድ፣ ለሞተር አልባ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምቹ መሰረተ ልማት መፍጠርና ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መፍቀድ፣ በካይ ሆነው የተገኙ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ መገደብ፣ የነዳጅ ጥራትን ማሻሻል እና ለተናበበ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ቅድሚያ መስጠት ናቸው። 

ይህን በተመለከተ ቢያንስ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከውጭ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ከ 3 ዓመታት በላይ ካገለገሉ እንዳይገቡ ለማድረግ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር እንቅስቃሴ እንደተጀመረ አባል ዋሚ ቁምቢ ይገልፃሉ።

ከህብረተሰቡ ይጠበቃሉ ተብለው ከተቀመጡት መፍትሄዎችም ሞተር አልባ የትራንስፖርት አማራጮችን ባህል ማድረግ፣ ጊዜውን እና ጥራቱን የጠበቀ የተሽከርካሪ ጥገና ማድረግ እና የቴክኒክ ብቃት ፍተሻን ማስተካከል ዋነኞቹ ናቸው። 

መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው የአየር ብክለትን በተመለከተ ተገቢውን ሽፋን እየሰጡ አይደለም የሚሉት የጥናት ቡድኑ አባል አቶ አክሊሉ አደፍርስ፣ “እለታዊ ጉዳዮችን ማቅረብ የመገናኛ ብዙኀን ሙያና ግዴታ ቢሆንም የአየር ብክለት ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ሊነፍጉት አይገባም” በማለት ያሳስባሉ። 

ከቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች አንፃር መታየት ስላለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አቶ መሳይ ሸምሱ ሲናገር፣ “የአየር ብክለት ዓለም አቀፍ ችግር ነው። ነገር ግን እንደ ሀገር በኢትዮጵያ የከተማ መስፋፋትና ማደግ ውስን በመሆኑ በከተማ እቅዶች ላይ ከመነሻ እስከ መድረሻ ያለውን ጉዞ ለማጥበብ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል” ይላሉ።

አቶ መሳይ በሚሰጠው ማብራርያ፣ የፈረንሳይ መዲና ፓሪስን ምሳሌ ያደረገ ሲሆን ለነዋሪዎች የሚያስፈልጉ ነገሮች በሙሉ በ20 ደቂቃ ውስጥ በከተማዋ ተደራሽ እንዲሆኑ እየተደረጉ ይገኛሉ። ይህም ሞተር አልባ የመጓጓዣ አማራጮችን ከማስፋትና ከጤና ጥበቃ አንፃር ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።

“የህዝብ ትራንስፖርት ታሪፍን ምክንያታዊ ማድረግ፣ የመንገድ ክፍያን ጥናት ላይ ተመስርቶ መወሰን፣ የህዝብ ትራንስፖርት ‘የድሃ ነው’ የሚባለውን ሀሳብ የሚቀርፍና የከተማውን ነዋሪዎች ገቢ እና የተጠቃሚ ብዛት ያገናዘበ ማድረግ ተገቢና ዘላቂ መፍትሔዎች ይሆናሉ” በማለት አቶ መሳይ ጥቆማውን ያቀርባል።  

በአዲስ አበባ ከተማ እስከ 2013 ዓ.ም. ባለው መረጃ መሰረት ከ700 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ። ይህም ማለት በመላ ኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች 78 በመቶ የሚሆነው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

አስተያየት