የመጀመሪያዎቹ ባቅላባ ቤቶች በኢትዮጵያ

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራውነሐሴ 23 ፣ 2013
City: Dire Dawaታሪክ
የመጀመሪያዎቹ ባቅላባ ቤቶች በኢትዮጵያ

ከዛሬ 90 ዓመት በፊት የየመን ዜግነት ባለቸው ሰዎች እንደ ባቅላባ፣ ሙሸበክ፣ ሀለዋ እና የመሳሰሉት ጣፋጭ የምግብ ዓይነቶች ወደ ድሬደዋ እንደገቡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በ1890ዎቹ መጨረሻ አካባቢ እንደተመሰረተች የሚነገርላት ድሬዳዋ ከተማ ከቀደምት ስልጡን ከተሞች ጎራ ትጠቀሳለች፡፡ የንግድ መናኸሪያና የምድር ባቡር ተጠቃሚ መሆኗ ብዙዎች ለስራ እና ለኑሮ እንዲመርጧት አድርጓል፡፡ አሁን ያላትን የስነ-ሕዘብ ስብጥር የፈጠረውም ይህ የአኗኗር ዘይቤዋ ነው፡፡ የሐገሬውን ሰው ብቻ ሳይሆን የውጭ ዜጎችን ጭምር ማርካ ነዋሪዎቿ ማድረግ ተችሏታል፡፡

በወቅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ጣፈጭ ምግቦቹን ለንግድ ያቀረቡት “ቀደሲ” ወይም “ሰይፍ ቀደስ” በሚል ስያሜ የሚታወቁት ሱቆች ናቸው፡፡ በአብዛኛው የድሬዳዋ ነዋሪ በምግብ ዘይት አከፋፋይነታቸው የሚታወቁት እነኚህ ሱቆች ቀዳሚው ተግባራቸው የከተማዋ መለያ የሆኑትን ጣፋጭ ምግቦች ማስተዋወቅና ማላመድ ነበር፡፡ በወቅቱ የአራት መአዘን እና የስድስት መአዘን (ዳይመንድ) ቅርጽ ያላቸው የባቅላባ ዓይነቶች በ15 እና በ20 ሳንቲም ለገበያ ያቀርብ ነበር፡፡ አሁን ካለው ጋር ሲነጻጸር በመጠን ከፍ ያለ እንደነበር የዕድሜ ባለጸጎች ይናገራሉ፡፡

ከዚህ የባቅላባ መሸጫ ብዙም ሳይርቅ የተከፈተው “አል-ሀሺሜ” ባቅላባ ቤት ደግሞ እስከአሁን ድረስ ተወዳጅነቱን እንዳተረፈ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የድሬደዋ ተወላጅም ሆነ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶች የሀሽሜን ጣፋጭ ምግቦች ያደንቃሉ፡፡

አቶ ተስፋሁን በየነ የድሬደዋ ነዋሪ ነው፡፡ ተወልዶ ባደገባት ድሬደዋ የሀሺሜን ጣፋጭ ምግቦች ሊገዛ ተሰልፎ አግኝተን አነጋግረነዋል፡፡ ተስፋሁን ከልጅነቱ ጀምሮ የዚህ ባቅላባ ቤት ደንበኛ እንደሆነ፣ ከድሬዳዋ ውጭ የሚኖሩ ጓደኞቹ ሳይቀሩ ለማንኛውም ጉዳይ ድሬዳዋ ሲመጡ አል-ሀሺሜን ሳይጎበኙ እንደማይሄዱ አጫውቶናል፡፡

የሀሺሜ ጣፋጭ መሸጫ ሰራተኛ የሆነው አብዲ “ከሰባት ዓመት በላይ ሰርቻለሁ” ይላል፡፡ ሁሌም በተመሳሳይ ሞራል እንደሚሰሩ ገልፆ ብዙ ዓይነት ደንበኞች እንደሚያጋጥማቸውም ገልፃል፡፡ ደንበኞቻቸውንም ሁልጊዜም በተገቢው መልኩ እንደሚያስተናግዱ ተናግሮ በተለይ ማታ ማታ በጣም ብዙ ደንበኞች እንደሚመጡና እንደሚዋከቡ ተናግሯል፡፡

ባቅላባ የሚዘጋጀው ከዱቄት፣ የቀለጠና ሎሚ የተጨመረበት ስኳር እና የተፈጨ ለውዝ የሚደረግበት ሲሆን የማብሰያው እቃ ደግሞ ፓትራ ይባላል፡፡ በተለይ ባቅላባ በትኩስነቱ የበለጠ ጣፋጭ እንደሆነና እነሱም ለደንበኞቻቸው ሁሌም በትኩስነቱ ለማቅረብ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግሯል፡፡ ብዙ ደንበኞችም ስላላቸው በብዛት ሳይቆይ ቶሎ ቶሎ እንደሚጨርሱ ነግሮናል፡፡

ሊባኖስ ዮሴፍ የተባለች የድሬደዋ ነዋሪ ደረቅ ሀለዋ በጣም እንደምትወድ ገልፃ ትኩሱን መብላት ስትፈልግ ሁሌ ወደ ሀሺሜ ትመጣለች በተለይ ከስራ መልስ ከጓደኞቿ ጋር ብዙ ሆነው ስለሚመጡ እንደልባቸው መስተናገድ ስለሚፈልጉ ቦታው አመቺና ከሌሎች ባቅላባ ቤቶች አንፃር ስፋቱም እንደሚመቻቸው ተናግራለች በተለያም የጥንት ጣፋጭ መሸጫ በመሆኑ ልጆች እያሉ ከሰፈር ልጆች ጋር እየተደበቁ እየመጡ ይበሉ እንደነበር ተናግራ በሰአቱ ባቅላባ 50 ሳንቲም እንደነበርና 50 ሳንቲም ለማግኘት ከባድ እንደነበር ትውስታዋን አጋርታናለች፡፡ አል-ሀሺሜም የዚን ያህል መቆየቱ ብዙ ሰዎች በድሮ ስሙ ስለሚያውቁት ደንበኞቹም ከዘመን ዘመን ሳይቀንሱ እንዲቆዩ አድረጓቸዋል ስትል የግል አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

የማርኬቲንግ ባለሞያ የሆነችው ፀጋነሽ መለሰ እንዴት የዚህን ያህል ጊዜ አንድ የንግድ ድርጅት ደንበኞቹ ሊቆይ ይችላል የሚል ጥያቄ አንስተን ባወራንበት ወቅት በተለይ ምግብ ነክ አገልግሎቶች ለረጅም ጊዜ ደንበኞቻቸው ሳይቀንሱ ለመቆየት ከባድ እንደሚሆን ጠቅሰው የአል-ሀሺሜ የጣፋጭ መሸጪያ ቤት የጣፋጮቹን ጥራት እንደተጠበቀ እስካሁን መቆየቱ እና ጣእሙ ሳይቀየር መቆየቱ እንዲሁም ቦታውም አለመቀየሩ የንግድ ድርጅቱ የዚህን ያህል ጊዜ ለመቆየቱ አስተዋፅኦ አለው ሌላው ደሞ በሞያው ቋንቋ word of mouth ወይም ሕብረተሰቡ ስለጣፋጭ መሸጫው የሚያወራው ጥሩ ስለሆነ ምንም ዓይነት ማስታወቂያ መስራት ሳያስፈልገው ከራሱ አልፎ ድሬደዋን ማስተዋወቅ መቻሉን የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል ስትል ሞያዊ አስተያየቱዋን ገልፃ የአል-ሀሺሜ ጣፋጭ መሸጫ የግል ንግዳቸውን ከማሳደግ በተጨማሪም ድሬደዋ በጣፋጭ ምግቦቿ እንድትታወቅ እንዳደረጋት ትናገራለች፡፡

ፍፁም እና ፍሰሀ የተባሉ ሁለት ጓደኛሞች የ50 ዓመት ጎልማሶች ሲሆን በልጅነታቸው የአንድ ብር 10 ጃጁር ለዛውም መጠኑ ከአሁኑ የተሻለ እንደነበር ገልው በአሁኑ ሰዓት ካለው ዋጋ ጋር ሲያነፃፅሩጽሩት ብሩ ውድ እንደሆነ ምክንያቱም ሀምሳ ሳንቲም ይገዙት የነበረው ባቅላባ በአሁን ሰአት ሰባት ብር እንደሆነና ይህም ከመጠኑ አንፃር ተገቢ እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡

Author: undefined undefined
ጦማሪዝናሽ ሽፈራው

I graduated from Bahir dar university in the field of journalism and communication, and a reporter at Addis Zeybe in Dire Dawa branch.