በጎንደር ዙርያ ወረዳ የሚገኙ 7ሺህ 548 አርሶ አደሮች ያለሙትን 25ሺህ 262 ኩንታል ነጭ ሽንኩርት የሚረከባቸው ማጣታቸውን ተናገሩ። በበጋ መስኖ ልማት ከፍተኛ ምርት የሰበሰቡት በለሳ እና በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ ገበሬዎች መሆናቸው ተነግሯል። ከማእከላዊ ጎንደር ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2002 ሄክታር መሬት ላይ መስኖ የለማው የነጭ ሽንኩርት ምርት ገበያ ያላገኘው በያዝነው ዓመት ከፍተኛ ምርት በመሰብሰቡ ነው።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ግብይት ባለሙያ አቶ ፈቃዱ ይግዛው ‹‹ከዚህ በፊት ያሉበት ድረስ ሄደው የገበሬዎችን ምርት የሚረከቡት ነጋዴዎች በዚህ ዓመት የቀነሱት በአቅራቢያቸው በቂ ምርት በማግኘታቸው ነው›› ብለዋል። እንደ ባለሙያው ገለጻ የዚህ ዓመት ምርት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ9 በመቶ ብልጫ ዓሳይቷል።
በነጋዴዎች እና በገበሬዎች መካከል የተፈጠረ የዋጋ አለመግባባት የገበያ ትስስሩ እንዳይፈጠር ያደረገ ምክንያት መሆኑንም ባለሙያው ተናግረዋል። ገበሬዎቹ ለውሃ መሳቢያ ጀነሬተር ያወጡትን ነዳጅ ጨምረው ያወጡት ዋጋ ነጋዴዎቹን ስላላዋጣ ሊገዟቸው አልደፈሩም።
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ነጭ ሽንኩርት ያመረቱ ገበሬዎች ለኪሳራ መዳረጋቸውን ያስታወሱት አቶ ፈቃዱ ‹‹ገበሬዎቹ የግብርና ባለሙያዎችን ምክር አለመቀበላቸው በዚህኛው ዓመትም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ጥሏቸዋል” ብለዋል።
አርሶ አደር ዋሲሁን ካሱ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ የበጋ መስኖ የነጭ ሽንኩርት አምራች ናቸው። ባለፈው ዓመት ቀይ ሽንኩርት አምርተው ገዢ በማጣታቸው ከ50 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ምርት እንደተበላሸባቸው ያስታውሳሉ። በያዝነው ዓመትም 13 ኩንታል ነጭ ሽንኩርት ቢያመርቱም ገዢ ባለማግኘታቸው የአምናው እጣ እንዳይደርስባቸው በስጋት ውስጥ መሆናቸውን ነግረውናል።
የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች ግብይት ባለሙያው አቶ ፈቃዱ መስሪያቤታቸው ገበሬዎቹን ከኪሳራ ለመታደግ እየጣረ እንደሚገኝ ተናግረዋል። “የገበያ ትስስር የመፍጠር ጥረቱ አካል የሆነ የእሁድ ገበያ በጎንደር ከተማ ከሚያዝያ 2 ቀን ጀምሮ ይሄዳል” ያሉ ሲሆን፤ ሌሎችም ምርቱ ሳይበላሽ ለረዥም ጊዜ የሚቆይበትን ብልሃት ከገበሬዎቹ እና ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመሆን እየመከሩ እንደሚገኙ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።