ሚያዝያ 7 ፣ 2014

በአማራ ክልል ባለፉት 9 ወራት የ586 ሰዎች ህይወት በትራፊክ አደጋ አልፏል

City: Bahir Darዜና

የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ባለስልጣን በያዝነው ዓመት ያጋጠመው የትራፊክ አደጋ ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር ቅናሽ ማሳየቱን ተናግረዋል።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

በአማራ ክልል ባለፉት 9 ወራት የ586 ሰዎች ህይወት በትራፊክ አደጋ አልፏል

በአማራ ክልል ባለፉት 9 ወራት በትራፊክ አደጋ የ586 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፣ 488 ሰዎች ለከባድ 586 ሰዎች ለቀላል የአካል ጉዳት መዳረጋቸው ተነገረ። የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመንገድ ትራፊክ ደህንንት ቁጥጥር ቢሮ ለአዲስ ዘይቤ እንዳሳወቀው በ9 ወራት ውስጥ ብቻ 429 ተሽከርካሪዎች ወድመዋል። የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ባለሙያው አቶ በአለውቀን ሻረው “በአደጋዎቹ ከሰው ህይወት እና አካል በተጨማሪ 31 ሚልዮን ብር የሚገመት ኪሳራ ተመዝግቧል” ብለዋል።

የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ባለስልጣን በያዝነው ዓመት ያጋጠመው የትራፊክ አደጋ ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር ቅናሽ ማሳየቱን ተናግረዋል።

የሞት አዳጋ ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ29 በመቶ (251) የቀነሰ ሲሆን፤ ከባድ የአካል ጉዳት 66 በመቶ (276) ቀንሷል፣ ቀላል የአካል ጉዳት ደግሞ 29 በመቶ (241) መቀነሱን አብራርተዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸው ተሸከርካሪዎች 25 በመቶ (በ148 ተሸከርካሪዎች) ቅናሽ አሳይቷል ያሉት ባለሙያው የንብረት ውድመትን በተመለከተ ከአለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ18 ሚልዮን ብር ቅናሽ አሳይቷል።

ባለሙያው እንደተናገሩት በያዝነው ዓመት በክልሉ በወቅታዊ ችግር ምክንያት በተለያዩ የክልል አካባቢዎች መደበኛ አንቅስቃሴ አለመኖሩ፣ የግንዛቤ ፈጠራ ስራው መሻሻል እና የትራፊክ ደህንነት ቁጥጥር ስራው መጠናከሩ ለመቀነሱ ምክንያት ናቸው ተብሏል።

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መረጃ በክልሉ ለትራፊክ አደጋ መከሰት 85 በመቶው በአሽከርካሪዎች ፍጥነት ምክንያት ሚከሰት መሆኑን ያሳያል። በኢትዮጵያ በየቀኑ በአማካይ 14 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ሲያጡ 31 ያህሉ ደግሞ ለከባድ የአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ መረጃዎች ያመላክታሉ።

የትራንስፖርት ሚኒስተር በቅርቡ ባስጠናው ጥናት በአገሪቱ ከሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች 68.3 በመቶ ያህሉ ምቹ በሆኑ መንገዶች ላይ የሚከሰቱ መሆቸውና ከሚደርሱት አደጋዎች መካከል 85.9 በመቶ በአሽከርካሪው ስህተት፣ 3.3 በመቶ በተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ጉድለት፣ 2.8 በመቶ በእግረኛ ችግር፣ 0.7 በመቶ በመንገድ ችግር የሚከሰቱ መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል።

በተያያዘ በጥናቱ መሰረት ሕይወታቸው ከሚያልፈው መካከል ተሳፋሪዎች 48.1 በመቶ፣ እግረኞች 43.2 በመቶ እንዲሁም አሽከርካሪዎች 8.7 በመቶ መሆናቸው ተነግሯል።

አስተያየት