ሚያዝያ 6 ፣ 2014

በአማራ ክልል የሚገኙ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች የክልሉን መንግሥት አስጠነቀቁ

City: Bahir Darዜና

የማኅበሩ አባላት የሆኑ ተቋራጮች ከመንግሥት በጨረታ የተረከቧቸውን የግንባታ ፕሮጀክቶች ማከናወን አለመቻላቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ አስገብተዋል።

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

በአማራ ክልል የሚገኙ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች የክልሉን መንግሥት አስጠነቀቁ
Camera Icon

credit: social media

 

በአማራ ክልል በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ሊያቋርጡ እንደሚችሉ ግንባታውን በጨረታ አሸንፈው የተረከቡት የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች አስጠንቅቀዋል። 300 አባላት ያሉት የአማራ ክልል የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማኅበር እንዳስታወቀው የማኅበሩ አባላት የሆኑ ተቋራጮች ከመንግሥት በጨረታ የተረከቧቸውን የግንባታ ፕሮጀክቶች ማከናወን አለመቻላቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለአማራ ክልል ር/መስተዳደር እንዲሁም ለሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት ማለትም ለአማራ ክልል ማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ፣ ለገንዘብ ቢሮ፣ ለከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ፣ ለፍትሕ ቢሮ እና ለአማራ ብልፅግና ጉዳዩን የሚያብራራ እና ምላሽ እንዲሰጥበት የሚጠይቅ ደብዳቤ አስገብተዋል።

የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮቹ እንደሚሉት የግንባታ ቁሳቁሶች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን በመናሩ ቀድሞ በጨረታ አሸንፈው ስራውን በተረከቡበት ዋጋ ግንባታውን ማከናወን እንዳይችሉ እንቅፋት ሆኗል። በመሆኑም የዋጋ ማሻሻያ የማይደረግ ከሆነ ስራቸውን ሙሉ ለሙሉ እንዲያቋርጡ ይገደዳሉ።

የማኅበሩ ጸሐፊ አቶ ጋሻው አቧሀይ ጥያቄአቸውን ከደብዳቤ በተጨማሪ የምክርቤት አባላትን በግል በማነጋገር፣ ወደ ቢሮዎች በአካል በመሄድ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። 

“ለክልሉ መንግሥት ያስገባነው ደብዳቤ እንደተጠበቀ ሆኖ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ተቋማት በአካል ሄደናል። የችግሩን አሳሳቢነት እንዲረዱ የሚመለከታቸውን የምክርቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አባላት አግኝተን አነጋግረናል። እስከ አሁን ያገኘነው ምላሽ የለም” ብለዋል።

እንደ ጸሐፊው ማብራሪያ የግንባታ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ዋና ምክንያት ቢሆንም ከአለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የኢንዱስትሪ ውጤቶች በበቂ ሁኔታ ገበያ ላይ አለመኖር፣ የነዳጅ እጥረትና የዋጋ ጭማሪ፣ የዶላር እጥረት፣ የኮሮና ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ለግንባታ ያሸነፉበት አጠቃላይ ዋጋ ድጋሚ ተከልሶ ማሻሻያ እንዲደረግበት ለመጠየቃቸው በገፊ ምክንያትነት ተጠቅሰዋል። 

የጉዳዩን አሳሳቢነት በተደጋጋሚ ያነሳው ማኅበሩ የፌደራል ገንዘብ ሚኒስቴር ከዓመት በፊት የክልሉ መንግስት የግንባታ እቃዎችን ዋጋ እንዲያሻሽል በደብዳቤ መጠየቁን አንስቷል። የአማራ ክልል መንግሥት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምላሽ እንዳልሰጠ ለማወቅ ችለናል። 

በተያያዘ ዜና በግንባታ እቃዎች መወደድ ምክንያት ሥራ የፈቱ የግንባታ ባለሙያዎች ችግር ላይ መውደቃቸውን የግንባታ ሞያ ላይ የተሰማሩት ግለሰቦች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግንባታ እቃዎች ዋጋ መናር ትልልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው የመንግስት ፕሮጀክቶችን ከመፈታተኑ በተጨማሪ የግንባታ ሰራተኞችን ገቢ ጎድቷል።

ራሱን እና ቤተሰቡን በግንባታ ስራ በመስራት የሚያስተዳድረው ታደሰ ይግዛው የባህርዳር ከተማ ነዋሪ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ስራ መፍታቱ ለችግር እንደዳረገው ይናገራል። 

“ሁለት ልጆቼን በግል ትምህርት ቤቶች አስተምራለሁ። ቤት ኪራይ አለብኝ። ባለቤቴም በኮንስትራክሽን ስራው ውስጥ ስላለች ችግሩን የከፋ አድርጎታል” ይላል።

የማኅበሩን ጥያቄ በተመለከተ የከልሉን መንገሥት ምላሽ ለማካተት በአዲስ ዘይቤ በኩል ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።