ነሐሴ 14 ፣ 2014

አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል-ጦርነት ያደበዘዘው የሰሜን ኢትዮጵያ ተናፋቂው በዓል

City: Gonderባህል የአኗኗር ዘይቤወቅታዊ ጉዳዮች

በትግራይ አሸንዳ፣ በሰቆጣ ሻደይ፣ በላሊበላ አሸንድዬ፣ በቆቦ ሶለል እየተባለ ቢጠራም የጋራ ትርጉሙ ለምለም ማለት እንደሆነ ይነገራል።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል-ጦርነት ያደበዘዘው የሰሜን ኢትዮጵያ ተናፋቂው በዓል
Camera Icon

ፎቶ፡ ከማህበራዊ ድረገጽ (አሽንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል በዓል ከነሃሴ 16 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል ይቆያል)

ክረምቱ ሊገባደድ ሲቃረብ ከቡሄ በዓል ቀጥሎ ከወርሃ ነሃሴ አጋማሽ ጀምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል በትግራይ፣ በጎንደር፣ በሰቆጣ፣ በላስታ እና በቆቦ አካባቢዎች በውብ ልጃገረዶች ጨዋታ ደምቆ የሚከበር በዓል አለ። ይህም በዓል እንደየቦታዎቹ ልዩነት አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል የሚል ስያሜ ይዞ በየዓመቱ ከነሃሴ 16 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል ይከበራል።

በክረምት ወቅት ከሚበቅለው ረጅም የሳር ተክል ስያሜውን እንዳገኘ የሚነገርለት ይህ በዓል በትግራይ አሸንዳ፣ በሰቆጣ ሻደይ፣ በላሊበላ አሸንድዬ፣ በቆቦ ሶለል እየተባለ ቢጠራም የወል ትርጉሙ ለምለም (እርጥብ ሳር) ማለት እንደሆነ ይነገራል። ይህንንም ተክል ቆርጠው በወገባቸው ዙሪያ በማድረግ ወዲያና ወዲህ ማወዛወዝ ዋናው የበዓሉ ምልክትና የጭፈራው አካል ነው።

በየዓመቱ ከነሃሴ 16 ጀምሮ እስከ ነሃሴ 20 ባሉት ቀናት (በአንዳንድ አካባቢዎች ለአራት ሳምንታት ሲከበር ይቆያል) የመንደሩ ሴቶች አምረውና ተውበው በቡድን በቡድን በመሆን በየሰፈሩ እየዞሩ ሲጨፍሩ የሚውሉበት፣ ያላገቡት ሴቶች በውበታችውና በአጨዋወት ችሎታቸው ከጎረምሶች ዐይን ገብተው ለትዳር የሚታጩበት፣ ከቤተሰብ ቁጥጥር ውጭ የሚሆኑበት የነጻነት ጊዜ ነው፤ ይህ የአሸንዳ ሰሞን።

ፎቶ፡ ከማህበራዊ ድረገጽ (አሽንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል በዓል በውብ ልጃገረዶች ጨዋታ ደምቆ የሚከበር በዓል አለ)

ዝናብ የጠገበው ምድር አረንጓዴ ለብሶ፣ ሳር ቅጠሉ አብቦ፣ የደፈረሱ ወንዞች ጠርተው፣ ሰማይ ብሩህ ሲሆን ወጣት ሴቶች እና ወንዶች አምሮባቸው አደባባይ ይወጣሉ። 

በዓሉን ለማክበር ሴቶች ፀጉራቸውን ጋሜ፣ ቁንጮ፣ ሳዱላና ቀጫጭን ሹሩባ ተሰረተው ሲዘጋጁ፤ ሴቶቹን አጅበው የሚውሉት ወንዶች ደግሞ ጸጉራቸውን ቁንጮ ተላጭተውና ንጹህ ለብሰው ጅራፋቸውን የሚያዘጋጁበት ወቅት ነው። ህፃናት ደግሞ ጆሯቸው ላይ ትላልቅ ክብ ቀለበት ጆሮ ጌጥ፣ መሃል ጸጉራቸው ተላጭቶ ዳርዳሩ ያደገ ቁንጮና ጋሜ ይቆረጣሉ። 

በሰሜን ወሎ ላስታ ላሊበላ እና በዙሪያው ያሉ ሴቶች ፀጉራቸውን ጋሜ፣ ቁንጮ፣ ሳዱላና በቀጫጭኑ ሹሩባ ይሰራሉ። አልባሶ፣ ጋሜ እና ድርብ ደግሞ ወደ ትግራይ ለዕለቱ የሚመረጡ የፀጉር አሰራር አይነቶች ናቸው። በበዓሉ ላይ የሚለብሷቸው አልባሳት እንደ አካባቢው ቢለያይም በአብዛኛው ሴቶች የሀበሻ ቀሚስ፣ የሻማ ጨርቅ ወይም ሽፎን የሚባለውን ሽንሽን ቀሚስ ለብሰው ይታያሉ። 

ለመድመቂያነት በጆሯቸው ላይ ጉትቻ፣ ለእጃቸወ አንባር፣ እግራቸው ላይ አልቦ፣ በአንገታቸው ላይ መስቀል፣ አሽንክታብ፣ ድሪ እና ሌሎች ጌጣጌጦችን ይጠቀማሉ። በዋዜማው ነሃሴ 15 ልጃገረዶች በቅቤና በኩል መዋብ ይጀምራሉ። የክረምቱ ዝናብ ያለመለመውን የአሸንዳ ተክል ቆርጦ ለወገብ እንዲመች ተደርጎ በማዘጋጀት እንደ አንቀልባ በወገባቸው ዙሪያ ያደርጉታል። 

ነሃሴ 16 ልጃገረዶች ተሰባስበው በጠዋት ወንዝ ወርደው እጅና እግራቸውን ይታጠባሉ። ይህም በአካል እና በመንፈስ ጽዱ እንደሚያደርጋቸው በማህበረሰቡ ይታመናል። ከዛም ቤተክርስቲያን በመሄድ ደጀ ሰላሙን ተሳልመው ለአምላካቸው ምስጋና በማቅረብ በዓሉን ማክበር ይጀምራሉ።

በአንድ ቡድን ውስጥ ከ 5 እስከ 30 የሚደርሱ ሴቶች ተሰብስበው ከመካከላቸው መልካም ባህሪ ያላቸውን መርጠው ለቡድኑ መሪነት፣ ከበሮ መችና ገንዘብ ሰብሳቢነት በመሰየም ስለ አለባበስ፣ አጊያጊያጥ እና ከማን ቤት እንደሚጀምሩ በመነጋገር የዕለቱን ውሎ ይጀምራሉ። 

በአሸንዳ፣ በሻደይ፣ በአሸንድዬ፣ በሶለል በዓል ሴቶች ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ያለቤተሰብ ተጽዕኖ እየተጫወቱ የሚውሉበት፤ ከቤት ስራ ነጻ የሚሆኑበት፣ እንደውም ቤተሰብ አልባሳትና ጌጣጌጦችን በመግዛት ልጆቹን አስውቦ ወደ በዓሉ የሚልክበት ሳምንት በመሆኑ “የሴቶች የነጻነት ጊዜ” ሊባል ይችላል።

የልጃገረዶቹ ዜማና ግጥም እምነትን፣ አመለካከትን፣ ፍቅርን እና ተስፋን በውስጡ ይዞ በጭፈራና በፈካ የፊት ገጽ ይቀርባል። በየደረሱበት ጨፍረው ብር ለሰጣቸው ሰው ሙገሳቸውን፣ ላልሰጣቸው ደግሞ በአሽሙር ትዝብታቸውን ይገልጻሉ። እናቶች የበዓሉ አካል ሆነው ባህሉ ከጥንት ጀምሮ ይዞ የመጣውን የበዓል አከባበር ስነ ስርዓት ለትውልድ እንዲተላለፍ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። ህጻናት ሴቶች የዕለቱ ተጨማሪ ድምቀት ሆነው ባህሉን ከታላላቆቻቸው በመማር ለቀጣይ አደራ ይቀበላሉ።

ፎቶ፡ሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም (በበዓሉ ላይ ህጻናት፣ ወጣት ሴቶችና እናቶች ይሳተፉበታል)

ይህ በዓል በአማራ ክልል ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል በሚል እንደየአካባቢው የተለያየ መጠሪያ ቢኖረውም አከባበሩ ግን ተመሳሳይ ነው። በአማራ ክልል ወሎ ዞን በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች ታሪካዊው ላስታ ላሊበላ ዋናው ሲሆን፤ በበዓሉ ላይ የተለያዩ የአሸንድዬ ጨዋታ ግጥሞች ይቀርባሉ።   

ሴቶቹ ከመካከላቸው ያገባች ጓደኛቸው በበዓሉ ላይ ያልተገኘች እንደሆነ ሰብሰብ ብለው ወደ ቤቷ በመሄድ 

“አለሜ ትተሽው ነይነይ፤ 

ባል ጉዳይ ነው ወይ” 

ሲሏት ባለትዳሯ ሴት ደግሞ

“ትቸውስ አልመጣም፤ 

ባል ጉዳይ ነው በጣም”

የሚል ምላሽ ትሰጣቸዋለች። በዚያን ጊዜ ባሏ ከፈቀደላት ወደ በድኑ ትቀላቀልና በአካባቢው ባሉ መንደሮች እየተዟዟሩ፤

አሸንዳዬ

አሃ አሸንዳ ሆይ፣

ሽርግፍ አትይም ወይ፣

አሸንዳ ሙሴ፣

ፍስስ በይ በቀሚሴ።

አበሙሴ አንቺ አበሙሴ፣ 

ሽርግፍ በይ በቀሚሴ።

አሸንዳዬ አሸንዳ አበባ፣

ጠብ እርግፍ እንደ ወለባ።

ምድር ጭሬ ጭሬ አወጣሁ ማሰሮ፣ 

እሰይ የእኔ እመቤት ድልድል ወይዘሮ።

ከሰፌድ ላይ አተር ኮለሌ ኮለሌ፣

የኔማ እሜቴ አንገተ ብርሌ።

እያሉ ማንጎራጎር ሲጀምሩ ቤቱ ተከፍቶላቸውና ወደውስጥ ከገቡ በኋላ የቤቱን ባለቤት ግጥም አውራጇ 

“እሜቴ አሉ ደህና ወይ”

ስትል ተቀባዬቹ በአንድነት ድምፅ

“አሉ እንጂ ግቡ ይላሉ እንጂ” ይላሉ በህብረት ዝማሬ።

በጭፈራው መሃል ላይ ሽልማት መስጠት በነገር ሸንቆጥ ከመደረግ ያተርፋል። ሽልማት ሲቀበሉ “ትሻል እሜትዬ ትሻል፤ ይሻል ጌትዬው ይሻል” በማለት አወድሰው ይሄዳሉ። በዘፈን ወይም በዝማሬ አወድሰው ሽልማት ካልተሰጣቸው ደግሞ በነገር ሸንቆጥ ማድረግ ይጀምራሉ፤ 

“መጫኛ ሲሰቀል ተጠቅልሎ ነው፣

ልጅ የረገመው ሰው መዳኛም የለው።

እናንተን አይደል ወይ የማወሳሳው፣

ቀና ብለው እዩን የሰው ጡር አለው” በማለት ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።

ፎቶ፡ሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም (በወገባቸው ዙሪያ ሳር በማድረግ ወዲያና ወዲህ ማዟዟር ዋናው የበዓሉ ምልክትና የጭፈራው አካል ነው)

በአሸንድዬ ክብረ በዓል ወቅት የክረምቱ ዝናብ እየቀለለ ስለሚሄድና መስኩ በልምላሜ የተዋበ መሆኑ፣ የአሸንድዬው ጨዋታ፣ ከሆያሆየው ድግስ ጋር ተደምሮ ልዩ ጊዜ ያደርገዋል። ልጃገረዶች በየመንደሩ እየዞሩ ሽልማታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ሁሉም ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ በዘፈንና በዜማ ውድድር ያደርጋሉ። 

በዚህ ውድድር ላይ ጎረምሳው ዐይኑ ያረፈባትን ቆንጆ ጎንተል (ነካ) በማድረግ እንደወደዳት ምልክት ያሳያታል። ሴቷ ከፈቀደች ወደሱ ሄዳ አብራው ትሆናለች። ከዛም ሽማግሌ እንዲልክ ይመካከሩና ለጋብቻ ይተጫጫሉ። ልጃገረዶች በዓሉ አልቆ ሊለያዩ ሲሉ የእድሜ ባለፀጋ ሰው ቤት በመሄድ ምርቃት ይቀበላሉ። 

“ከርሞ እንገናኝ ላመት፣ እኛም ሳንሞት” 

“ያላገባም ያግባ፣ ያገባም ይውለድ ዘራችሁ የበዛ ይሁን” በማለት የእድሜ ባለፀጋዎቹ ለልጆች እድሜ ለምነው የቀጣዩን አመት እንዲናፍቁ አጓጉተው ይሸኛሉ። 

በዚህ መልክ ይህ በዓል ለብዙ ዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ሲከበር ቆይቷል። ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም መከበር በኋላ በነበሩት ዓመታት የተለያዩ ባህላዊና ኃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ሙከራ ሲደረግ ተስተውሏል። በዚህም እንቅስቃሴ አንዳንዶቹን በዓላት (የኢሬቻ እና የፊቼ ጨንበላላን በዓል በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል) በዩኔስኮ የዓለም አቀፍ ቅርስነት እስከማስመዝገብ ተደርሷል። 

የአሸንዳ በዓልን በተለይ በትግራይ ክልል በአደባባይ ክብረ በዓል (carnival) ደረጃ በማክበር ለማስተዋወቅ እና በቅርስነት ለማስመዝገብ ሙከራ እየተደረገ፤ በመቀሌና በአዲስ አበባ ከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች እየተሳተፉበት በድምቀት ይከበር እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና አምና በ 2013 ዓ.ም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በዓሉ ሳይከበር ቀርቷል። እንደውም አንዳንድ ሴቶች በበዓሉ ሰሞን የአሸንዳ ቅጠል በወገባቸው ላይ አገልድመው የጦር መሳሪያ ደግሞ በደረታቸው አንግበው ታይተዋል። 

በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት እና ስቃይ የደረሰባቸው የትግራይ፣ የጎንደር፣ የሰቆጣ(የዋግ ህምራ) እና የወሎ የአካባቢ ሴቶች፤ ያለፈውን ሀዘንና እንግልት በመርሳት መጭውን ተስፋና ምኞታቸውን ይዘው የዘንድሮውን በዓል እንደሚያከብሩ ይጠበቃል። በተስፋና በስጋት መሃል ቢሆንም እንኳ፤ ሴቶች ለምለም ሳር ይዘው በፈገግታ ተሞልተው ሲስቁና ሲጫወቱ ማየት ደስታና ብሩህ ጊዜን ያመለክታል።     

አስተያየት