በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኘው ደቡብ ኦሞ ዞን በሰሜን እና ደቡብ አሪ፣ በጋዘር እና ቶልታ ወረዳዎች በተከሰተ ግጭት የ4 ሰው ህይወት ሲያልፍ 54 የሚጠጉ ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል። በተጨማሪም ለጊዜው ግምቱ ያልተሰላ የግለሰቦች እና የመንግሥት ቢሮዎች ንብረት ሲወድም የ117 ሰዎች ቤት ተቃጥሏል።
የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፉ እንደገለፁት በግጭቱ የመኖሪያ ቤታቸው እና የንግድ ሱቆቻቸው የወደመባቸው ዜጎች መከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ጸጥታ አካላት በሚገኙበት አካባቢ አንደተጠለሉና ጂንካ ከተማ የሚገኘው ቀይ መስቀል ማኅበር ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አሪ ወረዳ ወደ ዞን እንዲያድግ የቀረበው ጥያቄ መልስ ሳይሰጥበት ዘግይቷል በሚል ሰበብ የተነሳው ግጭት በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት ሆኗል።
ጥያቄ አቅራቢዎቹ “የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት በተነሳው የአሪ ወረዳን በዞን የማደራጀት ጥያቄ ላይ አለመወያየቱ ስህተት ነው። ለተግባራዊነቱም ዘግይቷል” የሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ ንጋቱ ዳንሳ ከግጭቱ በኋላ በሰጡት ምላሽ፣ “ምክር ቤቱ የአሪን ህዝብ የመዋቅር ጥያቄ በአጀንዳ ይዞ ባለመወያየቱ የአሪ ህዝብ መቆጣቱን ተመልክተናል፤ ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ እንጠይቃለን” ብለዋል።
ሚያዝያ 1 ቀን ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ የአሪ ወረዳ አሁን ከሚገኝበት አደረጃጀት ወደ ዞን ማደግ አለበት በሚል የኃይል እንቅስቃሴ የጀመሩት ወጣቶች ያነሳሱት ግጭት ወደ ጂንካ ከተማ እና “ቶልታ”፣ “ሜጸር”፣ “ጋዘር”፣ “ዎባ አሪ” ወደሚሰኙ የመኖርያ መንደሮች መስፋፋቱ ተነግሯል።
“የአካባቢው ነዋሪ አሁንም በስጋት ላይ ነው” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ የተናገሩት የጂንካ ነዋሪ አቶ ደረሰ ዓለሙ ወረዳው በዞን መደራጀቱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በፍጥነት መመለስ እንደሚያስችለው ያምናሉ።
ከመዋቅር ጥያቄው በተጨማሪ በአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው፣ ማቴዎስ ውርሳዮ የተባለ የቴኳንዶ አሰልጣኝ ግለሰብ ላይ ታጣቂዎች ተኩስ መክፈታቸው ግጭቱን አባብሶታል ተብሏል። የአሪ ወረዳ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ወ/ሮ ኢየሩሳሌም ምንቲሶ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት ማስተር ኒኮ በሚል የማዕረግ ስም የሚታወቀው ግለሰቡ ራሱን ‘ሸከን’ ብሎ የሚጠራ መደበኛ ያልሆነ የወጣቶች አደረጃጀት በመምራት አመጹን አነሳስተሃል በሚል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።
የኮምዩኒኬሽን ኃላፊዋ ኢየሩሳሌም እንዳብራሩት ሚያዝያ 1 ቅዳሜ ተባብሶ ለቀጠለው ግጭት ሌላው መንስኤ ከአንድ ቀን በፊት አርብ ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች የቴኳንዶ አሰልጣኙ መኖሪያ ቤት በማቅናት ተኩስ መክፈታቸው ነው። ማስተር ኒኮ በወቅቱ ቤቱ ውስጥ ባለመኖሩ የደረሰበት ጉዳት ባይኖርም አደረጃጀታችን ወደ ዞን ከፍ ይበል የሚለውን ጥያቄ ያነገቡ ግለሰቦች ለአመጽ እንዲነሳሱ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።
የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት እንዳስታወቀው በአካባቢው ከመጋቢት 2 ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ተደርጓል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪ (ሞተር) እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ የታገደ ሲሆን ከምሽት 2 ሰዓት በኋላ የሰውም ሆነ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሏል።
የሐመር፣ የማሌ፣ የሰላማጎ፣ የሰሜን እና የደቡብ አሪ፣ የበና ፀማይ፣ የኛንጋቶም እና የዳሰነች ብሄሮች መኖርያ በሆነው ደቡብ ኦሞ ዞን የምትገኘው አሪ ወረዳ በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው የህዝብ ቆጠራ ከ300 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ይገኙባታል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ በደቡብ ክልል ሥር የሚገኙ እንደ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጉራጌ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ከምባታ ጠምባሮ፣ ስልጤ፣ ጎፋ ያሉ ከ12 በላይ ዞኖች በክልል የመደራጀት ጥያቄ አንስተዋል።
ከእነዚህም መካከል ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በህዝበ ውሳኔ ክልል የመሆን መብታቸው ተከብሮላቸዋል።