ነሐሴ 18 ፣ 2014

አወዛጋቢው ድንጋይ ከሰል የማውጣት ስራ

City: Hawassaኢኮኖሚ

ከ500 በላይ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ይሳተፉበታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ እስካሁን ስራ አልጀመረም።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

አወዛጋቢው ድንጋይ ከሰል የማውጣት ስራ
Camera Icon

ፎቶ፡ እያደረ አዲስ ተሬሳ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዉስጥ የሚገኘዉ የዳዉሮ ዞን ተርጫ ዙሪያ ወረዳ በሀገሪቱ ከፍተኛ የድንጋይ ከሰል ምርት አለባቸዉ ተብለው ከተመረጡ ቦታዎች አንዱ ነው። በዚህም መሰረት ሁለት የድንጋይ ከሰል ማዕድን ማጠቢያ ማሽኖች በተርጫ ከተማ ለማስተከል የካቲት 26 ቀን ዓ.ም 2014 ዓ.ም የማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ታከለ ኡማ እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ነገር ግን ይህ መረጃ እስከ ተጠናከረበት ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም የግንባታ ስራ እንዳልተጀመረ ከዞኑ የዉሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል። 

የኢትዮጵያ ማዕድን ባለስልጣን በፊት ከቱርክ ፣ ከደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ከቻይና ወደ ሀገር ዉስጥ ሲያስገባ የቆየዉን የድንጋይ ከሰል እዚሁ ሃገር ውስጥ ለማምረት እንቅስቃሴ መጀመሩን ያስታወቀው በዚሁ አመት ነበር። በዚህም የተነሳ ለስምንት ሀገር በቀል ለሆኑ አምራች ኩባንያዎች በስምንት ከፍተኛ የድንጋይ ከሰል ክምችት ያለባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ እንዲሰሩ ፈቃድ ተሰጥቷል። 

ድርጅቶቹ ስራ መጀመራቸውንም ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እና የኩባንያዎቹ ባለቤቶች በጥር ወር 2014 ዓ.ም. ላይ በፊርማቸዉ አረጋግጠዋል። እነዚህም ኩባንያዎች በኦሮሚያ ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ  ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም በአማራ ክልሎች ውስጥ ከሚገኙት ክምችቶች ለኢንዱስትሪው የድንጋይ ከሰል እንደሚያቀርቡ የታመነባቸው ናቸው። 

ኢትዮጵያ ለሲሚንቶ እንዲሁም በዋነኝነት የኤሌክትሪክ ኃይልን ለሚፈልጉ ፋብሪካዎች የድንጋይ ከሰልን ከዉጭ ሃገር በዉድ ዋጋ ታስገባለች። ለዚህም በዓመት ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ እንደምታደርግ መረጃዎች ያሳያሉ። 

ኢንተርናሽናል ኤነርጂ ኤጀንሲ እ.ኤ.አ በ2021 ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው የድንጋይ ከሰል በዓለም 37 በመቶ ድርሻ ያለዉ ከፍተኛዉ የኤሌክትሪክ ኃይል ሰጪ መሆኑን ይጠቁማል።

በዳዉሮ ዞን የሚገኘዉ ተርጫ ከተማ ውስጥ ሊገነባ የታቀደው የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ለበርካታ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድልን ከመፍጠር ባሻገር የአካባቢውን ማህበረሰብ የረጅም ጊዜ የመሰረተ ልማት ጥያቄም ይመለሳል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ነገር ግን ይህ ተግባራዊ እንዳልሆነ በዞኑ ኢንተርፕራይዝ አማካኝት በስምንት ማህበራት የተደራጁት ወጣቶች ገልጸዋል። 

ለአዲስ ዘይቤ ቅሬታቸዉን ያቀረቡት የማህበራቱ ተወካዮች ስለጉዳዩ ሲያስረዱ "ከወራት በፊት በአካባቢው ሊገነባ  የታሰበዉ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ አገልግሎት መስጠት እስኪጀምር ድረስ በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የተደራጁ ስምንት ማህበራት ከሌሎች የድንጋይ ከሰል አምራች ኩባንያዎች ጋር ለመስራት በዞኑ አማካኝነት በተዘጋጀው ውል ላይ የተቀመጠው ዝርዝር ህግ እና ግዴታዎች ተፈፃሚ አልሆኑም ፣ የወጣቱ ድርሻ ከሚገኘዉ ትርፍ ላይ 30 በመቶ ማግኘት እንደሆነ ቢገለፅም ይህ ሳይሆን ቀርቷል" ይላሉ።  

የድንጋይ ከሰል ዋጋ እንደጥራቱ የተለያየ ነዉ፤ በዳዉሮ ዞን ከ 2,000 እስከ 4,500 ኪሎ ካሎሪ ማመንጨት የሚችሉ ምርቶች ይገኛሉ። ይህም እያንዳንዱ አይነት የተለያየ ዋጋ እንዲኖረው አድርጎታል እንደየጥራት ደረጃቸው አንድ ቶን የድንጋይ ከሰል ከ1 ሺህ 600 ብር እስከ 2 ሺህ 500 ድረስ ይሸጣሉ። በሎጂስቲክ ምክንያት ከዉጭ ሀገር የሚገባው የአንድ ቶን የድንጋይ ከሰል ዋጋ ወደ 17 ሺህ ብር ገደማ መድረሱን ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።

በሃገር ዉስጥ የሚመረተዉ የከሰል ድንጋይ ጥራቱና ደረጃዉ ከቦታ ቦታ የተለያየ መሆኑን የገለጸው የማዕድን ሚኒስቴር አስገዳጅ የሆነ መመሪያ እንዲሁም የዋጋ ተመንን በሚመለከት በግልፅ ያስቀመጠዉ ነገር የለም። ይህን ክፍተት ለማስተካከል እንደ ዳዉሮ ዞን ሌሎችም አከባቢዎች የተለያዩ አስገዳጅ አዋጆችን የያዘ ዉል አዘጋጅተዋል። የዚህ ስምምነት ዉል በዋናነት ያስፈለገዉ በማህበር የተደራጁ ወጣቶችን እንዲሁም ባለሀብቶችን ለማገናኘት መሆኑን ሰምተናል።

ቁምላቸዉ ተሾመ ኑዋን የአንድ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ነዉ። ቁምላቸው ቅሬታውን ሲገልፅ "በዉሉ ላይ የተገለጸው እያንዳንዱ መመሪያ አልተተገበረም፤ ስራ መጀመር የነበረብን ጊዜያት አልፎ ወራት ተቆጥረዋል” ሲል ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥበት በሚል ማህበራቱ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ለሚመለከተው አካል ቢያስገቡም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ይናገራል።  

በውሉ ላይ ከተቀመጡት መመሪያዎች መካከል አምራች ኩባንያዉ እና በስራ ፈጠራ የተደራጁት 500 ወጣቶች ወደ ስራ ሲገቡ ከከሰል ድንጋይ ምርት ላይ ከሚገኘዉ ትርፍ 30 በመቶ ለወጣቱ የሚሰጥ ሲሆን ለመንግስት ግብር ክፍያ እንዲሁም የባለሀብቱ ድርሻ የተቀረዉ ፐርሰንት እንዲከፈል የሚለዉ ይገኝበታል። 

ባለፉት ዓመታት በሀገር ዉስጥ የሚገኘዉ የድንጋይ ከሰል “ጥራት ይጎድለዋል ፣ የአመድ ይዘቱ እና የእርጥበት መጠኑ ከፍተኛ ነዉ እንዲሁም የኤሌትሪክ ኃይል ለሚፈልጉ ፋብሪካዎች አይሆንም” በሚል ከዉጪ ሲገባ ቆይቷል። የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ታከለ ኡማም በስድስተኛዉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት በ2014 የበጀት ዓመት ከድንጋይ ከሰል ጥራት ጋር በተገናኘ የነበረዉን ትርክት ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረው ነበር።

ይህን በተመለከተም ምርቱን ወደ ቱርክ፣ ቻይና እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ በመላክ በሶስቱም ሀገራት የተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ ዉጤት “ኢትዮጵያ ከዉጭ ሀገር ከምታስገባዉ የድንጋይ ከሰል ይልቅ በሀገር ዉስጥ ያላት ምርት የመቃጠል አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን” እንዳረጋገጠ ገልጸዋል። በተጨማሪም የዋጋ ተመኑን ለመወሰን የጥናት ስራዎች እየተካሄዱ እንደሆነ ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ሌላ የማህበር አባል የስራ ፈጠራ ዕድል ተጠቃሚ የሆኑት ወጣቶች መደራጀት የነበረባቸዉ በማዕድን አዋጁ መሰረት ቢሆንም በሃገር ዉስጥ የሚገኝ የከሰል ድንጋይ ምርትን በሚመለከት የተቀመጠ ነገር አለመኖሩ ችግር ፈጥሯል ብሏል። “ወጣቱ በትውልድ ስፍራው ስራ ሰርቶ መጠቀምና እና በተቀመጠው ውል መሰረት ወደ ስራ መግባት ነበረበት ግን ተግባራዊ አልተደረገም” ይላል ይህ ወጣት።

ይህን በተመለከተ የማዕድን ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ እንደተናገሩት አንዳንድ ክልሎች ከፋብሪካዎች እስከ 30 በመቶ የክልሉ ወጣቶች እንዲይዙ "የመፈለግ አዝማሚያ አለ"  ነገር ግን "ብዙ ፋብሪካዎች በሌሉባቸው እና ገና ብዙ ባልለሙ ክልሎች 30 በመቶ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ አይደለም" ብለዋል።

የዳዉሮ ዞን የዉሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ዋዳ “ችግሩ የተፈጠረዉ ከወጣቶቹ  ድርሻ ጋር በተገናኘ በሀገር ደረጃ የወጣ አዋጅ አለመኖሩ ነዉ” ይላሉ። 

“በኢትዮጵያ የወጣዉ የማዕድን አዋጅ ላይ በትክክል ድንጋይ አውጪ ማህበራት ይህን ያክል ድርሻ ከድንጋይ ከሰል ምርት ላይ ይጠቀማሉ በሚል የተቀመጠ ነገር የለም። ነገር ግን ስራዉ የግዴታ መሰራት ስላለበት እና በስራ ፈጠራ የተደራጀውን ወጣት ከባለሀብቱ ጋር ለማቀራረብ በዞን ደረጃ ውል አዘጋጅተናል” ያሉት ኃላፊው "70 በ 30" የሚል የዋጋ ተመን ማውጣታቸውን ገልጸዋል። 

አቶ ዮሐንስ እንደሚሉት ይህ ዉል በአሰሪዎችና ማህበራቱ መካከል ከተፈፀመ በኋላ ለአራቱ ማዕድን አምራች ባለሀብቶች ማለትም ኢስት አፍሪካ ትሬዲንግ ፣ ኬቶሮን ዳዉሮ ፣ ጎኀ ማይኒንግ እና አብሮሆት ማይኒንግ ወደ  ስራ ገብተው ቆይተዋል። ወደ ስራ የገቡት ኩባንያዎች አንድ ቶን የከሰል ድንጋይ ከ2,500 ብር ጀምሮ በዳዉሮ ዞን ከሚገኘዉ የከሰል ድንጋይ ምርት በማዉጣት ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር በገቡት የዋጋ ዉል መሰረት በተሳቢ መኪናዎች በመታገዝ ለሶስት ወራት ማስረከብ ጀምረው እንደነበርም ተነግሯል። ይህም የመሰረት ድንጋይ የተጣለለት ፋብሪካ ተገንብቶ እስከሚያልቅ ድረስ በስራ ላይ ለመቆየት ነበር።

የእነዚህ አራቱ የማዕድን አምራች ኩባንያዎች ዋና ስራ የድንጋይ ከሰል ማዕድንን በማምረት ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማቅረብ ሆኖ ቆይቷል።

በማህበር የተደራጁት ወጣቶች “በዚህ ጊዜ ለሰራነው ስራ 70/30 የሚለው ውል ቀርቶ ምንም ሳይከፈለን ወራቶች ተቆጠሩ፣ ምላሽ እንፈልጋለን” የሚል ቅሬታ ማቅረባቸዉን የዞኑ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በተለይ ተሳቢ መኪናዎች የሚመላለሱበት ድልድይ ከጥቅም ዉጪ እየሆነ በመሄዱ የመሰረተ ልማት ውድመት እየደረሰ ነው በማለት ማህበረሰቡ አቤቱታ ማቅረቡንም ጨምረው አስረድተዋል። 

ፎቶ: በዳዉሮ ዞን ተርጫ ዙሪያ ወረዳ የሚገኘዉ የድንጋይ ከሰል ምርት ተጭኖ ሲወጣ (ማህበራዊ ሚዲያ)

የዳዉሮ ዞን አስተዳደር ከማህበረሰቡ እየተነሳ የሚገኘዉን የመሰረተ ልማት ጥያቄ በተለይም በዛባ ወንዝ ላይ ያለውን ድልድይ በሚመለከት ከዚህ ቀደም ለአራቱም ማዕድን አምራች ባለሃብቶች አማራጭ ሀሳቦችን በደብዳቤ አቅርቦ ነበር። ነገር ግን ማህበራቱ ምንም አይነት ምላሽ ባለመስጠታቸው እንዲሁም የተበላሹ ድልድዮች ጥገናቸዉ እስኪካሄድና በተደራጁ ማህበራት እና በአምራች ኩባንያዎች መካከል የተገባው ውል ተፈፃሚ ሳይሆን ስራ እንዳይሰሩ እገዳ መጣሉን ኃላፊዉ አቶ ዮሐንስ ዋዳ ተናግረዋል። 

በተርጫ ከተማ ይገነባል ተብሎ የታሰበው ፋብሪካ የመሰረተ ድንጋይ ቢቀመጥለትም ከቻይና ሀገር የታዘዘው የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ማሽንን ወደ ሀገር ዉስጥ ለማስገባት ገና በሂደት ላይ እንደሚገኝና እና አሁን ላይ የተከላ እንዲሁም የጭነት አገልግሎት አለመኖሩ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሲሚንቶ ፍላጎት 7.8 ሚሊዮን ቶን በላይ ቢሆንም በቀጣይ ጊዜያት ኢትዮጵያ ዉስጥ የድንጋይ ከሰል ማምረት ይጀምራሉ የተባሉ  ፋብሪካዎች የማምረት አቅም ግን 4.5 ሚሊዮን ቶን ያልበለጠ መሆኑን የማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስትር መረጃ ያሳያል።

አስተያየት