የኤ ቲ ኤም ማሽኞች ከሰሞኑ ምን ነካቸዉ?

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታነሐሴ 26 ፣ 2013
City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮች
የኤ ቲ ኤም ማሽኞች ከሰሞኑ ምን ነካቸዉ?

“ከአንድ ቀን በፊት ነው በንግድ ባንክ በኩል ደሞዝ የገባልኝ። ገንዘብ ለማውጣት በአቅራቢያዬ ወደአገኘሁት የብርሃን ባንክ ኤቲኤም ማሽን ጎራ አልኩ። ልክ ካርዱን ማሽኑ ውስጥ አስገብቼ ማውጣት የምፈልገው ገንዘብ ሞልቶ ማሽኑ ብሩን መቁጠር እንደጀመረ መብራት ተቋረጠ። ካርዱም ብሩም ማሽኑ ውስጥ ቀረ” የሚለዉ አቶ ግሩም ጭጭአይበሉ ነዉ።

ግሩም ይህን ገጠመኝ ተከትሎ ኤቲኤም ማሽኑ አጠገብ ወደሚገኘው የብርሃን ባንክ ቅርንጫፍ ሄዶ ሲያመለክት መታወቂያ ጠይቀው ካርዱን መለሱለት። “ገንዘቡ መቆረጡ የፅሑፍ መልእክት ደርሶኛል” ብሎ ቢጠይቅም የባንኩ ሰራተኛ “እርሱን ወይ ንግድ ባንክ ሄደህ አሊያም 951ላይ ደውለህ አመልክት” የሚል ምላሽ አንደሰጠዉ ይናገራል። 

ምላሹን በመቀበል ወደ ንግድ ባንክ የጥሪ ማዕከል በመደወል የገጠመውን ችግር አስረዳ። ስልኩን ያነሳችዉ ሠራተኛም “ገንዘቡ ከስምንት እስከ አስር ቀን ባለው ጊዜ ወደ ሂሳብዎ ይመለስሎታል” ማለቷንም ያነሳል።

የቤት ኪራይ እንደደረሰበትና ያን ለመክፈል ሌላ አማራጭ እንደሌለዉ ቢገልጽም ገንዘብ ያወጡት ከንግድ ባንክ ማሽን ውጪ ስለሆነ ከባንኩ መረጃ ማግኘት እንደሚገባ ተነግሮት ስልኩ አንደተዘጋ ይናገራል፡፡“ይኸው አሁን ከቤቴ ከምባረር ብዬ ከስምንት ቀን በኋላ የሚከፈል ብድር እየፈለግኩ ነው”ይላል።

በተመሳሳይ አቶ እዮብ ገዛሀኝ ተመሳሳይ ነገር እንደገጠመዉ ይናገራል። በአዋሽ ባንክ የኤቲኤም ካርድ ከዳሽን ባንክ ማሽን ብር ለማዉጣት ሲሞክር ማሽኑ ብሩን ከቆጠረ በኋላ ካርዱን መልሶ ብሩን ሳይሰጠዉ ቀረ። ባቅራቢያዉ ያሉ የጥበቃ ሰራተኞችን ሲያናግራቸዉ ሌሎች ደንበኞችም ተመሳሳይ ችግር አንደገጠማቸዉ ይነግረዋል፡፡

እዮብም ወዲያውኑ ወደ ባንኩ ጎራ በማለት የቅርንጫፉን ሀላፊ ሲያናግር ጉዳዩ ባንኩን የማይመለከት እንደሆነና የኤቲኤም ካርዱን ያወጣበት ባንክ ሄዶ አንዲጠይቅ መደረጉን ይነገረዋል። እዮብ አሁን ላይ ማመልከቻዉን ለአዋሽ ባንክ አስገብቶ ገንዘቡ የሚመለስበትን ቀን እየጠበቀ እንደሚገኝ ነግሮናል፡፡

ባንኮች ደንበኞቻቸዉ ባሻቸዉ ጊዜ ገንዘብ አንዲያወጡ በየደጃፋቸዉና በሌሎች ቦታዎች ጭምር ያስቀመጧቸዉ አዉቶማቲክ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ከሰሞኑ እክል እየገጠማቸዉ ደንበኞችን እያጉላሉ እንደሚገኝ እነዚህን መሰል መረጃዎች ለአዲስ ዘይቤ እየደረሱ ይገኛሉ፡፡

በተለይ በአንድ የኤቲኤም ካርድ ከሌሎች ማሽኖች ገንዘብ ለማዉጣት የሞከሩ ደንበኞች ሂሳባቸዉ ተቀንሶ ነገር ግን ማሽኖቹ ገንዘቡን ሳይሰጣቸዉ እንደቀረ ይናገራሉ፡፡ ችግሩም ባሳለፍነዉ ሳምንት ጀምሮ እስከዚህኛዉ ሳምንት ተሻግሮ ደንበኞችን እያማረረ መሆኑን ተረድተናል፡፡

ለመሆኑ በኤቲኤም ማሽኖች ላይ ያጋጠመ የተለየ የቴክኒክ ችግር ይኖር ይሆን ስትል? አዲስ ዘይቤ የተወሰኑ ባንኮችንና የኤቲኤም ማሽኖችን ተቀናጅተዉ እንዲሰሩ ያደራጀዉን ኩባንያ አነጋግራለች፡፡

በሀገራችን በደንበኞች ቁጥር የመመሪያዉን የሚይዘዉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የህዝብ ግንኙነት ክፍል አቶ የአብስራ ከበደ ባንኩ የሚጠቀመዉ ቴክኖሎጂ በአሁኑ ሰዓት በአለም ላይ ያለዉን አሰራር እንደሆነና በሲስተሙ ላይ ያጋጠመ ይህ ነዉ የሚባል ችግር እንዳላጋጠመ ይናገራል፡፡   

“ከደንበኞች ጋር ሂሳብ ያለአግባብ የተቆረጠ ገንዘብ ለማስመለስ ቢያንስ እስከ አምስት ቀን ያስፈልጋል። ነገር ግን አንዳንዴ የመብራት እና የኔትወርክ ሁኔታዎች ጊዜዉን ሊያረዝሙት” ሲሉ ያብራራሉ።

እንደ የአብስራ ገለፃ ጥሪ ተቀባዮቹ ስራቸው ቅሬታ አቅራቢውን መዝግቦ ለሚመለከተው አካል ማስተላለፍ ሲሆን፡ ባንኩም ይሄን ቅሬታ ተመልክቶ ወደ ሚመለከተው ባንክ ደውሎ እስኪያረጋግጥ ድረስ በመሃል የተለያዩ የሲስተም ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ።

ይሁንና እንደሰሞኑ በተደጋጋሚ ችግር ሲፈጠር ከተለያዩ ሲስተም ችግሮች ሳቢያ ስለሚሆን ከተለያዩ የባንኪንግ ኔትወርኪንግ ድርጅቶች ጋር በመወያየት መፍትሄ እንዲሰጠው እየተሰራ ነው።

ከአቶ የአብስራ ጋር ተመሳሳይ መልስ የሰጡን የአቢሲኒያ ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ኦፊሰር የሆኑት ሶስና መንገሻ ሲሆኑ “የአንድን ባንክ ኤቲኤም ይዘሽ ሌላ ባንክ ላይ ችግር ከተፈጠረ በሁለቱ ባንክ መሃል ሪኮንሲሊየሽን ማድረግ ግድ በሆነበት ሁኔታ የሚታወቀው የሀገሪቱ ከባንኮች አቅም በላይ የሆኑት የመብራት እና የኔትወርክ ጉዳዮች አሉ” በማለት፣ ነገር ግን ችግሩ የተፈጠረው የአቢሲኒያ ባንክ ኤቴኤም ከአቢሲኒያ ባንክ ካርድ ጋር ከሆነ ግን ችግሩን ሳይውል ሳያድር መፍታት እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

ይህ ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ከመስተዋሉ አኳያ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉንም ባንኮች የኤቲኤም አገልግሎት በጋራ በአንድ ማዕከል አስተሳስሮ አገልግሎቱን እየሰጠ ያለው እና የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ኩባንያ የሆነው ኢትስዊች ዋና ሃላፊ አቶ ይለበስ አዲስን “ኤቲኤም የዲጂታል ፋይናንስ አንዱ መንገድ መሆኑ ይታወቃል፣ ሆኖም በሀገራችን በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ይህ ዘርፍ እንዲነቃቃ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል”ይላሉ፡፡

ይሁን እንጂ በዲጂታል ሲስተም ባንኮችን አስተሳስሮ ገንዘብ ማዘዋወር የሚያስችለው ይህ መንገድ በተለያዩ የሲስተም ችግሮች ሊስተጓጎል ይችላል። ይህ ደግሞ ከጀማሪዋ ሀገራችን ባለፈ በተለያዩ የሰለጠኑ ሀገራት ሳይቀር ይስተዋላል።”

በመሆኑም ሰሞኑን የሚቀርበው ቅሬታ ከችግሩ ተደጋጋሚነት አንጻር ተገቢ ነው የሚሉት ሃላፊው ይሁንና ከችግር የጠሩ ስርዓቶችን ለማደላደል አሁንም ኩባንያው በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አክለውም እንደዚህ አይነት ጉድለቶች እስኪጠሩ እና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እስኪሰጥ ድረስ እንዲህ ያለ ችግር በተደጋጋሚ የገጠማቸው ደንበኞች ቅሬታቸውን ማስገባት መቀጠል እንዳለባቸው እና በተጨማሪም በቀጥታ ካርዱ የወጣበት ባንክ ማሽን ላይ መጠቀማቸው ለጊዜው የተሻለ አማራጭ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

Author: undefined undefined
ጦማሪንግስት በርታ

Nigist works at Addis Zeybe as a reporter while exploring her passion for storytelling and content creation.