በትግራይ ወጣት ልጃገረዶች በየዓመቱ አሸንዳን በጉጉት ይጠባበቃሉ። አሸንዳ ከነሃሴ 16 ጀምሮ እንደየአካባቢው ከአንድ ሳምንት እስከ አንድ ወር ድረስ በውብ ሴቶች ጭፈራ ደምቆ የሚከበር እና በማህበረሰቡ ትልቅ ተቀባይነት ያለው በዓል ነው።
የአሸንዳ በዓል ታዳጊ ሴቶች፣ ወጣት ልጃገረዶች እንዲሁም እናቶች በመሰባሰብ በቡድን በቡድን በመሆን “አሸንዳ” እያሉ በየሰፈሩ በመዟዟር ሲጫወቱ የሚቆዩበት ጊዜ ነው። ሴቶች ከጓደኞቻቸውና ከእኩዮቻቸው ጋር በመሆን ማራኪ የሆኑ አልባሳትንና ጌጣጌጦችን በመልበስ፣ የበዓሉ ዋና መገለጫ የሆነውን የአሸንዳ ቅጠል በወገባቸው ዙሪያ በማድረግ፣ወደ አደባባይ በመውጣት በየሰፈሩ በየቤቱ በመሄድ የሚጨፍሩበት ወቅት ነው።
የአሸንዳ በዓል በመላው የትግራይ አካባቢ በድምቀት የሚከበር ሲሆን የትግራይ ክልል መዲና በሆነችው በመቀሌ ከተማ በፌስቲቫል ደረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በተገኙበት ለሶስት ተከታታይ ቀናት ይከበራል። የአሸንዳ በዓል በአብዛኛው የትግራይ አከባቢዎች “አሸንዳ” በሚል ይታወቃል በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ ስያሜ ያለው ሲሆን በአክሱም “ዓይኒ ዋሪ” ይባላል።
ቆልዓ ኣሸንዳ (የአሸንዳ ልጃገረድ)
የአሸንዳ ሳምንታት ልጃገረዶቹ ''ቆልዓ ኣሸንዳ'' ወይም የአሸንዳ ልጃገረድ በመባል ይጠራሉ። የአሸንዳ ልጃገረድ በዚህ በጣም ተቀባይነት ባለውና በጉጉት በሚጠበቀው የአሸንዳ በዓል የተለመደ ልብስ ሳይሆን ለየት ያለና በተለያዩ ጌጣ ጌጦች የደመቀ ባህላዊ ልብስ ይለብሳሉ።
በዓሉ ከመድረሱ በፊት ልጃገረዶቹ ልብስ ይገዛሉ፣ ጸጉራቸው ይሰራሉ፣ ለአሸንዳ የሚሆን “አሸንዳ” የሚባል ቅጠል ከመስክ ለቅመው ያመጣሉ እንዲሁም ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ነገሮች ያደርጋሉ። በበዓሉ ልጃገረዶቹ “ሽፎን” እና በልዩ ቀለማት ያሸበረቀ ባህላዊ ቀሚስ ይለብሳሉ። በትግራይ የተለያዩ የሽፎን ዓይነቶች አሉ ከእነርሱም ሽብሽብ፣ ዝናው፣ ኮበለይ፣ ጀርሲ እና ጀዲድ የሚባሉ ይገኙበታል። የሽፎኖቹ እና የባህላዊ ልብሰቹ መልክ የተለያየ መሆን በዓሉ የበለጠ ያሸበረቀ እንዲሆን ያደርገዋል።
ቆልዓ አሸንዳ (የአሸንዳ ልጃገረዶች) የሚዋቡበት እንደ ቅርፃቸውና ስያሜያቸው የሚለያዩ የተለያዩ የጸጉር አሰራሮች አሉ። እነሱም ሽብዓተ ኣልባሶ፣ ሓምሽተ አልባሶ፣ ግልብጭ፣ ክንፊ ዓሳ (የዓሳ ክንፍ)፣ ሳርጌታ፣ አዙርኻ ሕቆፈኒ፣ ሳዱላ ተብለው ይጠራሉ። እያንዳንዳቸው አሰራሮችም የየራሳቸው የሆነ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትርጉም አላቸው።
አሸንዳ ለልጃገረዶቹ የተለየ ቀን ስለሆነ ራሳቸውን በተለያዩ ጌጣጌጦች ያስዉባሉ። እነዚህ ጌጣ ጌጦች በአንገት፣ በጸጉር፣ በግንባር፣ ጆሮ ላይ፣ እጅ ላይ እንዲሁም እግር ላይ የሚደረጉ ናቸው። አንገት ላይ የሚደረግ ሕንቆ (ግዋግው) ይባላል። በተጨማሪም ከብር እና ነሓስ የተሰሩ ከሁለት በላይ ብዛት ያላቸው መስቀሎችን ያስራሉ።
ጸጉር ላይ የሚደረገው ጌጥ ሰቁር ሲባል ግንባር ላይ የሚደረገው ደግሞ ዝተረበበ ዕንቂ ይባላል። የዚህ ጌጥ ስም ከቦታ ቦታ ይለያያል። ለአብነት በራያ አከባቢ ሱንዱድ እየተባለ ይጠራል። ጆሮ ላይ የሚደረግ ደግሞ ጓግቶ (ሕንፀ ወይም ኩትሻ) ይባላል። እጅ ላይ የሚደረገው ዝዉጦ የሚባል ሲሆን እግር ላይ የሚደረገው ደግሞ ኣልቦ ይባላል።
ለአሸንዳ የሚደረግ ጫማም ማንኛዉም ቀን ላይ እንደሚደረገው ዓይነት ጫማ ሳይሆን እንደ ቀኑ ለየት ያለ ነው። እንደ አካባቢዉም ይለያያል። ለምሳሌ በራያ አከባቢ የሚደረግ ጫማ ስፋይ ሣእኒ የሚባለው የተሰፋ ጫማ ሲሆን በሳምረ አከባቢ ቆዳ ይባላል። ቢሆንም በአብዛኛው የትግራይ አከባቢ የሚታወቀው የአሸንዳ ጫማ ኮንጎ (ሸበጥ) ነው።
በትግራይ ወጣት ሴት ልጅ አሸንዳ ከመድረሱ በፊት ብዙ ዝጅግት ታደርጋለች። ከላይ እንደተገለፀው የተለመደ ልብስ አትለብስም። በጸጉሯ፣ በጆሮዋ፣ በእጇ እና በእግሯ የተለያዩ ጌጣጌጦች በማድረግ እና በተለያዩ ቀለማት የደመቀ ባህላዊ ልብስ በመልበስ ራሷ የሚታስዉብበት ጊዜ ነው።
የአሸንዳ ጊዜ ከቤት ወጥታ የማታውቅ ልጃገረድ ሳይቀር ከጓደኞቿ እና ከእኩዮቿ ጋር ሆና ባህላዊ ዘፈን በመዝፈን እና በጭፈራ ደስታዋን ትገልጻለች። ጊዜውን የሚረዱ ወላጆችም ልጃገረዶችን ከቤት ዉስጥ ሥራም ጭምር ነጻ ያደርጓቸዋል። አሸንዳ በዓል ለልጃገረዶች የነጻነት ቀን ነው።
“የአሸንዳ ልጃገረድን አይተህ አንዳታጭ”
ሁሉም ልጃገረዶች ለአሸንዳ በተለየ ሁኔታ ስለሚዘጋጁ እና ራሳቸው ስለሚያስውቡ በትግራይ አንድ የተለመደ አባባል አለ እሱም “ቆልዓ አሸንዳ ሪእኻ አይትትሓፀ” የሚል ነው። ትርጉሙም የአሸንዳ ልጃገረድ አይተህ አታግባ የሚል ነው። ይህ የሚያሳየው ደግሞ የአሸንዳ ወቅት ልጃገረዶቹ ምን ያህል ውብ እንደሚሆኑ እና ከብዙ ውቦች መሃል አንዷን መምረጥ በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ለመግለጽ ነው።
በበዓሉ ወጣት ወንዶች ይገኛሉ?
ወጣት ወንዶች የባህል ልብስ በመልበስ ከአሽንዳ ልጃገረዶች ጋር አብረው ይሄዳሉ። አብዛኛውን ጊዜ በትር(ዱላ) በመያዝ የአሸንዳ ልጃገረዶች በማጀብ ጠባቂ ይሆናሉ።
የልጃገረዶቹ የአሸንዳ ዘፈን ምን ይመስላል?
የትግራይ ልጃገረዶች “አሸንዳዋይ ና’ዓሚ ና’ዓሚየ ተጋኒና ሎሚየ” ወይም
“አሸንዳ መፀት፤ አሸንዳ ዕምበባ መፀት” በማለት የአሸንዳ በዓል መግባቱን ያበስራሉ። አሸንዳ ከመግባቱ ከነሓሴ 16 ጀምረው የተለያዩ ዘፈኖችን በመዝፈን፣ በመጨፈር እና በመጫወት ደስታቸውን ይገልፃሉ።
ልጃገረዶቹ በዓሉን የት ያሳልፉታል?
አሸንዳ በገጠር አከባቢ በየዓመቱ ከበዓሉ ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል ይከበራል። በዚያ ጊዜ ዉስጥ ልጃገረዶቹ በቡድን ሆነው የተለያዩ ዘፈኖችን እያሰሙ በእጅ ከበሮ እና ጥሩምባ ይዘው ወደ ጎዳናዎች ይወጣሉ። ቀጥሎም ቤት ለቤት እየዞሩ ይዘፍናሉ፣ ይጫወታሉ ከቤቱም አምባሻን ጨምሮ የተለያዩ ሽልማቶች ይሰጣቸዋል። ወደ ቤት ሲገቡ፣ ከገቡ በኋላ እና ሲወጡ የሚያሰሟቸው ዘፈኖች እና ጭፈራዎች ይለያያሉ። ለምሳሌ ገና ወደ ቤት ሳይገቡ ዘበኛው የቤቱን በር እንዲከፍትላቸውና እንደዚያ ባያደርግ ደግሞ እንደሚቀየሙት በዘፈን መልክ እንዲህ ይላሉ
“ኣታ አጋፋሪ ጎይታይ በሪ ሕዘኛ፤ ክፈትዶ በሎይ ነቲ በረኛ”
“ጎይታይ ኣጋፋሪ ክፈተለይ በሪ፤ ኣነማ ከይኹሪ”
ወደ ቤቱ ከገቡ በኋላ “ኣቲ እምበይተይ ፅሓየ፤ መፅኤ ኣለኹ ናብ መፅብዓየ” በማለት ጫወታቸውን ይጀምራሉ።
ገብተው ከተጫወቱ እና ከቤቱ የተሰጣቸው ነገር ይዘው፣ የቤቱን ባለቤት “ፈሰሰ ከም ማይ ንሓሰ፤ መኾምቢያ ለይለይ ክበረት ይሃበልይ” በማለት የሰዎቹ ልግስ እና መልካምነትን ያመሰግናሉ።
ከላይ እንደተገለጸው ቤት ለቤት ብቻ ሳይሆን ተስብስበው እየዘፈኑ እና እየጨፈሩ ወደ ጎዳናዎችም ይወጣሉ። በዚያን ጊዜ በዘፈን መልክ ከወንዶቹ ብር ይጠይቃሉ። ወንዶቹ እንዳያመልጧቸው “እንክበበው” ይሉና እንዲህ በማለት ይዘፍና፡
“ክበባየ ክበባ፤ ከም ሸምባቆ ርበባ” ወይም
“ሓዛለይ ሓዛለየ ከይትሰዳለይ”
እያሉ ከበው ይዘው በመጨፈር ብር እንዲሰጣቸው እንዲህ በማለት ይሞጋግሳሉ፣ “ዘለላ ቁመትየ፤ ዘለላ ቁመትየ ሹሉም ውዕላቶ ክዳነምህረትየ” ይላሉ። የተሰጣቸውን ብር ከተቀበሉ በኋላ ደግሞ “ፈሰሰ ከም ማይ ንሓሰ” (ፈሰስ እንደ ነሃሴ ዝናብ) በማለት የተሰጣቸውን የገንዘብ ሽልማት ብዙ መሆኑን በነሃሴ ዝናብ መስለው በመግለጽ ምስጋናቸው ያቀርባሉ።
ልጃገረዶቹ አንድን አባወራ ከበው ከያዙት በኋላ በዘፈን መልክ እያሞካሹ ብር እዲሰጣቸው አብዝተው ይጠይቁታል። ሽልማቱ ከተሰጣቸው ውብ በሆኑ ባሕላዊ ዘፈኖችና ጭፈራዎች ያመሰግኑታል። የተሰጣቸው የብር መጠን ይነስም ይብዛ ተቀብለው በባህሉ መሰረት “ፈሰሰ እንደ ዝናብ ናሓሴ” በማለት ማወደሳቸው አይቀርም። ይሁንና ጨፍረው ብር ለማይሰጥ ወንድ በባህሉ ተቀባይነት ባላቸው ስድቦች ይወርፉታል። እንዲህም ይላሉ
“ዋይ እዚ ጋሕጣጢ ሽሮ ረስዒዋ ድሮ፤ ዋይ እዚ ጋሕጣጢ ክክዕ ዘይብሉ እኳ መልክዕ” ወይም
“ጎማ ስዓቱ አድጊ ሰበይቱ” አልያም “ዓመት ዓቅሪዎ አሚስ ሓሪምዎ”
የሰበሰቡትን ብር ምን ያደርጎታል ?
ሴቶቹ በአሸንዳ ጭፈራ መንገድ ላይ ወንድ በማደን እና ቤት ለቤት በመሄድ ብር፣ አምባሻ እና ሌሎች የተለያዩ ስጦታዎችን ያገኛሉ። የተገኘውን ምግብ ከጫወታው እና ጭፈራው በኋላ ተሰብስበው ይበሉታል። የሰበስቡትን ብር ግን አንድ ላይ ሆነው በአቅራቢያቸው ላለ ቤተ ክርስትያን አስተዳዳሪ ያስረክቡታል። ይህን ዓይነት ተግባር በተለይ በገጠር አከባቢ በጣም የተለመደ ነው።
በአሸንዳ የመጨረሻ ቀናት ምን ይዘፈናል?
ልጃገረዶቹ የአሸንዳ የመጨረሻ ቀናት ላይ የአከባበሩ ጊዜ እንዳለቀ ለመግለጽ እንዲህ ይላሉ፡
“ኣቦይ ቀሺ ንዑ ዳንዩና፣ አሸንዳ ከይዳ ሳኣን ብዓል ዋና” (አባ ይምጡ ይዳኙን፣ አሸንዳ ሄደችብን) ወይም ደግሞ
“አሸንዳዋይ ኸደት’የ ገረብ ተሻገረት (አሸንድዬ ሄደች ወንዝ ተሻገረች) እያሉ ይጨፍራሉ።
ጦርነቱ በዓሉ ላይ ያሳረፈው ተፅዕኖ
ይህንን የአሸንዳ በዓል በካርኒቫል ደርጃ በመቀሌና በአዲስ አበባ ከተሞች በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ በነበረበት ዓመታት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን በሀገሪቱ በተከሰተው ጦርነት በ2013 ዓ.ም በዓሉ ሳይከበር አልፏል። አሁን በአሉ በተቃረበበት ወቅት በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያ አውታሮች በሚዘዋወሩ ፎቶዎች እንደውም አንዳንድ ልጃገረዶች በበዓሉ ሰሞን የአሸንዳ ቅጠል በወገባቸው ላይ ቢያገለድሙም ፈፅሞ ባልተለመደ ሁኔታ የጦር መሳሪያ ደግሞ በደረታቸው አንግበው ታይተዋል።
በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት እና ስቃይ የደረሰባቸው የትግራይ ሴቶች፤ ያለፈውን ሀዘንና እንግልት በመርሳት መጭውን ተስፋና ምኞታቸውን ይዘው የዘንድሮውን በዓል እንደሚያከብሩ ይጠበቃል። በተስፋና በስጋት መሃል ቢሆንም እንኳ፤ ሴቶች ለምለም ሳር ይዘው በፈገግታ ተሞልተው ሲስቁና ሲጫወቱ ማየት ደስታና ብሩህ ጊዜን ያመለክታል።